Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዛሬው ሁለንተናዊ ለውጥ በትናንቱ ውጣ ውረድ የተገኘ ነው!

0 239

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዛሬው ሁለንተናዊ ለውጥ በትናንቱ ውጣ ውረድ የተገኘ ነው!

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

የግንቦት 20 26ኛ ዓመት የድል በዓል ከጥቂት ቀኖች በኋላ “የህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ስርዓት እየገነባች ያለች ሀገር—ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ ዕለቱን ስናከብር ውድ የህዝብ ልጆች ዛሬ ለምንገኝበት ሁለንተናዊ ለውጥ የከፈሉትን መስዕዋትነት ማሰብ የግድ ይለናል፡፡ አዎ! ሀገራችንን ወደ ላቀ ማማ እያሸጋገራት የሚገኘው ፌዴራላዊ ስርዓት የትናንት አባጣና ጎርባጣ መንገድን በፅናት የመውጣት ውጤት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ዛሬ ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሕዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ ጨለምተኞቹ ሠላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም፡፡ አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ሥራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እድገትና አንድነት ሠላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም።

ያም ሆኖ ወታደራዊው አምባገነን የደርግ ሥርዓት በተደመሰሰበት ወቅት ለሌላ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች በሀገሪቱ መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ በወቅቱ ተራማጅ አስተሳሰብን የያዙ ፌዴራሊዝም ለዘመናት ደም አፍሳሽ የሆነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ያመኑ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በአንድ ጎራ ተሰለፉ፣፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ሁለት ፅንፍ ጫፍ ላይ የወጡ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ።

በወቅቱ የታጠቁ ብሔር ተኮር ድርጅቶች መኖራቸው ቀዳሚው ጉዳይ ነበር፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ የችግሮቹ መፍትሄ መገነጣጠል ነው ብለው ያምኑም ነበር፡፡ በሌላኛው ወገን የሀገሪቱ መፍትሄ የሆነውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንደ መበታተን አደጋ በመቁጠር ባረጀ እና ባፈጀ የአንድነት ስም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎም መፈቃቀድን “በእኛ እናውቅልሃለን” የፖለቲካ እሽክርክሪት በማጦዝ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ለመክተት አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ነበሩ፡፡ ታዲያ በወቅቱ እነዚህን ተግዳሮቶች በሰከነ ብስለት በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊት ሀገርን ለመመስረት ከፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ከባድ ትግል ማካሄድ ግድ ብሎ ነበር፣፣  ውጤቱም በተራማጅ ኃይሎች አሸናፊነት እልባት አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላም ቢሆን ሁሉም ነገር ቀላል አልነበረም። መግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ሀገሪቱ ከባድ ፈተናዎች እንደገና ከፊት ለፊቷ ተደቀነባት፡፡ ከእነዚህ ፈተናዎች የላቀ ስፍራ የያዘው እና የሀገሪቱ ዋነኛ ጠላት የሆነው ድህነትን የመዋጋት ዘመቻ ነበር፡፡

ይህ የጋራ ጠላት መፍትሄ የሚያገኘው በመንግሥትና በመላ ሀገሪቱ ዜጎች  የተባበረ ክንድ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ በቅድሚያ መንግሥት የመሪነት ሚናውን በመውሰድ ህዝቡን በአስተሳሰብ ደረጃ በድህነት ላይ ድል እንዲቀዳጅ የማድረግ ኃላፊነትን በሚገባ ለመወጣት ቆርጦ ወደ ትግበራ ተገባ፡፡

በወቅቱም ድህነትን የመታገል ታላቅ ጉዞ እንዴት ሊከናወን ይቸላል? ይህን የጋራ ጠላት ተዋግቶ ለማሸነፍ መሠረታዊ የሚባሉ ቁልፍ ጉዳዮችስ ምንድናቸው? የሚሉ ዐበይት ተግባራትን መለየት ወሣኝ ጉዳይ ነበር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሀገሪቱ የበላይ ህግ የሆነውን ህገ መንግሥት ማፅደቅ ቁልፉ ተግባር ነው፡፡

ምንም እንኳን ህገ መንግሥቱን ለማፅደቅ መንግሥት መድረኩን ቢያመቻችም አንዳንድ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎችና የህዝቡን የሥልጣን ባለቤትነቱን በአቋራጭ ለመንጠቅ ያሰፈሰፉ ፀረ ሠላም ኃይሎች ሁኔታውን በቀላሉ ሊቀበሉት አልፈቀዱም፡፡

ሆኖም በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ከህዝብ የሚመነጭ መሆኑን እነዚህ ወገኖች በግልጽ እንዲያውቁ የተለያዩ ጥረቶችን ከማድረግ አልቦዘነም፡፡ እናም ሥልጣን የሚገኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰጥ ድምጽ እንደሆነም የማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ወቅት ‘ሀገሪቱ ህገ መንግሥት ሊኖራት አይገባም እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ፈዴራላዊ ሥርዓት የምትገነባ ሀገር በምንም መልኩ ተጠቃሚ ልትሆን አትችልም’ የሚሉ ተቃራኒ አመለካከቶች ዋነኛ ፈተናዎች ሆኑ፡፡ ታዲያ እነዚህ ጋሬጣዎች ዴሞክራሲያዊ ምላሽ እየተሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈቅደውና ተማምነው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትን አፀደቁ፡፡ ይህ ህገ መንግሥትም የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎች ሊመልስ በቃ፡፡

ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መግጠም ተያዘ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አረጋገጡ፡፡ ይህን በጽናት ለመዋጋትም እጅ ለእጅ ተያያዙ፡፡

ዜጎች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመሩ። ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት መሸጋገርን ተያያዙ፡፡ ውጤቱንም ማጣጣም ጀመሩ፡፡ ህገ መንግሥቱ ፀድቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እውን ከሆነ ወዲህ የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ምላሽ እያገኙ መጡ፡፡

ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ አረጋገጠላቸው፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ነበርና ነበርና ይህም ሆነ፡፡

ርግጥ በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ተችሏል፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተነፍገው  ከነበሩ መብቶቻቸው  መካከል የራስን ዕድል በራስ  መወሰን አንዱ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት  በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች  ዓለም አቀፍ  ዶኩመንቶች  የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (Self determination) ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያለፉት የኢትዮጵያ  ገዢ  መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል፡፡  

በመሆኑም በተለይም ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና  ሕዝቦች ጋር ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት  የመሳተፍ  መብት አልነበራቸውም፡፡ በአካባቢያቸው አስተዳደር ውስጥ በአመራር ላይ የሚቀመጡ አስተዳደሮችና ዳኞች በማዕከላዊ መንግስት የሚሾሙ ነበሩ፡፡ የመንግስት ሠራተኞችን ሁኔታ ብንመለከት እንኳ ሙሉ በሙሉ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ነበሩ፡፡

የአካባቢው ተወላጆች እንኳንስ መሾም ይቅርና በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ የመካተት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመሆኑም እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት  ተነፍጓቸው በሌሎች እየተተዳደሩ፤ ሀብታቸውም እተየመዘበረ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለጽጉበት ዕድል ተነፍጓቸውም ኖረዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር  ወዘተ. መብት አልነበራቸውም። አብዛኛው ቋንቋዎችን እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና  በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም   እጅግ  የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር እንዲሁም የማስፋፋት  መብታቸው  የተነፈገ እንደነበርም የኋላ ታሪካችን ያስረዳል፡፡

ከዚያም በኋላ ቢሆን ሀገራችን በተለይም ባለፉት 15 አምስት ዓመታት በአስተማማኝ ሰላም፣ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጎዳና ላይ ልትተም ችላለች፡፡ ዛሬ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በግንቦት 20 በተገኘው ድል በየደረጃው እየተጠቀሙ ነው፡፡ የታገሉለትን ሁለንተናዊ መብቶች ዕውን ማድረግ ችለዋል፡፡ ለሌሎች ጎረቤት ህዝቦችም የሰላም አለኝታ፣ በልማት የመስተሳሰርና አብሮ የማደግ ተምሳሌቶች ሆነዋል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ትናንት በተወጣው ውጣ ውረድ የተገኙ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy