Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፓርቲዎችን ሚና ተክተው ለመስራት የሚሹ ፕሬሶችም ሆኑ ማኅበራት አያስፈልጉንም!!

0 306

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፓርቲዎችን ሚና ተክተው ለመስራት የሚሹ

ፕሬሶችም ሆኑ ማኅበራት አያስፈልጉንም!!

ዮናስ

በሃገራችን ሕገ መንግሥት የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ እንዲሁም የመደራጀት መብት በግልጽ ተደንግጓል፡፡የመደራጀት መብትን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 31 ላይ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው ይላል፡፡ በማስከተልም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ መሆኑን ደንግጓል፡፡በዚሁ መሰረት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ በመደራጀት የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ከመቻልም በላይ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡በሌላ በኩል በሙያና በጥቅም ማኅበራት፣ እንዲሁም በሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ተደራጅተቶ ዓላማን ማሳካት ይቻላል፡፡ አለማቀፉን የፕሬስ ቀን ምክንያት በማድረግ ሃሳብን በነጻ ከመግለጽ መብት ጋር ተያያዥ የሆኑ ህገ መንግስታዊ መብቶችን ከነአፈጻጸማቸው ማየት የዚህ ተረክ ጉዳይ ነው።

ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን በተከበረ ቁጥር ገና ከዋዜማው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ ተቋማትና አንዳንድ ሚዲያዎች በኩል የሚወጡ አለም አቀፍ ሪፖርቶችና ዘገባዎች በሃገራችን ያለው የጋዜጠኝነት አፈና ያልተቀረፈ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው። ዘንድሮ የሚከበረውን የፕሬስ ቀን አስመልክቶ የወጡ ሪፖርቶችና ዘገባዎችም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው። እነዚህ ሪፖርቶች ወይም ዘገባዎች  ዞን ዘጠኝን (ZONE NINE) መንግስት መክሰሱን፣ የተወሰኑትን ከጥፋተኝነት ነጻ ቢላቸውም የተቀሩትን ግን እስካሁንም በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን ስለክሳቸው በማስረጃነት ያነሳሉ። በ2016 ወደ 20 የሚጠጉ ጋዜጠኞች በተለያዩ መንገድ ከአገር ወጥተው ጠፍተዋል በማለትም ክሳቸውን ያጠናክራሉ።

ተቋማቱ ይህን ቢሉም ከላይ በተመለከተው አግባብ አንዳች ጋዜጠኛ በህገመንግስታዊ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ እስከሰራ ድረስ ሊደርስበት የሚችል ጉዳት ወይም ስጋት እንደሌለ በአስራዎቹ ለሚቆጠሩ አመታት በስራ ላይ ካሉት ፕሬሶቻችን በላይ ዋቢ የለም።(ሪፖርተር ፣ ፎርቹን እና አዲስ አድማስ ልብ ማለት ይቻላል)። ወዲህ ደግሞ ተቋማቱ ተሰደዱ ከሚሏቸው ጋዜጠኞች አብዛኞቹ የስፖርት ጋዜጠኞች ናቸው። ማኅበራቱም ቢሆኑ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲነትን እና የማህበራትን ሚና ደበላልቀው ለመጫወት የሚሹ ስለመሆናቸው ምርጫ 97ን እና ምርጫውን ሲታዘቡ የነበሩ ማህበራትን በማስታወስ መጠየቅ ይቻላል።  

እዚህ ጋር ግን በተለይ ለወጣቶች አርአያነት ያላቸው ተግባራትን ማከናወን የሚችሉ፣ በጥናትና በምርምር የታገዙ ችግር ፈቺ መፍትሔዎችን የሚያመነጩ፣ ወጣቶች በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መሠረታዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡና በርካታ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሲቪክ ማኅበራት የነበሩና ያሉ ስለመሆናቸው መዘንጋት አይገባም። ይልቁንም ሊደገፉ ሲገባ ተሽመድምደው የተቀመጡትን ማስታወስ የሚገባ እና የመንግስትን ሁሉን የመፈረጅ ድክመት የሚያጠይቁ ማህበራት በመሞት ሂደት ላይ መሆናቸውንም ማስታወስ ይገባል፡፡

የሠራተኛ ማኅበራት የዓለም የሠራተኞችን ቀን ሲያከብሩ በምሬትና በሰቆቃ ውስጥ ሆነው የሚታዩ መሆኑ የመንግስትን ድክመት የሚያሳይ ነው፡፡ ከሥራ ቦታ ደኅንነት፣ ጤንነት፣ ክፍያ፣ ጥቅማ ጥቅምና ሌሎች በደሎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ዛሬም በስፋት ይታያሉ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሠሪዎች ድብደባ የሚፈጸምባቸው፣ ያለምንም ክፍያ ከሥራቸው የሚባረሩ፣ ለጤና ጠንቅ በሆነ ቦታ ላይ ተመድበው በሰቆቃ ዕድሜያቸውን የሚገፉ፣ ለአካል ጉዳትና ለሕልፈት የሚዳረጉ ሠራተኞች ጉዳይ ዛሬም መልስ አልተገኘለትም፡፡ በሕጉ መሠረት ተደራጅተው ከአሠሪዎች ጋር መደራደር ያለባቸው ሠራተኞች ማኅበራቸው ሲፈርስ ወይም እንዳይቋቋም ሲከለከል ሊከላከል የሚገባው መንግስት ዝም ካለ በእርግጥም ያሳስባል፡፡  

ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡት ክሶች ግን ውሃ የሚያነሱ አይመስሉም። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 እንዳለ ተወስዶ፣ የሃገራችን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የሆነው መብት በተግባር መከበሩን ከላይ የተመለከቱት የፕሬስ ውጤቶችን ጨምሮ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ከሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለ ምልልሶች በላይ አስረጅ ከየት ይመጣል፡፡ ይህ አንቀጽ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለው አረጋግጧል፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡ የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል ይላል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተለይ የተለያዩ መብቶች ተዘርዝረውለታል፡፡ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ የተገኘም በሕግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም በህግ የሚጠየቁቱ በህገ መንግስቱ ከተደነገገው ገደብ ውጪ ሲሆኑ ብቻ ነው።ይህ ደግሞ ህጋዊነት እንጂ ህገወጥነትን አያመላክትም።ጋዜጠኛ ስለሆንኩኝ እንዳሻኝ ልፈነጭ ይገባኛል ብሎ ሙግት የባሰው ህገወጥነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ከላይ የተመለከቱ መብቶች ይከበሩ የሚል ሚዲያ እና ጋዜጠኛ ህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩ ክልከላዎችንም ሊያከብር ይገባል። ሃገራችን ከዚህም በላይ የሆኑ ሌሎች ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የምታከብርበት ምክንያቶች አሏት። ሃገራችን የሰብዓዊ መብት ሁለንተናዊ ድንጋጌዎች፣ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መርሆዎች ድንጋጌ፣ የዊንድሆክ ድንጋጌ፣ የአፍሪካ ብሮድካስቲንግ ቻርተርና የአፍሪካና የኔፓድ ኮሚሽን የተጠቃለሉ መርሆዎች ፈራሚ መሆኗ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ከህግ ውጭ ሆና በተገኘች ጊዜ ከህዝቧና ከህገ መንግስቷም ተጨማሪ እነዚህ አካላት ጠያቂዎች መሆናቸው በሚታወቅበት አግባብ የተሻለ ኑሮ ፍለጋና በኪራይ ሰብሳቢነት ስብእና ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች በህግ የተከለከሉ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ነክረው ቪዛ ከሸመቱ ኋላ መዘባረቃቸው ፤ ተሟጋች ነን የምንለው ደግሞ እነርሱ በቀደዱት ቀዳዳ የምንጮህ ከሆነ የምንሞላው የእነርሱን ከርስ እንጂ በሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ጠብ የምናደርገው ነገር አይኖርም።

የአገሪቱ ፕሬስ 120 ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ በተሟላ ሁኔታ የግሉ ፕሬስ በዚህች አገር ውስጥ በይፋ መሥራት የጀመረው ከዛሬ 25 አመታት በኋላ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ አንድ ነገር ሆኖ ከክሶቹ አስቀድሞ የግል ፕሬሱ ለሙያው አዲስ ከመሆኑም በላይ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባርና የልምድ ጉድለቶች ያሉበት መሆኑንም መካድ ፋይዳ የለውም፡፡ በሃገራችን ገበያው በሚፈልገው መጠን ጋዜጠኞችን የሚያፈሩ የትምህርት ተቋማት የሌሉ መሆኑስ ስለምን ይደበቃል።   ብዙዎቹ የግል ፕሬሶች የሙያ ሥነ ምግባር መመሪያም ሆነ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሌላቸው እንደሆነም ፍቃድ ሰጪው አካል በተደጋጋሚ መናገሩ ስለምን ይዘነጋል፡፡    ይህ በሌለበት ሜዳ ደግሞ ገለልተኝነት እየጠፋ ጽንፈኝነት መንገሱ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ  ወደ ፖለቲካ አቀንቃኝነት (Activism) ውስጥ የተገባ መሆኑን እያወቅን ፤ እነዚህን ሃይሎች በጋዜጠኝነት ካባ ማንገስና ስደተኛ ሆኑ ብሎ ማሞካሸት ስለሃገራችን ፕሬስ እድገት አንዳች አስተዎፅኦ አይኖረውም፡፡

ሚዲያ ለህብረተሰቡና ለሃገር የሚያስፈልገው አንዳች ቁምነገር / Purpose / ስላለው ነው፡፡ ነገር ግን ፕሬስ የሃላፊነት / Purpose /  ጉዳይ እንደሆነ ከቁብ የገባ አይመስልም፡፡ በእኛ ሀገር ጋዜጠኝነት አላፊ አግዳሚውን ጨምሮ በሥርዓቱ ላይ የተናደደው ሁሉ ንዴቱን ለማወራረድ የተሠማራበት ዘርፍ እንደሆነ በግልጽ ታይቷል፡፡  

በህክምናና በህግ እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች ተጠያቂነት እንዳለ የሚያውቁትና ይህንኑም የሚጽፉት በሚዲያም ተጠያቂነት እንዳለ ታሳቢ በማድረግ ስለፕሬስ ነፃነት መከራከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትኛውንም ርዕዮተ አለም አንድ ጋዜጠኛ ቢከተል መብቱ ነው። ግን ደግሞ እንደጋዜጠኛ ለመፃፍ የሚያስችል ሙያዊ ህግጋት እንዳለም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ይህም ስለሆነ እና የተደራጀ የንግድ ሚዲያ(commercial media) በብዛት በሌለባት ሃገራችን ፕሬሱ በፖለቲከኞች እንዲጠለፍ ምክንያት ሆኗል።በሠላማዊ ሠልፍ ሱስ የተጠመዱ ተቃዋሚ ሃይሎች ቅደሚያ መፈክሮቻቸው ነፃ ፕሬስ የሚል የሆነበት ምክንያት ስለዚህ ነው፡፡ የተለየ አስተሣሠብ መስተናገድ የለበትም በሚሉ የራሳቸው ሃይሎች የተያዘ መሆኑ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ወደመፍትሄው ልንመጣ ከሆነ መጀመሪያ ሽብርተኝነትን ለማበረታታት ጐሳን ከጎሳ ለማጋጨት የሃይማኖት እኩልነትን ለመናድ ተጠቀመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም ታማኝ አንባቢዎች ያላቸው እንደሆነም የአስተሣሰብ አንድነት ባላቸው የሚበዙ ፕሬሶች ማረጋገጥ ስለቻልን፡፡ ታማኝ አንባቢና የአስተሳሰብ ብዝሃነት የሌላቸው መሆኑንም ከህትመት ኮፒ ብዛታቸው መረዳት ይቻለናል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠር ብር እየተሸጡ የሚገኙበት የመጽሃፍ ገበያ እንዳለ እያየን ፕሬሶቹ በ2ሺህ እና 5ሸህ ኮፒ የመታተማቸው ጉዳይ ተደራሽነታቸውን የሚያጋልጥ ነው፡፡

እነዚህ ደግሞ በአፋዊ ስለፕሬስ ነፃነት ይጮኸሉ እንጂ በአስተሳሰብ የተሸነፉ የነፃነት ጣላቶች ናቸው፡፡ አክቲቪስት  ሆነው አቋም ይዘው ስለሚዛናዊነት በማይጨነቁ ፀሐፊዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ  ሳይወድ በግድ እንዲቀበለው የተደረገ አስተሣሠብ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ  እየተፈሩና እየተደመጡ  ያሉት  የነፃነት ጠላቶችና የነፃነት አፋኞች፤  ወይም በነጻፕሬስ ስም የፖለቲከኞቹ ሠለባ የሆኑት ፕሬሶች እንደሆኑም እናውቃለን፡፡

የፕሬስ ነፃነትም ሆነ ሚዲያ የሚያስፈልገው የፕሬሱ ምንጭ የሆነው ህብረተሰብ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታ ተሣታፊ እንዲሆኑ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የሙያተኛው ቦታ በጩኸትና በግርግር ተይዟል፡፡ ፖለቲከኞች ጋዜጠኛ ሆነው የፖለቲካ አላማቸውን እያራመዱበትና ሌሎች እንዳይደመጡ እያደረጉ ነው፡፡  

ስለሆነም አሁን የሚያስፈልገን ስለሃገራችን ፕሬስና ጋዜጠኞች ታሰሩ ቆሰሉ (ሊያውም ያለአንዳች ምክንያታዊነትና ህጋዊነት)ብሎ የሚያወራልን አይደለም። የሚያስፈልገን የሃገራችን ሚዲያ ደካማ፣ ጽንፈኛና ስሜታዊ፣ ከሙያውም ከሥነ ምግባሩም የሌለበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ደካማ፣ በሙያውም እዚህ ግባ የማይባል፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትና ሙያተኞችን መሳብ የማይችል መሆኑን አምኖ በማሳመን ከዚህ የሚወጣበትን መላ የሚመታልን ነው፡፡ የሚያስፈልገን የፖለቲካን እና የፓርቲን ድንበር ለይተው የሚያውቁ ሚዲያዎችና ማህበራት የሚፈጠሩበትን መላ የሚዘይድልን አካል ነው ። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊት ሃገር ልንገነባ ከሆነ ያለጠንካራ የግል ፕሬስ እና የሲቪክ ማህበራት ስለማንችል ፡፡  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy