Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግንቦት ወግ

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግንቦት ወግ

ስሜነህ

በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና እኩልነትን በማረጋገጥ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ተልእኮ ያነገበው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት የግንቦት ሃያ ቱሩፋት ነው። በህዝቦች የዘመናት ተጋድሎ በግንቦት ሃያ ድል እውን የሆነው የፌዴራል ስርአት የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መገኘቱ እና አለመገኘቱ ሊወሳ እና ሊፈተሽ ከተገባ ጊዜው አሁን ነው። በማናቸውም መለኪያ ግንቦት ሃያ የእልቂትና የብተና ምንጭ የነበረውን የብዝሃነት ችግር ከመሰረቱ በመለወጥ አገራችን ቀጣይነት ባለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ደሎች እንድታስመዘግብ ያስቻለ ያልተማከለ የፌዴራል ስርአት ለመገንባት ማስቻሉ ተረጋግጧል።

አገራችን ከ1983 በፊት የነበሩት ጨቋኝ መንግስታት ብዝሃነትን በመካድ በአስተዳደራዊ መንገድ የኢትዮጵያ አንድነትን በሃይል ለማምጣት ተረባርቦ የነበረ መሆኑ የመለኪያው ወይም የፍተሻው መነሻ ነው። በዚህም በሀገራችን ዜጎች በግል ጥረታቸው ያፈሩትን ሃብትና ቋሚ ንብረት በመውረስ በገዛ አገራቸው የበይ ተመልካች እንዲሆኑ፣ በድህነትና የእርስ በእርስ ጦርነትና ብጥብጥ፣ በተስፋ ቢስነት ህይወታቸውን ለመምራት የተገደዱባት ሃገር መሆኗ የማያከራክር ሃቅ ነው። አምባገነን ስርአቶቹ ስልጣንን አማክሎ በመቆጣጠር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሳይቀበሉና ጥያቄው በተነሳበት ቦታ ሁሉ በሃይል የመድፈቅ አቅጣጫ በመከተል አገዛዛቸውን አስፋፍተዋል። ስርአቶቹ የህዝቦችን ሰብእዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በግላጭ የሚጥሱና የማያከብሩ በመሆኑ ህዝቦች በሃገራቸው ሀብት ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆናቸው ቀርቶ ሰብአዊ ክብራቸው ተዋርዶና ተንቆ የሚኖሩባት ሃገርም የነበረች መሆኑን ማስታወስ ግንቦትን ለማውጋት  መነሻ ይሆናል።

በጥቅሉ ያለፉት አምባገንን መንግስታት ሲከተሉ በነበረው አስተዳደር የህዝባችን ማንነትና ባህል እውቅና የማይሰጥና ህዝቡ ራሱን በራስ የማስተዳደር የዘመናት ጥያቄዎቹ ተደፍቀው ከማእከል የሚታዘዘውን ትእዛዝ በመተግበር ላይ ብቻ እንዲጠመድ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን አጨናግፈው ቆይተዋል። የዴሞክራሲያዊ መብቶችን በአዋጅ እንዲታገዱ በማድረግ ከዚህ በማፈንገጥ በተፈጥሮ ያገኙትን የመናገር፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብቶችና ሃብት የማፍራትና የመዘዋወር መብቶች በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ የሃገራችን ህዝቦች በተለይም ወጣቱና ተራማጁ የህብረተሰብ ክፍል ለቀይና ለነጭ ሽብር ጅምላ ጭፍጨፋዎች ሰለባ ሆኗል።    

በአሃዳዊ አስተዳደር ተጠርንፎ ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተደፍቀው፣ ህዝቦች ባልተገደበ ሁኔታ በፍትሃዊነት የመልማት እድላቸው ተቀንብቦ የነበረበት ኋላቀርና ኢዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በግንቦት ሃያ ድል  ከመሰረቱ  ተቀይሯል። በግንቦት ሃያ ድል የተረጋገጠው ያልተማከለው የፌዴራል ስርአት በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ስርነቀል ለውጦችን አስከትሏል። ከሁሉ በፊት የዘመናት የሃገራችን ጭቁን ህዝብች ጥያቄዎች የነበሩት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት፣ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ እንዲሁም የመደራጀትና የመዘዋወር ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ተደርገዋል።  

ግንቦት ሃያ ህዝቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን የማስተዳደር ፣ በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸው በጥብቅ እንዲከበር ከማድረጉም በላይ ህዝቦች በአካባቢዊና በጋራ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ስልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ህዝቦች አካባቢያቸውን የማልማት እኩል መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ በማስቻሉም በልማት ተሳታፊና በተሳተፉት ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በልማት ወደኋላ የቀሩ አካባቢዎችም በግንቦት ሃያ ድል የማስፈፀም አቅማቸውን ለማጎልበትና የመሰረተ-ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረጉ የተመጣጠነ የክልላዊ ልማት እንዲሰፍን ሆኗል፡፡ በዚህም አማካኝነት በህገመንግስታችን ላይ የተቀመጠው  አንድ ጠንካራ ትስስር ያለው የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይ በህዝቦች እኩልነት፣ መከባበርና መፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

የግንቦት ሃያ ፍሬ የሆነው የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 52 ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ድንጋጌ አስቀምጧል። በዚህም መሰረት ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር የማዋቀር፣ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት፣ የፌዴራሉን ህገመንግስት የመጠበቅ፣ የመከላከልና፣ ህገመንግስትና ሌሎች ህጎችን የማውጣት ስልጣን ተጎናፅፈዋል። በተጨማሪም  የፌዴራሉ መንግስት በሚያወጣው ህግ መሰረት መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የማስተዳደር፣ ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ፣ የክልሉን በጀት የማውጣትና የማስፈፀም መብቶችን ተጎናፅፈዋል።  ክልሎች በክልል ውስጥ የመሰረቱትን የመስተዳድር ሰራተኞች አስተዳደር የስራ ሁኔታዎች በተመለከተ ህግ የማውጣት፣ የማስፈፀም፣ የክልል የፖሊስ ሃይል የማደራጀትና የመምራት እንዲሁም  የክልልን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ስልጣኖች የግንቦት ሃያ መሰረት በሆነው ህገ መንግስታችን ተጎናጽፈዋል።  

የኋላቀርነትና የድህነት ምሽግ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ ክልሎች በግንቦት ሃያ ድል ያልተማከለው ፌዴራላዊ ስርአት በአገራችን እውን መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አንፃራዊ ልዩነት ቢኖርም በሁሉም አካባቢዎች ፈጣን ልማት በማረጋገጥ ፣ የፖለቲካና የአስተዳደር ማእክላት እየሆኑ ይገኛሉ።   

የግንቦት ሃያ ምንጭ የሆነው የፌዴራል ስርአት ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ፣ በሃገር ደረጃ የምግብ እህል ምርት በማረጋገጥ በየወቅቱ ሊከሰቱ የሚችሉትን የምግብ እህል እጥረት በራሳችን ውስጣዊ አቅም ማሟላት የምንችልበት ደረጃ እንድንደርስ አስችሏል። የከተማና ገጠር ትስስር ለማቀላጠፍ በየክልሎቹ የሚከናወነው የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ፈጣንና በየደረጃው ህዝብ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሆነ ልማት በማረጋገጥ ደረጃ ግንቦት ሃያ ወሳኙን አስተዋጽኦ አድርጓል። በገጠር ሁሉን አቀፍ የመንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም /URRAP/ መሰረት ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከወረዳና፣ ወረዳን ከዞን ማእከላት የሚያስተሳስሩ የገጠር መንገዶች ግንባታ በግንቦት ሃያ ድል እውን መሆናቸው ከዚህ በፊት ከልማት ተገልለው የቆዩና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተዳርገው የቆዩ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና የታዳጊ ክልሎች ተወላጅ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከልማቱ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

በመላው ሃገራችን የሚገኙ ከተሞች ለዘመናት አገዛዞቹ ሲከተሉት በቆየው ኢፍትሃዊ የሃብት ድልድልና ፀረ ልማት አቅጣጫ የተነሳ ለተደራራቢና ውስብስብ ችግር ተጋልጠው ነበሩ። እነዚህ  ከተሞች ከጉስቁልናና እርጅና ወጥተው መታደስ የጀመሩት የግንቦት ሃያ ምንጭ በሆኑት ፖሊሲና ስትራቴጂዎቻችን ነው። ሁሉንም የከተማ ነዋሪ በገቢውና በአቅሙ ልክ እንደዜጋ በእኩልነትና በፍትሃዊነት ተጠቃሚ መሆን የጀመሩት ግንቦት ሃያ ቱሩፍት በሆነው ስርአት ነው።  

ይህ ስርአት በከተማ በሚኖረው ህዝብ የነቃ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት እየታገዘ በከተሞች ለስራ አጥነት ተጋልጦ የኖረውን ሰፊውን የወጣት ሃይል በየአካባቢው በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ልማት ተደራጅቶ በእንጨትና ብረታብረት ስራ ፣ በምግብና ሸቀጣሸቀጥ፣ በእደ ጥበብና ሽመና ወዘተ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቦቹን ኑሮ እንዲለውጥና እንዲያሻሽል በማድረግ ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል። በተጨማሪም ወጣቱ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በሪል እስቴት በግብአት አቅራቢነት፣ በቀለም ቅብ፣ በልስንና በአናፂነት፣ በከተሞች ድንጋይ የማንጠፍ ስራ ወዘተ እንዲንቀሳቀሱ የስልጠናና የብድር አገልግሎት ድጋፍ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንቀሳቀሾችና ቤተሰቦቻቸው ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ አድርጓል። ቀሪዎቹ በከተማና ከከተማ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችና ሌሎች ስራአጥ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በከፈቷቸው ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ሁሉም የሃገራችን ዜጎች  በመፈጠር ላይ ካለው ሃብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

በግንቦት ሃያ ድል እየተገነባ ያለው የፌዴራል ስርአት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ስርአት ነው።በዚህም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በህዝቦች መፈቃቀድና እኩልነት ላይ የተመሰረተች፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት ሃገር የመገንባት ራእይ ተቀርፆ እየተሰራ ይገኛል።በጥቅሉ ግንቦት ሃያ ፍሬ የሆነችው ሃገራችን በሰብእዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩባት፣ የዴሞክራሲ ባህልና ተቋሞች የሚያብቡበት፣ ህዝቡ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ የነቃ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥባት፣ በህዝቦች መብት መከበር፣ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠንካራ አንድነት የሚጎለብትባት ፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ስርአት ለመፍጠር  በመትጋት ላይ ስለመሆኗም ከላይ የተመለከቱት  አብነቶች  ማረጋገጫዎች ናቸው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy