Artcles

ድርቅን በተቀናጀ አቅም መቋቋም ተችሏል!!

By Admin

May 16, 2017

ድርቅን በተቀናጀ አቅም መቋቋም ተችሏል!!

ስሜነህ

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን የድርቅ አደጋ ደርሶባታል፡፡ በዚህም ድርቅ  ከ5 ሚሊዮን የማያንሱ ወገኖች ለምግብ ዋስትና እጦት የተዳረጉ ሲሆን፣ መንግሥት 15 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለመቋቋም ችሎ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተያዘው ዓመትም እንዲሁ ከ5.2 ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎች ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የተዳረጉ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቋቋም 948 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱም ተከታታይ የድርቅ አደጋዎች ይህ ነው በሚባል ደረጃ የውጭ ዕርዳታ ባይገኝም፣ መንግሥት ከራሱ ግምጃ ቤት በጀት በመመደብ ችግሩን ለመቀልበስ ችሏል፡፡

በዚህ ሂደት የመሠረተ ልማትና የውኃ እጥረት ችግሩን ከማባባሳቸው በተጨማሪ ሕገወጦች ለተጎዱ ወገኖች የሚላከውን ዕርዳታ ለራሳቸው ለማዋል የሚሞክሩበት አጋጣሚም ተፈጥሮ  የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ከእርዳታው ክፍፍል ባሻገር መንግስት እየተጋ ለመሆኑ ማሳያው የኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ እስካሁን ባለው ሁኔታ አጀንዳ ሆኖ አለመገኘቱ ነው፡፡ድርቁን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም በመንግስት በኩል የተገነባ ቢሆንም ግን ዘላቂነት ላለው መፍትሄ የችግሮቹን ምንጭና የተሳትፎውን ደረጃ ፈትሾ ሁሉንም ባለድርሻ ማብቃት ያስፈልጋል ።  

ለሁለት ተከታታይ አመታት ሰለባ ለሆንበት ድርቅ ምክንያት የሆኑት የኤልኒኖ ክስተቶች ሁለት እንደሆኑ የሚገልጹት የዘርፉ ተመራማሪዎች በእኛ ላይ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ልንቆጣጠረው የማንችለው ላኒና የተባለው የኤልኒኖ ክስተት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ላኒና በውኃ ብዛት ጉዳት የሚያደርስ ክስተት ነው፡፡ ባለፈው አመት ገጥሞን በነበረው ድርቅ ሰው የሞተብን በድርቁ ምክንያት ሳይሆን በውኃ ሙላትና በመሬት መንሸራተት ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ክስተቱ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ነው፡፡ ድርቁን በተመለከተ ግን መንግስት በቂ ዝግጅት አድርጎ የነበረ በመሆኑ መቋቋም ስለመቻላችን የአለም አቀፍ ሰብአዊ ተቋማት መስክረዋል።  

ከአምና የተሻገሩ ምርቶች በትክክል መጠናቸው እንዲታወቁ መደረጉ የመጀመሪያውና የመንግስት ዝግጁነት መገለጫ ሲሆን፤ ሁለተኛ በአምናው ግዥ አገር ውስጥ ያልገቡ ምርቶች በወቅቱ  እንዲገቡ መደረጉ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከስትራቴጂካዊ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ወጪ እንዲሆን መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ ድርቁን ለመቋቋም ካስቻሉን ምክንያቶች ዋነኞቹ እና የመንግስትን ዝግጁነት የሚያጠይቁ ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ እጅግ የባሰ ሁኔታ ይመጣል የሚል ሥጋት እንዳለ በመንግስት በኩል ተገልጿል። የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ትንበያን መሰረት ያደረገው የስጋት መግለጫ  የበልግ ዝናብ እጥረት ስለሚታይ ድርቁ ሊጨምር ይችላል የሚል ነው፡፡ መንግሥት ከ5.2 ሚሊዮን ያላነሱ ተረጂዎች አሉ ብሎ ይፋ ያደረገው የመኸር ግምገማ ውጤት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ የበልግ ግምገማ ቀጥሎ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ግምገማ የተረጂዎች ቁጥር  ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል፡፡ ለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስት ተጨማሪ መጠባበቂያ የምግብ ክምችት እና የአደጋ ጊዜ ፋይናንስ መያዙን አረጋግጧል፡፡

በእንዲህ አይነት ስትራቴጂካዊ ዕርምጃዎች ችግሮችን መቋቋም እንደቻለ የሚገልጸው መንግስት አሁን ያጋጠመን ችግር ከአምና የሚለይባቸው ባህርያት ያሉት መሆኑንም ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና ችግር ያጋጠመው በአርብቶ አደር አካባቢዎች ነው፡፡ አካባቢዎቹ ቆላማና ጠረፋማ ናቸው፡፡ የተደራሽነት ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህ የተበጀው መፍትሔ ደግሞ በከባድ ተሽከርካሪዎች (400 ኩንታል የሚጭኑ) እስከ አደጋ ቀጣናው የተወሰነ ቦታ ድረስ የዕርዳታ ምግቦችን እንዲያደርሱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በመለስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎችና በጋማ ከብቶች በማጓጓዝ ተደራሽ እየተደረገ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ኮማንድ ፖስት አለው፡፡ እነዚህ መዋቅሮች ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡

አሁን ባለው ስታንዳርድ በወር 47 ሺሕ ሜትሪክ ቶን (470 ሺሕ ኩንታል) እህልና አልሚ ምግቦች አሉ፡፡ ለ5.6 ሚሊዮን ተረጂዎች 35 በመቶ ክምችት ተይዟል፡፡ አልሚ ምግቦች ለእናቶችና ለሕፃናት የሚውሉ ናቸው፡፡ ሁለተኛ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ በክምችት ላይ ያለ እህል እንዳይበላሽ ጥቅም ላይ እየዋለ ከሥር ከሥር እየተተካ መሆኑን የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን አስታውቋል፡፡እንደውም የተረጂዎች ቁጥር እጥፍ ቢሆን እንኳ የመቋቋም አቅም ሃገሪቷ ያላት መሆኑን  ኮምሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው እና የኮምሽኑን ማረጋገጫ አሳማኝ እንደሆነ የሚያረጋግጠው ለእርዳታ የሚያስፈልገው ከላይ የተመለከተ ገንዘብ እስካሁን በአብዛኛው እየተሸፈነ ያለው በመንግሥት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የአጋሮች ድርሻ በፍጹም የለም ማለት አይደለም። ሁለት መሠረታዊ አጋሮች እንዳሉ ኮምሽኑ ገልጿል፡፡ አንደኛ የሶማሌ ክልልን በአብዛኛው የያዘው የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ነው፡፡ ሁለተኛ በካቶሊክ ሪሊፍ አስተባባሪነት በጥምረት የሚሠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ነው፡፡ አምና የያዙትን ኪስ ቦታዎች ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት እየሸፈነ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ለተረጂዎች 919,179 ሜትሪክ ቶን ምግብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 744,275 ሜትሪክ ቶን እህል፣ 74,428 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ፣ 22,328 ሜትሪክ ቶን ዘይት፣ 78,148 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ ያስፈልጋል፡፡ በገንዘብ ደግሞ 948 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ፡፡

አልሚ ምግብ የሚሰጠው ለሕፃናትና ለሚያጠቡ እናቶች ነው፡፡ይህም እየሆነ ያለው ትኩረት የሚሹ አካባቢዎችን በመለየት እንደሆነ የሚገልጸው ኮምሽኑ ሦስት የትኩረት ቦታዎች መለየቱን አረጋግጧል፡፡ በትኩረት አንድ 192 ወረዳዎች አሉ፡፡ በትኩረት ሁለት 174 ወረዳዎች አሉ፡፡ በትኩረት ሦስት 88 ወረዳዎች አሉ፡፡ ጠቅላላ 454 የትኩረት ወረዳዎች አሉ፡፡በዚህ አግባብ አብዛኛው አልሚ ምግብ የሚሰጠው ለትኩረት አንድና ለትኩረት ሁለት ነው፡፡ አልሚ ምግብ የሚሰጠው ፅኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው አካባቢዎች ነው፡፡ በዚህም የተጠቃሚዎችን 35 በመቶ የሚሆነው በመጠባበቂያ ክምችት  በተረጂዎች ቁጥር ላይ ተመስርቶ ተይዟል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም በሎጀስቲክስ በኩልም አቅም ተገንብቷል፡፡ ከጂቡቲ የሚነሳው ለግል የትራንስፖርት ኩባንያዎች በጨረታ እየተሰጠ ነው፡፡ በርካታ አቅም ያላቸው የትራንስፖርት ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ ኮምሽኑ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የማከማቸት አቅም ያለው መጋዘን አዳማ ከተማ ውስጥ አዘጋጅቷል፡፡ እያንዳንዳቸው 300 ሺሕ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው መጋዘኖች በኮምቦልቻና በድሬዳዋ ከተሞችም አሉ፡፡   ስለዚህ እህሉ ከወደብ ተነስቶ ወደእነዚህ መጋዘኖች ይገባል፡፡ ወደ ተጠቃሚው ሕዝብ ለማድረስ ኮምሽኑ 20 ከባድ ተሽከርካሪዎች (400 ኩንታል የሚጭኑ)፣ እንዲሁም 200 ኩንታል የሚጭኑ 20 ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ እነዚህን ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀመው በጣም አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮች ነው፡፡ ለጨረታ ዕድል ለማይሰጡ ።

ስለሆነም የከፋውን ድርቅ በመንግሥትና በህዝብ የተቀናጀ አቅም መቋቋም ተችሏል ። በአገራችን ድርቅ ረሀብ  የማይሆንበት  ሁኔታም  ተፈጠሯል። መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው ከሰሩ ለሁሉም ችግሮቻችን መፍትሄ እንደሚሰጡ ባለፈው አመት የታየው ልምድ ያሳያል። የአገራችን ህዝቦች የመረዳዳት ባህላቸውን  (የአማራና የትግራይ ክልሎች  በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ያደረጉትን ድጋፍ) እንዲሁም በኦሮሚያ ያሉ በድርቅ ያልተጎዱ ዞኖችና ወረዳዎች  እያደረጉ ያሉትን ድጋፎች  ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።  በተመሳሳይ በርካታ ባለሃብቶች  በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች  እያደረጉ ያሉት ድጋፍም ሌላኛው ማሳያና ዘላቂነት ላለው መፍትሄ ሊወሳ የሚገባው ነው።  እንዲህ ያሉ መልካም ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

ድርቁ በተከታታይ ዓመትም ሊቀጥል እንደሚችል አንዳንድ የሜትሪዮሎጂ  ትንበያዎች ያሳያሉ። በመሆኑም  የግብርና ባለሙያዎች  አርብቶና አርሶ አደሩን በማስተባበር ጠብ የምትለውን የዝናብ  ውሃ የማቀብ ስራ መስራት  ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃዎችን በአግባብ በመጠቀም የመስኖ ስራዎች ማከናወን ተገቢ ነው።  ህብረተሰቡም ቀድሞ ያዳበረውን የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።