Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ስንል

0 415

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ስንል
ሰለሞን ሽፈራው
ኢህአዴግ እንደ አንድ ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ ከትናንት እስከ ዛሬ የሚታወቅባቸው መሰረታዊ የራሱ መርሆዎች አሉት ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት ጥረት ማድረግ በኢትዮጵያ ሁኔታ ምርጫ ሳይሆን፤ የህልውና ጉዳይ ነው›› ሲሉ የኢፌዴሪ መንግስት ከፍተኛ የአመራር አካላት አዘውትረው የሚናገሩትን ከግንባሩ መሰረታዊ አቋሞች መካከል አንዱ አርገን ብንወስደው ተገቢ ይመስለኛል፡፡
በተለይም ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው›› የሚለውን የኢህአዴግ ድርጅታዊ አቋም በምክንያታዊ ትንተና አስደግፈው ለማስረዳት ከመጣር ቦዝነው እንደማያውቁ ማስታወስ አይከብድም፡፡ እናም እንደርሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት አለመገንባት ጉዳይ፤ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሀገራዊ ህልውና ጥያቄ የሚሆነው ፤በተለይም ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትን የጋራ ችግሮቻችንን ግነምት ውስጥ ማስገባት ስለሚጠበቅብን ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይህን ስንልም ደግሞ፤ ከሰማንያ በላይ የየራሳቸው ማንነት መገለጫ የሆነ ቋንቋ፤ ባህል፤ እንዲሁም መንፈሳዊና ስነልቦናዊ ዕሴት ባላቸው ብሔሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል ጤናማ የእርስ በርስ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠርም ሆነ ለማዳበር የሚቻለው፤ በእኩልነት ዓይን የማየትን አስፈላጊነት አምኖ የሚቀበል ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ መኖር እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይህን ቁልፍ ነጥብ ጨምሮ፤ ሌሎች ተያያዥ ቅድመ ሁኔታዎችን ለሟሟላት ሲባል የዴሞክራሲን ፅንሰ ሀሳብ ማጎልበት ይጠይቃል ተብሎ እንደሚታመን ነው አቶ መለስ የሚያስረዱት፡፡ ለማንኛውም ግን፤ ‹‹ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት አስፈላጊነት በኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ውስጥ የህልውና ጉዳይ እንጂ ምርጫ አይደለም›› ሲል፤ በተለይም ብዝሃነትን በአግባቡ ከማስተናገድ ጋር እያገናዘበ ስለሚያየው ነው ቢባል የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥም ደግሞ፤ ኢትዮጵያ እንደሀገር የምትገለፅበትን ህብረ ብሔራዊ ተጨባጭ እውነታ ከፌደራሊዝም ቅርፀ መንግስት ውጭ ማሰብ እንደሚያዳግት ሁሉ፤ ዴሞክራሲያዊ የዕርስ በርስ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ጤናማ ሀገራዊ አንድነትን የመፍጠርና የማዳበር ጉዳይም የህልውና ጥያቄ ነው ቢባል ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ በግልፅ አነጋገር፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያን ህዝቦች ‹‹ዴሞክራሲ›› የተሰኘውን የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ፅንሰ ሃሳብ መሰረት ያደረገ የመንግስት አስተዳደር ዘይቤ የሚያስፈልገን፤ የጋራ ህልውናችንን የማስቀጠል አለማስቀተል ጉዳይ የሚሆንበት አግባብ ስላለ ነው እንጂ፤ ምዕራባውያኑ ሀገራት ስለሚከተሉትና ስለሚመርጡት አይደለም ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡
ይህን መሰረታዊ ነጥብ በተሻለ መልኩ ግልፅ ማድረግ ጠቃሚ ስለሚሆን፤ የመጣጥፌ ዋነኛ ትኩረት ከሆነው ጉዳይ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምክንያት ብዙ ጊዜ ሲነሳ የሚደመጥን የፖለቲካዊ ታሪካችን ዳራ ማስታወስ የሚኖርብኝ ይመስለኛል፡፡ እንግዲያውስ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለምትመራበት የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦቿን ብዝሀነት በአግባቡ ለማስተናገድ ሲባል ተግባራዊ የተደረገ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት መረቀቅና መፅደቅ መነሻ ምክንያት ተደርጎ ወደሚወሰደው፤ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ፤ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ወደተስተዋለ ‹‹የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ›› በመባል የሚታወቅ ፐለቲካዊ ክስተት ተመልሰን አንድ ጠቃሚ ነጥብ እንመለከታለን፡፡
ስለሆነም፤ ከዚያን ዘመኖቹ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ ናፋቂ ወጣት ፖለቲከኞች መካከል የሚመደቡት፤የኦሮሞ ብሔር ተወላጁ ኢብሳ ጉቶማና የወሎ አማራ ስለመሆኑ የሚነገርለት ዋለልኝ መኮንን አብረው ስለሚነሱበት የታሪክ አጋጣሚ የሚያወሳን አንድ ነጥብ ለዚህ ጉዳያችን ማጠናከሪያ ላደርገው ወድጃለሁ፡፡ ማለትም፤ ሁለቱ መጣቶች በያኔው የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ (በአሁኑ የአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ) ይማሩ በነበረበት ወቅት የለውጥ ፍለጋ ቃና የሚስተዋልባቸው የስነፅሁፍ ስራዎችን እያዘጋጁ ማቅረብ የተለመደ ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እናም በዚሁ መሰረት፤ ኢብሳ ጉተማ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?›› ሲል አጥብቆ በጠየቀበት ርዕስ የፃፈው የአማርኛ ግጥም፤ ያኔ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ እያዘጋጀ ያካሒደው በነበረየተማሪዎች የግጥም ውድድር ቀርቦ እንዳሸነፈ ይነገራል፡፡ ኦሮሞው ወጣት ተማሪ ኢብሳ ጉተማ በዚያ የግጥም ስራው ላይ፤ ያነሳው መሰረተሃሳብ ‹‹በእርግጥ ስለኢትዮጵያዊነት ትክክለኛ ትርጉም ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ሀገራዊ የጋራ ግንዛቤ አለን? ወይስ ሾላ በድፍኑ ዓይነት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው እያሉ የሚነግሩንን፤ የጥቂት አካባቢዎች ህዝብ ማንነት ብቻ መላውን የዚች ሀገር ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚወክል፤ ባህል፤ቋንቋና ስነልቦና አድርገን መውሰድ ይኖርብናልን?›› የሚል አንድምታ ያዘለ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
የግጥሙ አጠቃላይ ጭብጥ (ይዘት) በያኔዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነመፈጠራቸውም ተረስተው ይኖሩ የነበሩትን የብሔር፤ ብሔረሰብ ህዝቦች ስም፤ በዝርዝር እየጠቀሰ ታዲያ ይህቺ ሀገር አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ተደርጎ የሚቆጠርባት አይደለችምን? የሚል ቃና ያዘለ ምፀታዊ ጥያቄውን በአፅንኦት ያነሳበት ሆኖ በመገነቱ ምክንያት ወጣት ኢብሳን በ‹‹ገንጣይ- አስገንጣይነት›› አስጠርጥሮት እንደነበርም ጭምር የሚያስታውሱ የዚያን ዘመን ፖለቲከኞች አሉ፡፡ እናም እነዚሁ ወገኖች ፅፈው ካስነበቡን የአይን ምስክርነት መረዳት እንደሚቻለው፤ ያኔ ኢብሳ ጉተማ ‹‹ማነው ኢትዮጵያዊ?›› በሚል ሞጋች ርዕስ፤ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዓመታዊ የውድድር መድረክ ላይ አቅርቦ ያሸነፈበትን ግጥም ካልወደዱለት ሰዎች አንዱ ዋለልኝ መኮንን ስለነበር ነው ዛሬም ድረስ ሁለቱን ወጣቶች አብረው እንዲነሱ የሚያደርጋቸው ታሪካዊ አጋጣሚ የተከሰተው፡፡
ለማንኛውም ግን፤ ከሁለቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ወጣት ፖለቲከኞች ጋር ተያይዞ የሚወሳው ፍሬ ነገር ከሞላ ጎደል የሚከተለውን ይመስላል፡፡ እርሱም፤ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ካውንስል አባል የነበረው ዋለልኝ መኮንን፤ ኢብሳ ጉተማን ወደ አንድ ጥግ ወስዶ ‹‹ እንዲያው ምንስ ሃሳብህን የመግለፅ መብት ቢኖርህ እንዲህ ዓይነቱን አገር የሚያፈርስ ርዕሰ ጉዳይ ያውም በዚህ መድረክ ላይ ታነሳለህ እንዴ ጃል!? እኛ መታገል ያለብን እኮ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ የሚታደግ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ነው እንጂ ጭራሽ በጎሳና በብሔር ብሔረሰቦች ግጭት ወደ ጠቅላላ ጥፋት የሚያስገባትን ዘረኝነት ለመቀስቀስ አይደለም፡፡ ደግሞስ አንተን የህል የተማርክ ሰው ኃላፊነት ካልተሰማህ ከተራው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምን የሚጠበቅ ይመስልሀል!?›› ወዘተረፈ እያለ ተግሳፅ አዘል ምክሩን ሊለግሰው ይሞክራል፡፡
ከዚያም፤ ኢብሳ በተራው ‹‹ አይ ዋለልኝ፤ ተጨባጩን የጋራ ችግራችንን በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ስላለፍነው ብቻ እቺን ሀገር ከብተና አደጋ መታደግ ይቻላል ብለህ ታስባለህ?›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ እንደመለሰለትና ከዚህ የተነሳም በሁለቱ ወጣት ምሁራን መካከል ለስዓታት የቆየ ፖለቲካዊ ክርክር እንደተካሄደ ነው የታሪክ ድርሳናት የመዘገቡት፡፡ ይህን የምስክርነት ቃል በፅሁፍ መልክ አስፍረው የተውሰን የ1960ዎቹ ለውጥ ፈላጊ ትውልድ አባላት እንደሚነግሩን ከሆነ ደግሞ፤የሁለቱ ተጠቃሽ ወጣቶች ፖለቲካዊ ክርክር የተቋጨው በኢብሳ ጉተማ አሳማኝነት ነበር፡፡ መቸስ አንድን ፈፅሞ ሊስተባበል በማይችል መልኩ እጅጉን አፍጥጦና አግጥጦ የሚታይን ነባራዊ ጥሬ ሀቅ አምኖ የመቀበል አለመቀበል ጉዳይ ነገሮችን በምክንያታዊነት አስደግፎ የማጤን ቅንነት እንጂ የዚያኛው፤ወይም የዚህኛው ብሔር ተወላጅ ሆኖ መገኘትን አይጠይቅምና ዋለልኝ ሊመክር ሔዶ ጠቃሚ ምክር ሲቀስም ጊዜ አቋሙን ማስተካከሉ ሊያስገርመን የሚገባ አይመስለኝም፡፡
እንዲያውም፤መጀመሪያ ከኢብሳ ጋር ያነታረካቸውን አከራካሪ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ አድርጎ የዚችን ሀገር ህዝቦች እጅግ በጣም የተመሰቃቀለና የተዛባም ጭምር ግንኙነት በጥልቀት ለመመርመር ባይሞክር ኖር “ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” ሲል አሳምሮ የገለፀበትን መጣጥፉን በለውጥ ፈላጊዎቹ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መፅሔት ላይ ባላቀረበና ከዚያን ጊዜ በኋላ የአጠቃላይ ንቅናቄውን የትግል አቅጣጫ ፈር ለማስያዝ ባልበቃም ነበር ዋለልኝ መኮንን፡፡ አንድን ጉዳይ ማንም ያቅርበው ማን፤ሊስተባበል የማይችል ጠቃሚ እውነት ያዘለ ሆኖ እስከተገኘ ግን፤ ድፍን ዓለም የማይስማማበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ የዛሬዋ የፌደራላዊት፤ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የምትመራበትን ሕገ መንግስታዊ እሳቤ ህወሐት አመጣሽ አድርገው በመውሰድ ብቻ፤ አቃቂር ሊያወጡለት የሚሞክሩ ወገኖች ሀቁን ሸሽቶ ማምለጥ እንደማይቻል ከዚሁ የዋለልኝ ቅንነት ይማሩ ዘንድ እመክራለሁ፡፡
በግልፅ አማርኛ እንቅጩን መነጋገር ካለብን ደግሞ፤ኢህአዴግ “በኢትዮጵያ አጠቃላይ እውነታዎች ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት አለመገንባት ጉዳይ የህልውና ጥያቄ እንጂ ምርጫ አይደለም!” የሚለውን ፅኑ አቋም ሲያራምድ የሚስተዋለውም፤ከላይ በተወሳው የፖለቲካዊ ታሪካችን ዳራ ለነዋለልኝ ትውልድ የተገለፀለትን እቺ ሀገር የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦቿ በፈርጀ ብዙ ጭቆና የሚማቅቁበት የመሆኗን ጥሬ ሀቅ የሚያመለክት ነባራዊ እውነታ፤መሰረት ላደረገ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ እታገላለሁ የሚል ማንኛውም ፓለቲካዊ ሃይል፤የዴሞክራሲን አስፈላጊነት ዘንግቶ ቢገኝ “ውሃ ልትቀዳ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃውን ረስታ መጣች”የሚያሰኝ ግዙፍ ስህተት እንደመፈፀም ሊቆጠር የሚችል ሆኖ ይሰማኛል ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ፤ያኔ በነበረው የሀገራችን ተራማጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሃይል አሰላለፍ ውስጥ፤ከላይ በተወሳው የዋለልኝ መኮንን ትንታኔ አማካኝነት ግልፅ የተደረገውን የጋራ ችግር አምኖ ለመቀበል የተቸገረ አለመስተዋሉንና ልዩነቱ አደጋውን እንዴት መቀልበስ ይቻል ይሆን?ከሚለው ጥያቄ አኳያ የሚሰነዘርን የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ ረገድ የሚገለፅ ብቻ እንደነበር የሚያስረዱ መፅሐፍት ጥቂት አይደሉምና ነው፡፡
ከዚህ የተነሳም፤ኢብሳ ጉተማን ጨምሮ ሌሎች የ 1960 ዎቹ ትውልድ አባል የሆኑ ብሔርተኛ የኦሮሞ ወጣት ፓለቲከኞች “ከዚህ በሁዋላ በዚች ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ውስጥ አብሮ ለመቀጠል የሚያስችል ምንም ዓይነት የጋራ እሴት ያለን ህዝቦች ነን ብሎ ማመን ተራ የዋህነት ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት፤የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦ.ነ.ግ ) በመባል የሚታወወቀውንና ኦሮሚያን ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለመገንጠል ያለመ አጀንዳ የሚያራምደውን ድርጅት መስርተው ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግሉን ለመጀመር ወደ ጫካ ወረዱ፡፡
እንዲሁም ደግሞ ለአሁኑ ኢህአዴግ መፈጠር ፅኑ መሰረት እንደጣለ የሚነገርለትን ሌላኛውን የ1960ዎቹ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ፈላጊ ወጣት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች የሚወክሉበትን የአስተሳሰብ ጎራ ያራምዱ የነበሩት የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ ተዋናይ ምሁራን “የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ እስከ መገንጠል በሚቀልቅ መብትና ነፃነት የሚያረጋግጥ ሕገ መንግስት እንዲኖረን ማድረግ ከተቻለ እንደ ሀገር አብረን የማንቀጥልበት ምንም ምክንያት የለም” የሚለውን አቋም እንደ ቀዳሚ የመፍትሔ አቅጣጫ ወስደው፤በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚገለፅ ፀረ ጭቆና ትግላቸውን ተያያዙት፡፡የዛሬን አያርገውናም፤እነ ኢ.ህ.አ.ፓ.ንና መ.ኢ.ሶ.ን.ን ጨምሮ፤ ሌሎዎች የ1960ዎቹ ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊ ወጣት ምሁራን ዜጎቻችን የመሰረቷቸው ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፤አሁን በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 ላይ የሰፈረውን መሰረተ ሃሳብ ያለ አንዳች ማቅማማት የሚቀበሉበት ሁኔታ ተስተውሎ እንደነበር ነው የታሪክ መዛግብት የሚያመለክቱት፡፡
ይህን ስንልም ደግሞ፤ከኦ.ነ.ግ. በስተቀር ገና ከመነሻው “አብሮ መቀጠል አይቻልም” የሚል አቋም ላይ የደረሰ የዚያን ዘመን ፓለቲካዊ ድርጅት እንዳልነበርና በርካታ የኦሮሞ ወጣት ምሁራን ጭምር በአባልነት ታቅፈው ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የታገሉባቸው እንደ መ.ኢ.ሶ.ን ዓይነቶቹ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎችም እንኳን “ባለፈው ታሪካችን የተፈፀሙ ስህተቶች እንዲታረሙና አሉታዊው የህዝቦች ግንኙነት በጤናማ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት እንዲተካ የሚያደርግ ዴሞክራዊያዊ አንድነት መፍጠር የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም” ብለው ያምኑ እንደነበር የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡
አንድ ወቅት ላይ፤እጅግ ገናና ስም በነበረው የኢ.ህ.አ.ፓ .ሀገር አቀፋዊ መዋቅር ውስጥ ታቅፈው፤የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦቿ እርስ በእርስ ተፈቃቅደው፤ተከባብረውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመመስረት ያለመ ፀረ ጭቆና የትግል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የወደቁት የአገዛዝ ስርዓቶች ጭፍጨፋ ሰለባ የመሆን እጣ የገጠማቸው የአማራው፤የኦሮሞው፤የትግራዩ፤የመላው ደቡብ ህዝቦችና እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያዊው ሶማሌ፤የሐረሪው፤የአፋሩ፤የመሻንጉል ጉሙዙና የጋምቤላው ተወላጅ ቀለም ቀመስ ወገኖቻችን ጭምር፤በዚች አገር የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከመሻት በሚመነጭ ተቃውሞ ተሰልፈው የየራሳቸውን ጥረት ሲያደርጉ ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነት ለመክፈል የተገደዱበት ምክንያት ዴሞክራሲ ለኛ የህልውና ጉዳይ የመሆኑን እውነት ስለተረዱ ነው ብለን ብናምን ስህተት እንደማይሆን ይሰማኛል፡፡
ይልቅስ፤ዛሬ ላይ በሀገራችን የሰፈነውን የፌደራሊዝም ስርዓት እንደ መልካም ዕድል ተጠቅመው ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ የበቁትን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመምራት ታሪካዊ ሃላፊነት የተጣለብን ዜጎች፤የዴሞክራሲን አስፈላጊነት ባስከፈለን ፈርጀ ብዙ ዋጋ ልክ እንገነዘበዋለን ወይ? ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ነው አንገብጋቢ የቤት ስራችን መሆን የሚኖርበት፡፡እንደኔ የግል ትዝብት የሚወሰን ምስክርነቴን እንድሰጥ የሚፈቀድልኝ ከሆነ ግን፤ከአንድ የትውልድ ዘመን በላይ በረዘመ የፀረ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና የትግል ሂደት ተሰልፈው የአፈና አገዛዞችን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲፋለሙ ክቡር ህይወታቸውን እስከማጣት የደረሰ መስዋዕትነትን የከፈሉት እልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለወደቁለት የዚች አገር ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብት መረጋገጥ እንብዛም ስንጨነቅ አንስተዋልም ባይ ነኝ፡፡
እንዲያውም አንዳንድ የፌደራሉ መንግስትና እንዲሁም ደግሞ የክልል መስተዳደሮች አስፈፃሚ አካላት፤ ለጉዳዩ ካላቸው አናሳ ግንዛቤ በሚመነጭ ግዴለሽነት ዴሞክራሲን በስሙ ሲገድሉት የሚታዩበት አግባብማ ብዙ የሚያስተዛዝብ ገፅታ እንዳለው ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ስለዚህ እንደኔ እንደኔ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንጂ ምርጫ አይደለም” ስንል የምር ከማመን በሚመነጭ ተግባራዊ እርምጃ አስደግፈን ካልገለፅነው በስተቀር ትርፉ እርስ በርስ ከመተዛዘብ አያልፍም የሚል እምነት አለኝ፡፡ አለበዚያ ግን፤
በጉብዝና ወራታችን ፤የህዝቡ ጉዳት ቢሰማን
ከቁም ሞት ልንታደገው፤እንዳልቆሰልን ፤እንዳልደማን
ታዲያ ዛሬ በስተ እርጅና፤ ህሊናችንን ማን ቀማን!?
እያልን በአፅንኦት መጠየቃችንን የማንቀጥልበት ምክንያት እንደማይኖር ልብ ይባልልን፡፡ በተረፈ መጭው ዘመን ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ባህል ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አብቦ የምናይበት ይሆን ዘንድ እየተመኘሁ የዛሬውን ሃተታየን እዚህ ላይ ልቋጨው፡፡
መዓ ሰላማት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy