NEWS

ዶክተር ቴድሮስ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጋር ተወያዩ

By Admin

May 11, 2017

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪና  የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አንዋር ቢን ሞሃመድ ጋርጋሽ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የኤሚሬቶቹ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

ዶክተር ቴድሮስ ከኢፌዴሪ መንግስት ለፕሬዝዳንት ሼክ ከሊፋ ቢን ዛይድ አል ናሂያን እንዲሁም  ለምክትላቸውና ለዱባዩ ሀገረገዥ ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ  የተላኩ ሁለት ደብዳቤዎችን ለሚኒስትር ዴኤታው አስረክበዋል፡፡

ደብዳቤዎቹ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከማጠናከር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን  ስለማካተታቸውም የዜና ወኪሉ ጨምሮ አስነብቧል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከኢትዮጵያ የመካከለኛው ምስራቅ የንግድ አጋሮች የሁለተኝነት ደረጃን ይዛለች፡፡

እኤአ ከ2002 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ብቻ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ከ45.4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 809 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማሻቀቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከመጋቢት – ሀምሌ 2008 ዓ.ም በነበሩት አምስት ወራት ብቻ መሰረታቸውን በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ያደረጉ 20 ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸው ግንኙነቱ እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ነው፡፡