Artcles

የግንቦት 20 ፍሬዎች፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት

By Admin

May 15, 2017

የግንቦት 20 ፍሬዎች፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት

ኢብሳ ነመራ

በጊዜ ጎዳና ላይ የኋሊት ልወስዳችሁ ነው፤ አራት አስርት ዓመታት ወደ ኋላ። ይህን ለማደረግ የገፋፋኝ ሰሞኑን የምናከበረው ወይም የምንዘክረው በሃገራችን ዘመናዊ ታሪክ ወደወሳኝ ምዕራፍ የተሻገርንበት የግንቦት 20 ድል 26ኛ ዓመት ነው።  

ከ1967 መስከረም ጀምሮ  በአዋጅ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት መስርቶ ሃገሪቱን ሲመራ የነበረው ወታደራዊ ደርግ በ1969/70 በመላ ሃገሪቱ በከተሞች ውስጥ በተቀሳቀሰ የተቃውሞ ትግል ክፉኛ ተንገዳግዶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ በከተሞች ጥቂት ልሂቃንንና ተማሪ ወጣቶችን ብቻ ይዞ ሲካሄድ የነበረ ትግል ዘላቂ ሆኖ ሥርአቱን ማስወገድ አልቻለም። ይሁን እንጂ ደርግን ክፉኛ ፈትኖታል። ወታደራዊው ደርግ የወጣቶቹን ትግል መከላከል  ዘውዳዊው ሥርአት መውደቁን ተከትሎ በተለይ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ሲታወጅ በዚህ ያኮረፉ ባለርስቶች አሽኮራቻቸውን አስከትለው ሲሸፍቱ እነዚህን ለመደመሰስ የቀለለውን ያህል አልቀለለውም። ወጣት ታጋዮቹ ላይ የፍየል ወጠጤ ብሎ መሸለል፣ ባላባትን ማርኮ ወይም ገድሎ የመሸለልን ያህል ቀላል አልሆነለትም። ይሁን እንጂ ህዝባዊ ተቃውሞ የወለደውን አብዮት ቀምቶ ስልጣን ላይ ጉብ ያለው ወታደራዊ ደርግ በከተሞች የተቀጣጠለውን የልሂቃንና የተማሪ ወጣቶች ትግል ለማክሸፍ ያለ የሌለ ሃይሉን አሟጦ የግፍ በትሩን ሰነዘረ።

ወታደራዊው ደርግ ህልውናውን ለማቆየት “ነጻ እርምጃ፣ ቀይ ሽብር” በተሰኙ የአፈናና የግድያ ዘመቻዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ ታሰሩ። በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ተገደሉ። ከዚህ ቁጥር የማይተናነሱ በድብደባ አካለ ጎዶሎ ሆኑ። እስሩ፣ ድብደባውና ግድያው ከ10 ዓመት እድሜ ጀምሮ ያሉ ህጻናትና ወጣቶች፣ አዛውንቶች ላይ የሚፈጸም ነበር። በዚህ ግፍ ብዙዎች የስነልቦና ቀውስ ሰለባዎች ሆነዋል።  

ወታደራዊው ደርግ በ1970 ዓ/ም በየቀበሌው አደራጅቶ ዲሞትፈርና ቺኮዝ ጠመንጃ ባስታጠቃቸው “አብዮት ጠባቂዎች” አማካኝነት ያካሄደው የቀይ ሽብር የጅምላ ግድያ ዘመቻ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በዘግናኝነቱ አቻ ያለው አይመስለኝም። በዚህ የግድያ ዘመቻ የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና አደበባዮች የሬሳ ማስጫ ሆነው ነበር። ማንነታቸውን ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ በጥይት የተደበደቡ አስከሬኖች ለመቀጣጫነት ቀኑን ሙሎ ጎዳና ላይ ተዘርግተው እንዲውሉ ይደረግ ነበር። በሌሎችም የሃገሪቱ ከተሞች የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። በአንዳንድ አካባቢዎች ይፈፀም የነበረው ግፍ ደግሞ ለመናገርም የማይመች ዘግናኝ ነበር። ጎንደርን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል።

እንግዲህ ለማስታወስ ያህል አነሳሁት እንጂ የዚያ ወቅት ታሪክ እንዲህ ባጭሩ የሚነገር አይደለም። በበቂ ሁኔታ ታሪኩ ተጽፏል የሚል ግምትም የለኝም። ለቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ የተሰራውም ሙዚየም ያኔ የተሰራውን ግፍ የሚመጥን ሆኖ አላገኘሁትም። የዚህ ዘመን ታሪክ መማሪያ ሊሆን ስለሚችል በሚመጥነው ልክ እንዲታወቅ መደረጉ ግን አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። የአስከፊ ታሪካችንን ገጽታ ማስታወስና ማወቅ ያለብን ግን ለበቀልና ጥላቻን ለመቆስቆስ ሳይሆን ዳግም እንዳይፈጸም ለመማሪያነት መሆኑን እንዲታወስ እፈልጋለሁ።

ወታደራዊው ደርግ 1970 ዓ/ም እየተገባደደ ሲሄድ ያሰረውን አስሮ፣ የገደለውን ገድሎ በከተሞች ሲካሄድ የነበረው የቀይ ሽብር የግድያና የእስርና የድብደባ ዘመቻ ጋብ አለ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ1969 የካቲት ላይ በሶማሊያ ዚያድ ባሬ ተፈጽሞ የነበረውን ወረራ በዋናነት በአርሶ አደር የህዝባዊ ሰራዊት ሃይል ተቀለበሰ። በዚህ አኳኋን ደርግ 1970 ዓ/ም መጨረሻ ላይ እፎይታ ያገኘ መሰለ። መስከረም 2፣ 1971 ዓ/ም 4ኛ ዓመት የአብዮት በአሉን በልዩ ድምቀት አከበረ። የ4ኛ ዓመት የአብዮት በአል የኩባው ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ በተገኙበት ከንጋቱ 12 ሰአት እስከ ምሽቱ 11 ሰአት ነበር የተከበረው። በነጋታው መስከረም 3 ከዚያ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ታላቅ ወታደራዊ ትዕይንት ተካሄደ። በዚህ ወታደራዊ ትዕይንት ደርግ ጦንቻውን አሳየ። “አብዮታችን ከተከላካይነት ወደአጥቂነት ተሸጋግሯል!” እያለ ፎከረ።

ይሁን እንጂ ጭቆናና ግፍ እስካለ ድረስ የህዝብ ትግል ሊቆም አይችልም። እናም ህዝባዊው ትግሉ በተለየ መልክ ቀጠለ። ትግሉ የቀጠለው እንደቀድሞው በከተሞች በየስርቻው በመታኮስ አልነበረም። ጥቂት ልሂቃንንና ተማሪዎችን ብቻ በማሰለፍም አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አብዛኛውን የሃገሪቱን ህዝብ የሚወክለውን አርሶ አደር በማሰለፍ ከገጠር ነበር የጀመረው። ይህ  በዋናነት አርሶ አደሩን ያሰለፈ ህዝባዊ ትግል በአንድ ግንባር የተከፈተ አልነበረም። ትግሉን የቀሰቀሰው ጥያቄ በዋናነት ለኢኮኖሚያዊ ጭቆናም ምክንያት የነበረው የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄ ስለነበረ፣ የብርታት ደረጃው ቢለያይም በሁሉም የሃገሪቱ አቅጣጫ ነበር። በወቅቱ ሃያ ገደማ በብሄር የተደራጁና የብሄራዊ ነጻነት ጥያቄን ያነሱ ቡድኖች የትጥቅ ትግል ያካሂዱ ነበር። ይህን እውነት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለመጨረሻ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ባደረጉት ንግግር ገልጸውታል።

ይህ በየአቅጣጫው የተለኮሰ የአርሶ አደር የብሄራዊ ነጻነት ትግል በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየበረታ ሄደ። ትግሉ በተለይ ከ1980 ዓ/ም በኋላ ወታደራዊው ደርግ ሸብረክ እንዲል አደረገው። እየታፈነ በግዳጅ ወደጦር ሜዳ የሚላከው ወጣት ህይወቱን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርብ የሚያነሳሰው ምንም ምድራዊ ምክንያት በማጣቱ ወታደራዊው ደርግ እንዳሰበው ሊዋጋ አልቻለም። ገሚሱ ባገኘው መነገድ ይሸሻል፤ እጁን ይሰጣል። እጃቸውን ከሰጡት መሃከል በርካቶች ህይወታቸውን ለመሰዋት እንዳይሳሱ የሚያደርጋቸው በቂ ምክንያት እያገኙ የነጻነት ትግሉን ተቀላቅለዋል።

ደርግ በዚህ ሁኔታ መፍረክረክ ጀመረ። በ1981 ዓ/ም ትግራይ ከወታደራዊው ደርግ ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጣች። ይህን ነጻ መሬት መነሻ ያደረገው የህብረ ብሄራዊው ኢህአዴግ ታጋይ ሃይል ወደደቡብ ያሀገሪቱ አካባቢዎች ገሰገሰ። በ1982 ዓ/ም በኤርትራ የምጽዋ ከተማና ወደብ ከወታደራዊው ደርግ ቁጥጥር ነጻ ወጡ። ይሄኔ ወታደራዊው ደርግ ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነት በአውሮፕላን ትራንስፖርት ብቻ ተገደበ። ሃይል የማንቀሰቀቀስ አቅሙም በዚያው ልክ ተዳከመ። የምጽዋ ወደብ ከቁጥጥሩ ከወጣ ጀምሮ ወደኤርትራ የመጓጓዝ አቅሙ ስለተሽመደመደ፣ አስመራን ጨምሮ በዲዝል ጄኔሬተር ሃይል ያገኙ የነበሩት የኤርትራ ከተሞች ጨለማ ዋጣቸው። ሞተሮቻቸው ጠፉ። ወታደራዊው ደርግ በዚህ ሁኔታ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ለነበሩ ተማሪዎች ቀለብ ማቅረብ ስላልቻለ፣ ዩቨርሲቲውን ዘግቶ ተማሪዎቹን ገሚሱን ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀረውን ደግሞ ወደአጋርፋ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል አጓጓዘ።

1983 ዓ/ም ለወታደራዊው ደርግ ኢሠፓ ሃይል የሽሽት፣ በተለይ ለህብረብሄራዊው ኢህአዴግ ደግሞ በድል ላይ ድል የሚቀዳጅበት ወቅት ነበር። ወታደራዊው ደርግ የብሄራዊ ውትድርና ግዳጃቸውን ጨርሰው የተመለሱ ወጣቶችን፣ ደካማ አዛውንት ጡረተኛ ወታደሮችን፣ በየቀበሌው የነበሩ አብዮት ጠባቂዎችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ወዘተ ጭምር አሰልፎ እንደሰደድ እሳት ይገሰግስ የነበረውን ህዝባዊ ትግል ለመመከት ያደረገው ጥረት መና ቀረ። ይህ ትግል የዛሬ 26 ዓመት ግንቦት 20፣ 1983 ዓ/ም የወታደራዊውን ደርግ የመንግስት ሥርአት አስወገደ።

የደርግ መወገድ ግን የትግሉ መጨረሻ አልነበረም። ዘውዳዊውና ወታደራዊው የመንግስት ሥርአቶች በህግ እውቅና ነፍገገው ለብሄራዊና ለኢኮኖሚያዊ ጭቆና የዳረጓቸው፣ በዚህ ምክንያት በየአቅጣጫው የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ የነጻነት ትግል ቡድኖች እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ የሚኖርበትን አካባቢ ወደመቆጣጠር ሄዱ። በዚህ አኳኋን ለክፍለዘመን ያህል በአሃዳዊ የመንግስት ሥርአት በብሄሮችና ብሄረሰቦች ላይ የተጫነው ጭቆና የቀሰቀሰው የነጻነት ትግል ሃገሪቱን የመበታተን ጠርዝ ላይ አደረሳት።

ይሁን እንጂ ወታደራዊው ደርግ ተወግዶ በወሩ በሃገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩና በውጭ ሃገራት በተለያየ መንገድ ስርአቱን ሲቃወሙ የነበሩ ሁሉም ሃይሎች፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን ወዘተ ቀጣይ የሃገሪቱ እጣ ላይ ለመወሰን በአንድ አዳራሽ ተሰበሰቡ። ይህ “የሰኔው ኮንፈረንስ” በመባል የሚታወቀው ጉባኤ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች በነጻነት የመሰላቸውን እየተናገሩ በአንድ አዳራሽ የተሰበሰቡበት ነው። ይህ ጉባኤውን ታሪካዊ ያደርገዋል።

ጉባኤውን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚያሰጠው ግን፣ ኢትዮጵያውያን ያለ ማንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ገብነት ቀጣይ የሃገራቸውን እድል ለመወሰን የታደሙበት መሆኑ ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ የታደሙት ኢትዮጵያውያን ከመለያየት ይልቅ አብረው በኖሩባቸው ዓመታት በክፉም ይሁን በደግ የተጋሩት ታሪክ ላይ ተመስርተው፣ በብሄራዊ ማነነታቸው ያላቸውን ነጻነት እንደጠበቁ አንድ የጋራ ሃገር መስርተው ለመኖር ወሰኑ። የአሁኗ ኢትዮጵያ የግንቦት 20 ድል ወጤት በሆነው በዚህ ጉባኤ የተደረሰበት ስምምነት ወጤት ነች።

የጉባኤው ታዳሚዎች ከመበታተን ይልቅ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በፍቃደኝነት፣ መከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያላት ሃገር ለማዋቀር ነበር የተስማሙት። በዚሁ ጉባኤ ላይ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የህዝቦች አንድነት ያላትን የተስፋ ሃገር ህገመንግስት የማዘጋጀት ተልዕኮ የተሰጠው ሁሉም የኢትዮጵያ ሃይሎች የተወከሉበት የሽግግር መንግስት መሰረቱ። ይህ የሽግግር መንግስት የመበታተን ጠርዝ ላይ ደርሰው የነበሩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማሰተዳደር መብታቸውን ባከበረ ቻርተር ነበር የሚተዳደረው።

የኢትዮጵያ ብሄሮቸ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተስፋ ሃገራቸውን ለመመስረት ያደራጁት የሽግግር መንግስት በነጻና ዴሞክራሲያዊ የህዝብ ተሳትፎ ህገመንግስት እንዲቀረጽ አደረገ።

ህገመንግስቱ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውክልና በነበረው አካል ተረቀቀ። ረቂቅ ህገመንግስቱ እያንዳንዱ ለአካለ መጠን የደረሰ ዜጋ በተደጋጋሚ በነጻነት ተወያይቶበት እንዲያዳብረው ተደረገ። በመጨረሻም ህዝብ በነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሰየመው የህገመንግስት አጽዳቂ ምክር ቤት ጸደቀ። ይህ ህገመንግስት የአንድነት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ህገመንግስቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ (በሚኖሩበት ወሰን ውስጥ በወኪሎቻቸው እየተዳደሩ፣ በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት እያገኙ፣ ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማሩ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡ፣ ባህላቸውን እያጎለበቱ) በአኩልነት ላይ የተመሰረተ የመሬት ሳይሆን የህዝቦች አንድነት ያላት ሃገር መስርተው ለመኖር የገቡት ቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ይህ በፍቃደኝነት፣ በእኩልነት አብሮ ለመኖር በተገባ ስምምነት የተፈጠረ አንድነት ጠንካራ አንድነት ነው።

አሁን ኢትዮጵያ ጠንካራ አንድነት ያላት ሃገር ነች። እርግጥ አሁንም የጋራ እሴቶችን ከማዳበር ይልቅ ልዩነታችን ላይ ብቻ ያተኮሩ አካሄዶች ይታያሉ። እነዚህ ልዩነት ላይ ያተኮሩ አካሄዶች፣ አንዳችን ለሌላችን ባዳ እንድንሆን በማደረግ አንድነታችን የታሰረበትን ውል እንዳያላሉት መጠንቀቅ ያለብን ይመስለኛል።

በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተው ብዝሃነትን (የአመለካከትና የብሄራዊ ማንነት) ያከበረው ዴሞክራሲያዊ አንድነት በሃገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል። ይህ ሰላም ደግሞ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ለተመዘገበው የሰፊው አርሶ አደር ህይወት ላይ ጉልህ ለውጥ ያመጣው እድገትና ልማት መሰረት ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ያረጋገጠው ሰላም ሃገራዊ የካፒታል ክምችትን በማሳደግ ለመዋቅራዊ ሽግግር መሰረት መጣል ያስቻለ ደረጃ ላይ አድርሶናል። ይህ እድገትና ልማት  ህገመንግስቱ ባረጋገጠው ሳላም የተገኘ ነው።

26ኛው የግንቦት 20 የድል ቀንን መነሻ በማድረግ በወፍ በረር የዳሰስኩት የባለፉ አርባ ዓመት የሃገራችን ጉዞ፣ ድሉ የዘመናት ጭቆና የወለደው የህዝባዊ ትግል ውጤት መሆኑን ያሳየናል።

በአጠቃላይ፤ የግንቦት 20 ድል ኢትዮጵያውያን ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መመስረት ያስቻለውን የኢፌዴሪ ህገመንግስትና ሥርአት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል። የግንቦት 20 ድል ፍሬ በሆነው ህገመንግስት የተገነባው  ዴሞክራሲያዊ አንድነት ደግሞ ሰላምን አረጋግጧል። ይህ ሰላም በመዋቅራዊ ለውጥ ኢኮኖሚውን ወደኢንደስትሪ መር በማሸጋጋር የዜጎችን የተሻለ ህይወት የሚያረጋግጥ ሃገራዊ ካፒታል ማከማቸት የተጀመረበትን እድገትና ልማት ማስመዝገብ አስችሏል። በሃገሪቱ የሰፈነው ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ሰላምና ልማት የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው።