NEWS

ዶ/ር ቴድሮስ በስልጣን ዘመናቸው ለታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ገለጹ

By Admin

May 25, 2017

ትናንት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን የተመረጡት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በስልጣን ዘመናቸው ለአፍሪካ እና ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ ገለፁ።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲመረጡ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ የጤና ባለሙያዎችን በአቅም እና በቁጥር በማሳደግ እና በመድሃኒት አቅርቦት ስኬታማ ስራዎችን አከናውናለች ነው ያሉት ዶክተር ቴድሮስ።

በጤና ፋይናንስ እና ወረርሽኝን በመቆጣጠር ረገድም ሀገሪቱ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች ብለዋል።

ሁሉንም ያካተተው የጤና ስርአት ለውጥ ሀገሪቱ አብዛኛውን የምዕተ አመቱን ግብ ቀድመው ካሳኩ ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ተያያዥ ዜና፦ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ተመረጡ 

“የጤና ስርዓቷን በመቀየር ለውጥ ካስመዘገበ ሀገር የሚመጣ ሰው በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ሲገባ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት የሚታዩ ችግሮችን ሊፈታ ወይም ሊያግዝ ይችላል” በማለት ሀገራት ድምፃቸውን እንደሰጧቸው ነው ዶክተር ቴድሮስ የተናገሩት።

ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ ዋነኛ መርሃቸው “ጤና ለሁሉም” እንደሚሆን የተናገሩት ዶክተር ቴድሮስ፥ ሁሉም ሀገር ጤናን እንደ መብት በመቁጠር የጤና አገልግሎቶችን ያለገደብ ለማዳረስ እንዲሰሩ እተጋለሁ ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት እና ሌሎች ታዳጊ ሀገሮች ከዓለም ጤና ድርጅት የበለጠ ድጋፍ ይሻሉ፤ ትኩረትም ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት ተመራጩ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር።

ዶክተር ቴድሮስ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት እንደገለጹት ሁሉ የአፍሪካም ሆነ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ከዓለም ጤና ድርጅት የሚደረግላቸው ድጋፍ ከሌሎች ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል።