Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲያችንን እንዴት እናጎልብት?

0 937

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲያችንን እንዴት እናጎልብት?
ዳዊት ምትኩ
ባለፉት ስርዓቶች በሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ባለመገንባቱ ምክንያት ሕዝቦች በገዛ ሀገራችው በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተረገጡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተገፎ የስቃይ ቀንበርን ሲሸከሙ ኖረዋል። ከጭቆና የአገዛዝ ስርዓቶች ሳይላቀቁ በመቅረታቸው ሳቢያም፤ ስለ ሰላም፣ ስለ ልማት እና ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ እንዳይሰሙ፣ እንዳያዩና እንዳይናገሩ ተደርገው ለሰቆቃ ተዳርገዋል።
ታዲያ ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት ከየብሔሩ የተወጣጡ ውድ የሕዝብ ልጆች ህይወታቸውን፣ አካላቸውንና ንብረታቸውን ቤዛ አድርገዋል። በዚህም የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት፣ የኃይማኖትና የእምነት ነፃነት እንዲሁም የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ብሎም ሌሎች ወሳኝ የሆኑ የቡድንና የግል መብቶች እንዲረጋገጡ ማድረግ ችለዋል።
እናም ሕዝቦቿ መብታቸውን ለዘመናት ተረግጠው የኖሩባት፣ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ያልታየበት፣ ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ ያልታሰበባት ሀገር፤ ዛሬ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘርግታ ይህን የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ጉዞ ማየቷ ማንኛውንም ዜጋ እንደሚያስደስተው ጥርጥር የለውም።
ታዲያ ይህን የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ በተለይም ዴሞክራሲን ለማጎልበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሚዲያና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። እንደሚታወቀው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው ምርጫ ነው፡፡ የምርጫ ጠቀሜታም ሕዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ፣ በተጨባጭ በምረጡኝ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ፖርቲዎች ያከናወኑትን ወይም የሚያከናውኑትን ተግባር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የእገሌ ፖርቲ በቀጣይ ለውጥ ያመጣልናል ብለው ያመኑበት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያላንዳች ተጽዕኖ ካርዳቸውን በመስጠት ተመራጩን ፓርቲ ለስልጣን ማብቃት ነው፡፡
ይህም በህገ-መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በሕዝብ ድምፅ እንጂ በሌላ መንገድ የሚገኝ እንዳልሆነ ያስረዳናል፡፡ የፖለቲካ ፖርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ይህን ዕውነታ ተረድተው የዴሞክራሲን ምንነት በውል ተረድተው በምርጫ በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የነበራቸው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ግና እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ዋነኛ ጉዳይ፤ የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ 26 ዓመት ብቻ የስቆጠረ ለጋ በመሆኑ፣ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ ሂደቱ ስር እንዲሰድና እንከን አልባ ርብርብ ተደርጓል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም መሰረታዊ የዴሞክራሰ ተግባራትን በማከናወንና ዴሞክራሲው እንዲጎለብት ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል፡፡
እንደሚታወቀው ባለፋት ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስርዓትን በሂደት እየገነባን መጥተን፣ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረግነው ርብርብ አንፀባራቂ ሊባል የሚችል ውጤት አግኝተናል፡፡ ሆኖም ልዩነታችን አንድነታችን ሆኖ ካልቀጠለ፤ በመነቋቆርና በመነካከስ ከቀጠልን እንደዚህ ቀደሙ ለዘመናት ወደ መጣንበት የድህነት አረንቋላ መዘፈቃችን አይቀርም፡፡ እናም ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ወሳኝ የህልውና ጉዳይ የሚሆነው ለዚሁ ነው፡፡
እርግጥ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ያለ አንዳች እንቅፋት ሳይሸራረፍ ሲቀጥል ነው፡፡ እናም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡ መንግስት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡
የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል። ተቃዋሚዎቹ ግን ይህን የተዘጋ ዶሴ ከ25 ዓመት በኋላ አዋራውን አራግፈው ሊጠቀሙበት የፈለጉ ይመስላል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ግን ይህን ዶሴ የሚያስተናግድበት ቦታ ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ምናልባትም ገዥው ፓርቲና መንግስት ‘ከስልጣናችን ቆርሰን እንስጥ’ ቢሉ እንኳን ስርዓቱ ይህን እንዲያደርጉ የሚፈቅድላቸው ስላልሆነ ነው።
እንደሚታወቀው በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ አንድ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባር የህዝብን ውክልና መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ለማስፈፀም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን ነገር በህዝቡ ላይ ለመጫን አይደለም። ምናልባትም የራሱን ፍላጎት በህዝቡ ላይ ለመጫን ካሰበ፣ ህዝቡ በፓርላማ አማካኝነት የሰጠውን የመተማመኛ ድምፅ ሊነጥቀው ይችላል። እናም ከዴሞክራሲ አኳያ የገዥ ፓርቲ ማናቸውም እንቅስቃሴ ከውክልና ጋር የተያያዘ ብቻ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።
ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ህዝብ ከሰጠው ውክልና ውጭ ሆኖ ስልጣንን ለሌላ ፓርቲ ሊያጋራ አይችልም። መብትም የለውም። ህዝቡ በ2007 ምርጫ ወቅት የሰጠውን ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ውክልና ችግር ስለገጠመው ብቻ ሸርፎ ለሌላ ፓርቲ የሚሰጥበት ምንም ዓይነት ህጋዊ አመክንዩ ሊኖር አይችልም።
በእኔ እምነት ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ከላይ እንደጠቀስኩት ዴሞክራሲውን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ፣ ስልጣንን ከመጋራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ሊኖረውም አይገባም እላለሁ። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ልክ እንዳለፉት ጊዜያት መንግስታዊ ስልጣንን ህገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ በውጭ ኃይሎች ግፊት ለመያዝ ከመሻት ከመነጨ በሚመስል ሁኔታ፣ ዛሬም መንግስት ‘ዴሞክራሲውን ለማስፋት ቆርጨ ተነስቻለሁ’ ሲል ጉዳዩን የመድብለ ፓርቲውን ስርዓት ከማጎልበት አኳያ ከማየት ይልቅ፣ ከስልጣን መጋራት ጋር ሊያያይዙት ይሞክራሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አስተሳሰባቸው የተሳሳተ ብቻ አይደለም—ህገ መንግስቱን ካለመገንዘብ ጭምር የመጣ እንጂ። የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ አንቀፅ 8፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውንና ሉዓላዊነታቸው የሚገለፀውም በህገ-መንግስቱ መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካኝነት እንደሚሆን ደንግጓል። ይህ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያሳየው ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን የሚያዘው የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነው ህዝብ ይሁንታ ብቻ መሆኑን ነው። ህዝቡ ሲፈልግ ይሾማል፤ ሳይፈልግ ደግሞ ይሽራል። የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማጎልበት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሚዲያና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy