Artcles

ይድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

By Admin

May 23, 2017

ይድረስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰለሞን ሽፈራው ክቡራት እና ክቡራን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሆይ፤ እኔ ይህቺን ማስታወሻ ለተከበረው ምክር ቤት የምፅፈው ግለሰብ፤ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግሉ ምክንያት የደምና አጥንት መስዋዕትነትን ከከፈሉት የትግራይ ወጣቶች አንዱ ነኝ፡፡ ወደ መሀል አገር የገባሁትም ልክ የዛሬ 26 ዓመት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ለመላው ኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተበሰረውን ታሪካዊ ድል እውን ካደረገው የህወሐት /ኢህአዴግ ሰራዊት አባላት አንዱ ሆኜ እንደነበር በዚህ አጋጣሚ አስታውሼ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡ እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ የማልፈውም፤ ዘንድሮ ለ26ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የግንቦት 20 ድል ዓመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ ለተከበረው ምክር ቤት ለማድረስ አባላት ለማስተላለፍ የምፈልገውን መልዕክት ወደ ማሰፍርበት መሰረተ ሃሳብ ይሆናል፡፡ ስለዚህም፤ እኔ እንደ አንድ የግንቦት 20ኛው ታሪካዊ ድል ድምር ውጤት የሆነችውን ፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን ለመመስረት ሲባል በተካሔደው፤ እጅጉን ደም ያፋሰሰና ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት መክፈልን የጠየቀ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ታሪክ ውስጥ አልፎ እንደመጣ የዚች አገር ዜጋ ዛሬ ላይ ሆኜ ለተከበረው ምክር ቤት አባላት መለገስ ይኖርብኛል የምለውን የግል አስተያየት እነሆ በሚከተለው መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ክቡራት እና ክቡራን የፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት ሆይ፤ መቸስ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት ለመጎናፀፍ ሲሉ ባካሔዱት የዘመናት ትግል ስለከፈሉት ለማመን የሚያዳግት ዋጋ ለእናንተ ማስታወስ ለቀባሪ እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም ደግሞ፤ አሁን ላይ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ሳያሻቅብ እንዳልቀረ ከሚገመተው የሀገራችን ህዝቦች አጠቃላይ ቁጥር አኳያ በሚታሰብ የምርጫ ስርዓት ሂደት ውስጥ እያለፋችሁ ወደዚህ እጅጉን በላቀ የኃላፊነት ስሜት መስራትን ወደ ሚጠይቀው የምክር ቤት አባልነት የመጣችሁበትን አግባብ እገነዘባለሁና ነው፡፡ በግልፅ አማርኛ ለመናገር፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እናንተን እንድትወክሏቸው እየመረጡ ወደዚህ የተከበረው ምክር ቤት አባልነት የላኳችሁ፤ እጅግ በጣም የከበደ ታሪካዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚያስችል ፖለቲካዊ ስብዕና ወይም ብቃት አላቸው ብለው ስላመኑ እንጂ፤ እንዲያው የየአካባቢያቸው ተወላጆች ስለሆናችሁ ብቻ አይደለም ለማለት ነው የፈለግኩት፡፡ ስለዚህም እንደኔ መረዳት ከሆነ፤ በተለይም የሕግ አውጭው አካል አባላትን በአዲሲቷ ፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ስርዓተ መንግስት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ ትርጉም ያለው አውንታዊ ተፅእኖ ለመፍጠር የሚያስችላችሁን የመሪ ተዋናይነት ሚና እንድትጫወቱ የሚያደርግ ዕድል በመረጣችሁ ህዝብ ተሰጥቷችሁዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እናም ከዚሁ ልባዊ እምነቴ በሚመነጭ ትህትና፤ የተከበረውን የፌዴራሉ መንግስት አምስተኛ የስራ ዘመን ፓርላማ ልጠይቅ የምፈልገውም፤ ኧረ ለመሆኑ እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች በምርጫ ካርዳችን አማካኝነት የሰጠናችሁን ልዑዋላዊ ስልጣን በአግባቡ እየተጠቀማችሁበት ነውን? የሚለውን ይሆናል፡፡ እኔ እንደ አንድ ለፌዴራል ስርዓቱ ጥንካሬ ከመታገል ቦዝኖ የማያውቅ የኢህአዴግ ነባር ታጋይ ይህን መሰል ጥያቄ ለተከበረው ምክር ቤት አባላት አቀርብላችሁ ዘንድ የተገደድኩትም ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ በፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚዋቀሩት የቁጥጥርና የክትትል ቋሚ ኮሚቴዎች፤ በተለይም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችንና ሌሎች የልማት ተቋማትን ዓመታዊ ዕቅድ የማስፈፀም ስራ ክንውን ለማረጋገጥ ያለመ የመስክ ጉብኝት የሚያደርጉበት አግባብ የሀገራችንን ሲቪል ሰርቫንት እጅግ በተወሳሰበ መልኩ የሚገለፅ ቢሮክራሲያዊ ደባ የተተበተበ መሰረታዊ ችግር እንብዛም ያላገናዘበና እንዲያውም “ለግብር ይውጣ” ያህል ብቻ የሚደረግ ስለመሆኑ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ታዝቤያለሁና ነው፡፡ ከዚሁ የሕግ አውጭው አካል የክትትልና የቁጥጥር ሰንሰለት እጅጉን የላላ ሆኖ መገኘት የተነሳም፤ ለሾማቸው መንግስት ቀርቶ ለገዛ ራሳቸው ህሊናም የመታመን ፍላጎት የማይታባቸው ብልጣ – ብልጥ አስፈፃሚ አካላት፤ የግላቸውን ኑሮ ይበልጥ ለማመቻቸት ሲሉ በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ላይ ሲጠመዱና ተገልጋዩን ህብረተሰብ በአስተዳደራዊ በደል ሲያማርሩት ማየት ሸሽተን እንኳን የማናመልጠው የዕድሜ ልክ ዕጣ ፋንታችን ይመስለን ጀምሯል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትርጉም ያለው የተጠያቂነት መንፈስን አሊያም ደግሞ አሰራርን ልናሰፍን ካለመቻላችን እንደሚመነጭ የሚነገርለት የአስፈፃሚ አካላት ስነ-ምግባራዊ ጉድለት የሚስተዋለው በፌዴራሉ መንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ብቻ እንዳልሆነና ይልቁንም በመላው የሀገራችን ክፍል የሚገኙ የክልል መስተዳደሮችን ህዝብ ጭምር ከላይ እስከ ታች ያስመረረ አሳሳቢ ጉዳይ ስለመሆኑ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ አዘውትሮ ለሚያሰማው ከመልካም አስተዳደር እጦት የሚመነጭ ቅሬታ፤ የተሻለ ማረጋገጫ ሊሆነን ይችላል የምለውም ደግሞ፤ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሀገር አቀፋዊ ግኝት ላይ የተመለከተው የአጠቃላይ ችግሮቻችን ተጨባጭ ገፅታ ይመስለኛል፡፡ የተከበራችሁ የምክር ቤቱ አባላት ሆይ፤ እንግዲህ ለአብነት ያህል ከዚህ በላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው፤ ስለ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ደፍሮ መናገር አያዳግትም ባይ ነኝ፡፡ እርሱም ደግሞ፤ እናንተን መርጠው ወደዚህ ከፍተኛ ታሪካዊ ሃላፊነትን መወጣት ወደሚጠይቅ ልዑዋላዊ የስልጣን ዕርከን እንድትመጡ ያደረጓችሁን ኢህአዴግና የአጋሮቹ ደጋፊዎች ጨምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝቦች፤ ሕገ መንግስቱ ያጎናፀፋቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአንዳንድ ምግባረ ብልሹ አስፈፃሚ አካላት ምክንያት ሳይጠቀሙባቸው እንደሚቀሩ ግንዛቤ የመውሰድ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ይህን ሊስተባበል በማይችል መልኩ እየተፈታተነን ያለ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፋዊ ችግር ደረጃ በደረጃ እየቀረፍን ቀጥለን፤ ህብረተሰቡ ክፉኛ ሲማረር የሚደመጥበትን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ ወደ ሚያስችለን አመርቂ ውጤት የምንደርሰው፤ ከፌዴራሉ መንግስት ፓርላማ ጨምሮ፤ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ባለው የክልላዊ መስተዳድሮቻችን መዋቅር ውስጥ የሚገኙት የህዝብ ምክር ቤቶች በሙሉ፤ የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ ስንችል ብቻ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህን ስንልም ደግሞ፤ በተለይ የፌዴራሉ ፓርላማ አባላት፤ ከመላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወክለው በመጡ አባላት የተመሰረተና ከፍተኛው የሕግ አውጭ አካላት ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን፤ ለሌሎቹ ምክር ቤቶቻችን አርአያ የሚያደርገውን ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ቁመና ይዞ መገኘት ይጠበቅበታል ማለታችን ነው፡፡ አለበለዚያ ግን፤ አሁን ላይ የስርዓቱ አሳሳቢ አደጋዎች ተደርገው የሚወሰዱትን ከኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ጋር በአንድ ወይም ደግሞ በሌላ መልኩ የሚገለፅ ቁርኝት ያላቸው ችግሮቻችንን ትርጉም ባለው ስፋትና ጥልቀት ቀርፈን የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ወደፊት ስለማስቀጠል አስፈላጊነት መናገር ብቻውን የተከበረው ምክር ቤት ህዝብ የጣለበትን ታሪካዊ ሃላፊነት እየተወጣ ነው ብለን እንድናምን አያደርገንም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ህብረተሰባችንን ከስርዓቱ ጋር እንዲቃቃርና የስር ነቀል ለውጥ ሂደቱን አስፈላጊነት ቸል እንዲለው እያደረጉ ያሉት ሀገር አቀፋዊ የመልካም አስተዳደር እጦትና መሰል ችግሮች ሁሉ የሚመነጩት ከተጠያቂነት መጥፋት ነው ተብሎ ይታመናልና ነው፡፡ ስለዚህ እንደኔ እንደኔ፤ ለአብዛኛዎቹ የዚች አገር አሳሳቢ ችግሮች ዋነኛ መንስኤ ተደርጎ የሚወሰደውን ትርጉም ያለው የተጠያቂነት አሰራርን ማስፈን አለመቻል የመሆኑን ያህል፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን ክፍተት የሚደፍን መፍትሔ የሚገኘውም በየደረጃው ባሉ የህዝብ ምክር ቤቶች እጅ ላይ ነው የሚለው ነጥብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የተከበረውን የፌዴራሉ መንግስት ፓርላማ ጨምሮ፤ ሌሎችም በመላው ሀገሪቱ ያሉ የህዝብ ውክልና የተሰጣቸው ምክር ቤቶች ስልጣናቸውን ተጠቅመው አስፈፃሚ የመንግስት አካላትን በአግባቡ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት ደካማ ባይሆን ኖሮ፤ ተጠያቂነት አይጠፋም ነበር ማለቴ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ተጠያቂነት በጠፋ ቁጥር፤ ህዝብን እንዲያገለግልበት ሲባል የሰጠውን የመንግስት ስልጣን ለርካሽ የግል ጥቅም ማጋበሻነት ሊያውለው የሚፈልግ ምግባረ ብልሹ ተሿሚ መበራከቱ እንደማይቀር ደግሞ ድፍን ዓለም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ዓለም አቀፋዊ ጥሬ ሀቅ መነሻ በማድረግ ጉዳዩን ወደኛ አገሩ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እውነታ ስናመጣውም፤ የተጠያቂነትን አስፈላጊነት ምናልባትም በብዙ እጥፍ እንዲጨምር የሚያደርጉ ነባራዊ ምክንያቶች እንዳሉ ለመረዳት የተለየ ዕውቀት የሚጠይቅ አይሆንም፡፡ ስለዚህም፤ የተከበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ አስፈፃሚ የመንግስት አካላትን የሚቆጣጠርበት አግባብ ከእስከዛሬው በተለየ መልኩ መቃኘት እንደሚኖርበትና እያንዳንዱ ሰው አጥፍቶ ሲገኝ ጉዳዩ እየተጣራ በፈፀመው ስህተት ልክ የሚጠየቅበትን ትርጉም ያለው ተፅእኖ ማሳደር እንደሚጠበቅበት ይሰማኛል፡፡ ለማንኛውም ግን ይህ በአምስተኛው የስራ ዘመን የተመሰረተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከእስከዛሬው ለየት የሚልበት ምክንያት ከኢህአዴግና ከአጋር ፓርቲዎች በስተቀር የተቃዋሚዎች አባላትን አለማካተቱ ነው አይደል? እንግዲያውስ እኔም “ኢህአዴግነት መስመር ነው” በሚል ርዕስ የፃፍኩትን ግጥም ለክቡራት እም ክቡራን የፌዴራሉ መንግስት ፓርላማ አባላት ጋብዣለሁ፡፡ የጥቂት ገዥ መደቦችን፣ የማያላውስ አፈና በትግል የደረመሰ፣ ህዝባዊ የድል ጎዳና መስመር ነው ኢህአዴግነት፣ ለሩቅ ግብ የተተለመ እየሞቱ የሚያኖሩት፣ በመስዋዕትነት የቆመ ፊቱንም ኢህአዴግነት፣ ከብረት በጠነከረ የፀረ ጭቆና መንፈስ፣ ህዝቦችን ያስተሳሰረ ሥርዓት ያፈራረሰ፣ የትግል መስመር ነበረ…! የብሔር-የብሔረሰብ፣ ህዝቦችን እያታገለ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ፣ ፅኑ መሰረት የጣለ እውነት ነው ኢህአዴግነት፣ በተግባር የደለደለ፡፡ ፍትህ ርትዕ ዕኩልነት፣ ዴሞክራሲን ሊያሰፍኑ የአዲሲቷን ኢትዮጵያን፣ ብሩህ ጉዞ የወጠኑ የተለሙትን የሩቅ ግብ፣ ዳር ለማድረስ ሲታመኑ ኢህአዴግነት መርህ ነው፣ ለአንድ ዓላማ መሰለፍ የጥቂት ገዢ መደቦችን፤ ጭቆና ታግሎ ማሸነፍ፡፡ በጋራ ጠላት ላይ ዘምተው፤ ከገዛ ራስ ጥረት ማትረፍ፡፡ የተስፋይቱን ምድር ህዝቦች፤ ፍትህ ርትዕ ማጎናፀፍ፡፡ ለእናት ሀገር ህዳሴ፤ ህያው ታሪክ ሰርቶ ማለፍ፡፡ ማለት ነው ኢህአዴግነት፤ ስርወ ትርጉሙ ሲብራራ ኦሮሞውን ከትግራይ ልጅ፤ ሲዳማውን ከአማራ ጎጃሜውን ከሀዲያው፤ ጉራጌውን ከዋግ ኽምራ የደቡቡን ሐመር ሱርማ ከሰሜንኛው ኩናማ የኦሞ ወንዙን ኤርቦሬ ከራስ ዳሽኑ ጎንደሬ የከረዩን ኦሮሞ ከጌዲኦና ከጋሞ ከኮንሶው ጋር አጣጥሞ… የበጌ ምድሩን ቅማንትም፤ ከኦጋዴኑ ሱማሌ የጉጂውን አባገዳ፤ ከአፋሩ ባለጊሌ የሐረሪውን ማንነት፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዙ በርታ ስልጤውን ከትግረ-ወርጂ፤ አርጎባውን ከወላይታ የመሃል አገሩን ባህል፤ ከጋምቤላው አኙዋክ-ኙዌር ገጠሬውን ከከተሜው፤ ብሔረሰቡን ከብሔር ቆለኛውን ከደገኛው፤ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ አርሶ በሌውን ገበሬም፤ ከአርብቶ አደር ወንድሙ የተስፋቱን ምድር ህዝቦች፤ አቀራርበው እያስማሙ ለእናት ሃገር ህዳሴ፤ በፍቅር እንዲታደሙ ማድረግ ነው ኢህአዴግነት፤ ሲብራራ የወል ትርጉሙ፡፡ ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት፤ በጠየቀ ውጣ ውረድ አርቆ አሳቢ ታጋዮች፤ ለቀየሱት የድል መንገድ በክቡር ደም ለተፃፈው፤ የትግሉ ቃልኪዳን ሰነድ… ታምኖ መገኘት የሚሻ፤ የሰማእታት አደራ ማለት ነው ኢህአዴግነት፤ ስርወ – ትርጉሙ ሲብራራ፡፡ ግንባር ቀደም ታጋዮችን ፤ውድ ዋጋ እያስከፈለ የአዲሲቷ ኢትዮጵያን፣ ፅኑ መሰረት የጣለ መስመር ነው ኢህአዴግነት፤ በመርህ የደለደለ! ሥር ከሰደደ ድህነት፤ ከዘመናት ጉስቁልና በሚታደግ ፈጣን ልማት፣ የጋራ ዕድገት ብልፅግና ለመቀዳጀት ያለምነው፤ የብሩህ ተስፋ ጎዳና ለዘላቂ ዕጣ ፋንታችን፣ መቃናት የተተለመ እየሞቱ የሚያኖሩት፤ በመስዋዕትነት የቆመ…!! ሕዝባዊ የትግል መስመር፤ ነው እንጂ ኢህአዴግነት ጥቂቶች ሥልጣን ጨብጠው፤ ለቡድናዊ ፍላጎት ለርካሽ የግል ጥቅም፤ እንዲፈልጡ እንዲቆርጡበት ለአድር ባዮች መፈንጫ፣ የሚተው አይደለም ዘበት!!! መዓሰላማት!!