NEWS

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ እስማኤል ቢቂላ የክስ መዝገብ በተከሰሱ 23 ግለሰቦች ላይ ቅጣት አስተላለፈ

By Admin

May 17, 2017

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት በእነ እስማኤል ቢቂላ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ ሀያ ሶስት ግለሰቦች በጅማ አከባቢ እስላማዊ መንግስትን ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል በሚል የሽብር ወንጀል ክስ ከ3 እስከ 15 በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጣቸው።

ተከሳሾቹ  ከ2002 እስከ 2006 ዓ.ም በጅማ የተለያዩ አካባቢዎች ግብር አትክፈሉ ፣ በሸሪዓ ሕግ እንጂ በመንግስት ሕግ መመራት አያስፈልግምና  ተያያዥ ቅስቀሳዎች አድርገዋል የሚሉ ክሶች  ቀርበውባቸዋል ።

ተከሳሾቹ ፊርቃ ነጃህ የሚል የሽብር ቡድን በማቋቋም ፣ አባላት በመመልመል፣ የመለመሏቸውን አባላት ወደ ሞቃድሾ  በመላክ ከአልሸባብ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ማድረጉን ክሳቸው ያስረዳል።

አባላቱ ያቋቋሙትን የሽብር ቡድን በገንዘብ በመደገፍ ከተለያዩ ምንጮች ፋይናንስ ከማድረግ  ባሻገር በጅማና አካባቢው ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ንብረትና ገንዘብ ከመዝረፍ ጀምሮ አንድ ቻይናዊ እስከ መግደል ደርሰዋል ብሏል የክስ መዝገቡ።

በዚሁ መሰረት ክሱን ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት 1ኛ ተከሳሽ የቡድኑ ሰብሳቢ የነበረው እስማኤል ቢቅላ በአስር አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ በክስ መዝገቡ 18ኛ  ተራ ቁጥር ተከሳሽ የሆነው ዙበይር የተሰኘው ተከሳሽ በ15 ዓመት  ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በቡድኑ አጠቃላይ ክስ ተመስርቶባቸው የተፈረደባቸው ተከሳሾች 23 መሆናቸው ተመልክቷል።

ሪፖርተ:- ጥላሁን ካሳ