NEWS

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ለመምከር ካምፓላ ናቸው

By Admin

May 02, 2017

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በዓባይ ወንዝ የውሃ አስተዳደር ዙሪያ ሊመክሩ ነው።

ሹክሪ ከፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ ኤል ሲሲ የተላከና በውሃ ደህንነትና በዓባይ ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዙሪያ የተፃፈ ደብዳቤን ለሙሴቬኒ እንደሚያደርሱም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቁሟል።

የሙሴቬኒ እና የሹክሪ ግንኙነት ኡጋንዳ እና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

ባለፈው መጋቢት ወር የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግብፅ የዓባይ ውሃን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ያሳየችውን ፍላጎት በተቃወመበት ስብሰባ፥ የግብፅ የውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስትሩ ሞሃመድ አብደል አቲ ተሳትፈው ነበር።

የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሳም ቸፕቶሪስ ከስብሰባው በኋላ እንደተናገሩት፥ በትብብር ማዕቀፉ መሰረት ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ ላይ እኩል መብት አላቸው።

አንዳንድ ሀገራት ከህዝብ ቁጥር እድገት ጋር ተያይዞ ግብፅ ዓባይን የምትጠቀመውን ያህል፥ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትን ለማምጣት መርህ እንዲቀመጥ መጠየቃቸውንም ቸፕቶሪስ ተናግረዋል።

ሙሴቬኒ በዚህ ዓመት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በነበራቸው ውይይት፥ በግብፅና በሌሎች ሀገራት መካከል በዓባይ ወንዝ ዙሪያ አለመግባባት የተፈጠረው ከመረጃ መዛባት ወይም በቂ ውይይት ካለማድረግ የመነጨ ነው ብለው ነበር።

ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሹክሪ የሚያደርጉት ውይይት በዓባይ ወንዝ ላይ የተፈጠረውን ውዥንብር እንደሚቀርፈው ይገመታል።

የኢንቴቤ ስምምነት በመባል የሚታወቀው የትብብር ስምምነት ማዕቀፉ ይፋ ከሆነበት 2010 ጀምሮ ግብፅ በናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ሳትሳተፍ የቆየች ሲሆን፥ ባለፈው መጋቢት ወር ስብሰባው ላይ ተገኝታለች።

የትብብር ስምምነት ማዕቀፉ በስድስት የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መፈረሙ ይታወቃል።

ምንጭ፡-ኦል አፍሪካ