Artcles

ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ሞጋች ትውልድ ለመፍጠር

By Admin

May 02, 2017

ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ሞጋች ትውልድ ለመፍጠር  /ዮናስ / 

በሃገራችን ህገ መንግስቱ በተመለከት የሚወጡ ድንጋጌዎች እንዲሁም ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ የተለያዩ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ የሚደረጉት በአስፈጻሚው አካል ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት የሕዝብን አደራ ተቀብሎ ሲያስተዳድር ከሃገር ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጋር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ የማያጠያይቅ ነው፡፡  በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ሕግ በማስከበር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ፣ በመሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ በመሬት አስተዳደርና ልማት፣ ወዘተ የሚደረስባቸው ውሳኔዎችና የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ደግሞ ከሕዝብ ፍላጎትና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡ ይህ በተግባር እንዲረጋገጥና መንግስትም ኃላፊነቶችን እንዲወጣ በማድረጉ ረገድ ባለድርሻዎቹ ብዙ ናቸው ፡፡ ከነዚህ ባለድርሻ አካላቱም የሚጠበቅባቸውን እምብዛም ያልተወጡ ስለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙባቸው ሲቪክ ማህበራትና ሚዲያ ነው።

ከዚህ ቀደም ሕዝብና መንግሥትን ያቀያየሙና ለግጭት የዳረጉ ጉዳዮች ምንጫቸው በመንግስት በኩል የነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦቶች፣ ፍትሕ መጓደልና ሙስና የመሳሰሉት ምክንያቶች ብቻ  ሳይሆን እነዚህ ባለድርሻ የሆኑ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸውም ጭምር መሆኑ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይልቁንም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የአፋኝነት ባህሪ ያላቸው ሕጎች፣ የሕዝብን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያሰናክሉ አጓጉል ድርጊቶች፣ በሕዝብ መሀል ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ውሳኔዎች፣ የአቅምና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ተሿሚዎች መብዛት፣ የሕገወጥነት መስፋፋት፣ የሕግ የበላይነትን መጋፋትና የመሳሰሉትን ችግሮች አስቀድሞ የመታገልና የማታገል ሚና የነዚሁ አካላት ነበር። እነዚህን ችግሮች በፍጥነት በማረም የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰድ ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸው የነበሩት እነዚህ አካላት በተለይ አንዳንዶቹ የሕዝብን ቁጣ በሚያንርና በሚያባብስ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው መገኘታቸው የበለጠው አደጋና ስጋት ሆኖ ቆይቷል ፡፡  

በእነዚህ ምክንያቶች ሃገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተዳርጋለች፡፡ የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ ለአራት ወራት ተራዝሟል፡፡ አዋጁ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋት ለመፍጠር ቢጠቅምም፣ ለአገሪቱ ዘለቄታዊ ህልውና ሲባል መንግስት የራሱን ጥልቅ ተሃድሶ ቢያደርግም እነዚህ ባለድርሻዎች ግን በተሃድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለመሆን አለመሆናቸው የተሰማ አንዳች ነገር የሌለ መሆኑ ያሳስባል ።  

ምርጫን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ጀምሮ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በማድረጉ ሂደት ያለነዚህ አካላት ተሳትፎ መንግሥት ለብቻው ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም። መንግሥት የሕዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ከሚችልባቸው መንገዶች መካከል ሲቪል ማህበራት እና ሚዲያ ግንባር ቀደምቶቹ ናቸው።  

የእነዚህ አካላት ዋነኛ ተልእኮ በሕግ የበላይነት ሥር ለሕዝብ ታዛዥ የሆነ መንግሥት የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ታግሎ ማታገል ነው፡፡ይህን ተልእኮ በአግባቡ የሚወጣ ሚዲያዎችና የሲቪል ማህበራት ቢኖሩን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አሁን ካለበት ደረጃ በበለጠ ከፍታ ይጠናክራል፤ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ይሰፍናል፤ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፤ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥርጊያው ይመቻቻል፤ የሙያና የሲቪክ ማኅበራት በብዛትና በጥራት እንዲያብቡ ይረዳል፣ የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ይረጋግጣል፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት የአገር ባህል እንዲሆኑ ያግዛል፤ የአገር ባለቤትነት መንፈስ ይፀናል፡፡ የበለጠ ደግሞ ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ለማፍራት መንገዱ ሁሉ አልጋ ባልጋ ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሲቪል ማህበራት የምንላቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ ሚዲያዎቻችን ከዚህ ተቃራኒ ተሰልፈው መገኘታቸው ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡

የምዕራባዊያንን እጅ በትከሻቸው ላይ ጭነው ኢትዮጵያዊነታቸውን ደግሞ ፈቃድ ማግኛ ያደረጉ ሚዲያዎችና የሲቪል ማህበራት የወሰዱት ፈቃድ ስለሃገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አልያም ደግሞ ልማት ቢሆንም በተግባር ግን በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ሌላ ሆነው መገኘታቸው ነው አሳሳቢው። ተቋማቱን እንደተቋም ጨምሮ በእነዚህ ተቋማት  ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች ለምእራባውያን አለቆቻቸው መረማመጃ ከመሆንም አልፈው ራሳቸውን አንጥፈው የሸጡባቸውን በርካታ ሁነቶች አይተናል። እነዚህ ተቋማትና ተቋማቱን በመምራት ስም የተሰየሙ ዜጎቻችን ከሚከፈላቸው ዩሮ እና ከሚመነዝሩት ዶላር  በላይ የሃገሪቱ ልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጉዳያቸው እንዳልሆነም በተለያዩ እና ለአደባባይ በበቁ ሴራቸው ተረጋግጧል። አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ከጀርባቸው አድርገው የተቋቋሙ ሲቪል ማህበራት ዜጎቻችንን ለተለየ እና ለአውዳሚ ተግባራቸው በውድ ዋጋ ሲገዙ ታይተዋል። ከዚያም የከበረ ወንበር ያሰናዱላቸዋል። በመቀጠል ደግሞ በየባህር ማዶው   ‹‹ፈረንጅ ባይደርስልን ኖሮ ተናንቀን እንተላለቅ ነበር፤  ፈረንጅ ባይደርስልን ኖሮ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተተብትበን እንሰቃይ ነበር›› ሲሉ ያስደሰኩሩና ፈረንጅ አምላኪ አድርገው እኛም ፈረንጅ አምላኪ እንድንሆን ይቀሰቅሱና ይሞግቱ ዘንዳ ሲልኩብን በተደጋጋሚ አይተናል። አስነዋሪ ስድቦችን ተሳድበው፣ ህዝባችንን በፈረንጅ አፍ ከስሰው፣ አቁማዳቸውን ሲሞሉም በተጨባጭ አይተናል።   

ሚዲያን የተመለከቱ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችም ሆኑ አዋጆች መነሻነት ብሄራዊ የሚዲያ ፖሊሲያችን በመድበለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የህብረተሰቡን የፖለቲካ ብዙሃነት፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ፈርጀ ብዙነት ከመቀበል የሚነሳ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖም ሚዲያው በማንኛውም የባለቤትነት ውስጥ ቢሆን ብሄራዊ መግባባትን ለማስረጽ መተኪያ የሌለው ቀዳሚ ሚና እንዲጫወት ፖለቲካል ኢኮኖሚው እና ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ያስገድዳል።

የመገናኛ ብዙሀንን የልማት አቅጣጫዎች በዝርዝር የሚተነተነውና በዋናነት በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የተስተካከለ የመገናኛ ብዙሃን ልማት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጠው / Media Development indiCators የተባለው የዩኔስኮ ሰነድ ሁለት ጥናትን መሰረት ያደረጉ ተያያዥ መነሻዎችን አስቀምጧል።

የዓለማችን የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ፍሰት አንደ ሃብት ክፍፍሉ ሁሉ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑ የመጀመሪያው መነሻ ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙሃኑ በባለቤትነትም ሆነ የአሰራር ፍልስፍናው በሊበራል አስተሳሰብ የሚመራና የመረጃ ፍሰቱም በዚሁ የሚወሰን በመሆኑ በማደግ ላይ ባሉና በድሃ ሀገሮች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩ ደግሞ ከአንደኛው ጋር የሚያያዝ ወይም የአንደኛው መነሻ ሌላኛው የሳንቲም ገጽታ የሆነ መነሻ ነው።

ይህ ስለሆነም በምዕራቡ አለም የሚታየውን የግል መገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት ሞኖፖሊ በመረጃ ፍሰት ላይ የፈጠረውን አሉታዊ ተጽእኖ በማገናዘብ ይፋ የተደረገው የዩኔስኮ ሰነድ ማህበረሰቡን በንቃትና በስፋት የሚያሳትፉ የመገናኛ ብዙሃንን በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ማስፋፋት የግድና ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣል።

በእነዚህና በማደግ ላይ በሚገኙ ሃገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃኖች (አስቀደሞ በሃገራችን እየተሰራበት ባለው መንገድ) እንዲሰሩ ይመክራል። የመገናኛ ብዙሃን  ሚና የዜጎች የመረጃ ልውውጥና የክርክር መድረክ ሆኖ ማገልገል፣ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በንግድ ተቋማት መካከል ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ በእውቀት ላይ በተመሰረተ የሃሳብ ክርክር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማጎልበት፣ የህዝቡን ባህል፣ ልምድና እሴት መገለጫና ማሳደጊያ መድረክ ሆኖ ማገልገል፣ በመንግስት ሥራ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማሳደግ፣የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን እንዲሁም የንግድ አሻጥሮችን ማጋለጥ፣ የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠንና ውጤታማነቱን ማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ይዘረዘራል።

በዚህ አግባብ መንግስትና ህዝቡ ችግራችን የስራ ዕድል ፈጠራ ፣ የቤት ልማት ፣ የመንገድና የትራንስፖርት አገልገሎት ፣ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፤ ብለው እነዚህን ከአጭርና ከመካከለኛ ጊዜ አኳያ ለመፍታት ሲረባረቡ ሚዲያውም ይህንኑ በመደገፍ ሂደት ውስጥ የጎላ ሚናውን ሊጫወት ሲገባ ከዚህ ተቃራኒ ሆኖ መሰለፉ በርከት ያሉ ዋጋዎችን አስከፍሎናል።

የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን ያረጋገጠውን ህገ መንግስት ሳይቀበሉ የሚዲያ ነፃነት ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ ጋዜጦች በሃገራችን የነበሩና አሁንም ያሉ የመሆናቸው እውነትነት ነው። መገናኛ ብዙሃን የህዝብ የመረጃ ምንጭ የውይይትና የክርክር መድረክ ሆነው ከማገልገል ይልቅ ሥርዓቱን ለሚቃወሙ ወገኖች ልሳን የሚሆኑበት ሁኔታም መፈጠሩ ሌላው የማይካድ እውነታ ነው።

ታፈንን፣ ተዘጋን በማለት የሚጮኹት ፕሬሶችም ቢሆኑ ታፍነው ከሆነና ተዘግተው ከሆነ የመታፈናቸውና የመዘጋታቸው መነሻ ከፖለቲካል ኢኮኖሚው ባሻገር የመቃኘታቸው የትም የማያደርስ አካሄድ ብቻ ነው የሚሆነው ።  

በአብዛኛዎቹ የህትመት ሚዲያዎች ላይ የሚታየው ማስታወቂያ እንጥል እቆርጣለሁ፣ ግግ እቧጥጣለሁ የሚል የአንድ ደብተራ ማስታወቂያ ነው። ስለሆነም ኮሜርሻል አይደሉም፤ ኮሜርሻል ካልሆኑ ይደጎማሉ፤ በድጎማ የሚተዳደሩ ከሆነ ታማኝ አንባቢ አላቸው ። ከተወሰኑ ርዕዮተ አለማዊ አጥሮች አልፈው መጓዝ አይፈልጉም። ስለሆነም የህትመት ሚዲያ እድገት ላይ አንድ ትልቅ ጋሬጣ የሆነው ከነፃ ሚዲያ ህግጋት ውጪ ተንጋዶ የበቀለ የሚዲያ አካሄድ ነው ብሎ መውሰድ ስለሚቻል ከሃገራችን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አኳያ ስጋታችንን ይጨምርብናል።

በጥቅሉ ስለልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከላይ የተመለከቱ ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው ሚዲያና ሲቪል ማህበራት በሰብአዊ መብት ጥላ ስር ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ማራመድ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ኢ-ስነምግባራዊ “ጥናቶች’’ በማሰራጨት ሉዓላዊነትን የሚጥሱ፣ በወገንተኝነት የሚመሩ ጣልቃ ገብነቶች በማድረግ፣ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎችን በማገዝና በማስተባበር፤የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አጋኖና አዛብቶ በማቅረብ፣ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን በሚል ሽፋን የመንግስታትን ስልጣን በመሻማትና ሀገራዊ ሰላምን በማደፍረስ፣ ግለሰባዊ የፖለቲካ አቋሞችን በማራመድ ወዘተ ስራዎች ዘወትር ሲጠመዱ የሚጎለብተው ሞጋች ሳይሆን ድንጋይ ወርዋሪ ትውልድ ስለሚሆን ከዚህ የተዛነፈና ያልተገባ ተግባር ወጥተው ከላይ በዮኔስኮ በተመለከተውና በህገመንግስቱ በተመለከቱ ድንጋጌዎችና መርሆዎች ሊመሩ ይገባል።