Artcles

የግንቦት ሃያ – ትሩፋቶች

By Admin

May 12, 2017

የግንቦት ሃያ – ትሩፋቶች

ወንድይራድ ኃብተየስ

ሁለት ሣምታት ቢቀሩት ነው – ታሪካዊው ግንቦት ሃያ የድል ዕለት 26ኛ ዓመቱን ሊደፍን። በኢትዮጵያ ዛሬ ሠላም ተረጋግጧል። ፍትህ ሰፍኗል፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ተገንብቷል። እነዚህን ጉዳዮች ያመጣው ይህ ታሪካዊ ዕለት ሲከበር ታላላቅ ታሪካዊ ክስተቶችን በመዘከር ይሆናል። ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት በወደቀ ማግሥት ሟርተኞች ስለኢትዮጵያ መጻዒ ሁኔታ ሲተነብዩ ብዙ…ብዙ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያና የዩጎዝላቪያ ዕጣ ፋንታ ይገጥማታል፤ መበታተኗም አይቀሬ ይሆናል ሲሉም ተንብየዋል። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል። በወቅቱ ኢሕአዴግ እና የሽግግር መንግሥቱ በያዙት የተጠና መስመር አገሪቱን ከብተና ታድገዋታል። ከዚህም ባሻገር ዛሬ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የልማት ለውጥ አብነት እንድትሆን መሠረት ጥለውላታል። በእውነትም ውጤቶቹ በግንቦት 20 የድል ዕለት የተገኙ ስለመሆናቸው መስካሪ አያሻውም።

ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ አያከራክርም። ለዚህም የምትመራበት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ህገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲና የልማት ድንጋጌዎች ጭምር እንደሆነም  ይታመናል፡፡ በቅድሚያ ህገ መንግሥቱ በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ነው፤ በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ድንጋጌዎችም አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ጉልህ ሚና ነበረው።  

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር ውጤቱን አፋጥኖታል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ይደነግጋል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር ቀይሶ ተፈጻሚ እያደረገ ይገኛል። በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መጥቷል። ህገ መንግሥቱም በግልጽ ለነዚህ መብቶች ዋስትና ሰጥቷል።

መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና ዕድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበት በህዳር ወር 1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ መንግሥት ያረጋግጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ህገ መንግሥቱ ሁሉም ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ይደነግጋል፡፡

ከዚህም ጋር በደርግ ሥርዓት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት ጠብቆ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ እንዲከበር አድርጓል። ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል፡፡ በመሬት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በጽኑ መሠረት ላይ ጥሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት አለው። ሁሉም ዜጋ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብቱ ተረጋግጦለታል። እነዚህ ሁሉ የግንቦት ሃያ ትሩፋቶች ናቸው፡፡

መላ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔሮችና ሕዝቦች ለነጻነት ባደረጓቸው ትግሎች ወታደራዊው ሥርዓት ላይመለስ እስከወዲያኛው ተገርስሶ ወድቋል። አምባገነኑ ሥርዓት ዳግም ላይከሰት እርቆ ተቀብሯል። ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት መላ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ዘርፎች በርካታ ድሎችን ጨብጠዋል። የድል ፍሬዎቹንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ሕይወታቸው ተለውጧል። ከዚህ ማዕድ ላይ የሚያፈናቅላቸውን በዋዛ ያልፉታል ተብሎ አይጠበቅም።

 

በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ ዕድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል፡፡ በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት ዜጎች እንዳላቸውም በገሃድ ታይቷል።  

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን ዕድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብትም አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝ}ቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋስትና ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሠራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል፡፡

የግንቦት ትሩፋቶች የሆኑት የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እነዚህም የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡

የክልሎችን እኩል የመልማት ዕድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ወሣኝ መሆኑን የህገ መንግሥቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ህገ መንግሥቱ ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ይገልጻል፡፡ የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑ በግልጽ ተደንግጓልና፡፡ የልማት አጀንዳ ደግሞ ለአገሪቱ ምን ያህል አንገብጋቢ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ፈጣን ልማት ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ እየተረባረበ ይገኛል፡፡

በደርግ ሥርዓት በአገሪቱ ለዓመታት ሰፎኖ የቆየው የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ተቀይሯል፡፡ በምትኩም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በነጻ የገበያ ሥርዓት እንዲመራ ማድረግ ብሎም የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ አገሪቱን ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጓል፡፡

በዚህም የገበያ መር የምጣኔ ሀብት ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሥራ ሥምሪት ፖሊሲዎች ተነድፈው በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ የመንግሥት ዋና ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማት በማካሄድ ብሎም ፈጣንና ውጤታሚ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና መደገፍ በአንፃሩ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ባለፉት ሥርዓቶች የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለመግታት ወጥተው የነበሩ ህጐችና ደንቦች ተወግደዋል፡፡ ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ተለውጧል፡፡ በየጊዜው የተለያዩ ዕርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ ልቅ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ፈጣን፣ ዘላቂና ሰፊ መሠረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም እንደሌለው እና ይልቁንም የህዝብና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሰማሩ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

በመሆኑም በሂደት መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚና የሚጫወትበት የነፃ ገበያ ሥርዓት መከተል በአንድ በኩል ህገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግና የሕዝብ /የግሉ ዘርፍ/ እና የመንግሥት ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር እየተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንትን  /ኘሮዳክቲቭ ኢንቨስትመንት/ የሚስፋፋበት በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸው የልማት ጥያቄዎች ደግሞ በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸውን አቅጣጫ እየተከተለ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የኪራይ ምንጮችን ለመዝጋት በመሠረተ ልማትና በሰው ሀብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ተጠናክሮም ቀጥሏል – እነዚህም የግንቦት ሃያ ትሩፋቶች መሆናቸውን ልብ ይሏል።