Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ገፅታችንና ተቀባይነታችን እየተቀየረ ነው!

0 976

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ገፅታችንና ተቀባይነታችን እየተቀየረ ነው!                                                                   

                                                  ቶሎሳ ኡርጌሳ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ የአፍሪካና የዓለም ሰላም መድን ናት። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በግጭት ሲታመሱ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመቁጠር የሚጠለሉባት ሆናለች። የአፍሪካም ድምፅ እየሆነች ነው። ምንም እንኳን አሁንም ይበልጥ መጠናከር የሚገባቸው ግዳዩች ቢኖሩም፤ ሀገሪቱ በኢፌዴሪ መንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ባለፉት 26 ዓመታት በገፅታ ግንባታ ስራዎች ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዛለች። ይህም መንግስት ሀገሪቱን ለመምራት የቀየሳቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷ እንዲጨምር እያደረጉ መምጣታቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል።

ለዚህ አባባሌ በአስረጅነት ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቻይናንና እንግሊዝን ጨምሮ በበርካታ ሀገራትን በመጎብኘት ስምምነት ማድረጋቸውን መጥቀስ ይቻላል። አባባሌን ይበልጥ ለማጠንከርም በቅርብ ጊዜያት ብቻ የኳታር፣ የእንግሊዝ፣ የሶማሊያ፣ የፖላንድ፣ የሲንጋፖር…ወዘተ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ከሀገራችን ጋር ጠንካራ ግንኙነት መስርተው በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን ማውሳት የሚቻል ይመስለኛል።

ከአሜሪካ ጋር ያለን ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነትም የሞቀና በጠንካራ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሞኑን ‘ለግንቦት 20 የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ’ በማለት ካስተላለፈው መረጃ ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም። እንዲሁም የዋሽንግተን አስተዳደር ከእኛ ጋር በሰላም፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና መሰል ጉዳዩች እንዲሁም በሽብርተኝነት ዙሪያ አብሮ የመስራት ፍላጎት ያለው መሆኑን ማስታወቁ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ጥልቀት የሚያሳይ ይመስለኛል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ከቻይና ጋር የተፈጠረውና በስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመስራት የተደረሰው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የቀየ የግንኙነት ደርዝ ከፍ የሚያደርገው ነው። በተለይም ኢትዮጵያ የኢስያ ኢንቨስትመንት ባንክ አባል መሆን መቻሏ ሀገራችን በክፍለ-አህጉሩ ያላትን አመኔታና ተደማጭነት የሚያረጋግጥ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር ጠንካራ ትስስር ያላት ሀገር ሆናለች።

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረትና ከእንግሊዝ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነትም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። ምንም እንኳን የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በቅርቡ በአንዳንድ የፓርላማው አባላት የተሳሳተ መረጃ ተገፋፍቶ በሀገራችን ላይ መግለጫ ቢያወጣም፤ ይህ ጊዜያዊ መግለጫ ከህብረቱ አባል ሀገራት ጋር ለአያሌ ዓመታት የተገነባውን ጠንካራ ትስስር የሚያበላሸው አይደለም።

እናም ሀገራችን ከህብረቱ ጋር ያላት ስደተኞችን በመቀበልና በፀረ-ሽብርተኝነት እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት ጉዳዩች ዙሪያ አብራ እየሰራች ነው። ከህብረቱ ከወጣችው እንግሊዝ ጋርም ለረጅም ጊዜያት የዘለቀ ጠንካራ፣ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ግንኙነትን መስርታለች። በሁለቱ ሀገራትና ህዝቦች መካከል ያለው ይህ ግንኙነት ዛሬም ድረስ ያለ አንዳች ሳንካ የቀጠለ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ የሰላም ጠባቂ ብቻ ሳትሆን፤ ከቀጣናውና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች። በዚህም ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ የአፍሪካ ድምፅ ሆና በየቦታው ውክልና እያገኘች ነው።

እነዚህ ጥቅል እውነታዎች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በተጨማሪ ከምዕራቡም ይሁን ከምስራቁ ሀገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ታላላቅ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላት ትስስሮች ጠንካራና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ፤ የሀገራችን ገፅታ እየተለወጠ መሄዱንና በዲፕሎማሲው ረገድም ተፈላጊ እየሆነች መምጣቷን የሚያረጋግጡ ይመስለኛል።    

ታዲያ ይህ የተፈላጊነት ደረጃዋ ከምንም ተነስቶ የተገኘ አይደለም። ምዕራባዊያንም ይሁኑ ምስራቃዊያን እንዲሁም የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ከእኛ ጋር ተቀራርበው ለመስራት የሚፈልጉት የስጋ ዘመዶቻቸው ስለሆንን አለመሆኑን መረዳት የሚገባ ይመስለኛል። አዎ! ሀገራቱና ተቋማቱ እኛን የሚፈልጉንና አብረናቸው እንድንሰራ የሚሹት ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም። ርግጥም እነርሱ ይህ ሀገርና ህዝብ ባለተስፋ መሆናቸው ይገነዘባሉ። ዛሬ እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ ሁሉንም ዜጎች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ፣ ልማቱ ከተሳለጠም ከኢትዮጵያ ህዝቦች ባሻገር ለቀጣናውና ለአፍሪካ ህዝቦች ፋና ወጊ እንደሚሆን ያውቃሉ። በልማቱ ሳቢያ እነርሱም በንግድና በኢንቨስትመንት ሊሳተፉ እንደሚችሉም ይገነዘባሉ። ይህ “የነገ ማንነታችንም” ዓለም ባንክን፣ የዓለም የገንዘብ ተቋምን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክንና የኢስያ ባንክን እንደሳባቸው በእርግጥኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። እናም ከዚህ የነገ ባለ ተስፋና ባለራዕይ ህዝብና ሀገር ጋር ተቀራርበው መስራት የማይሻ ሀገርም ይሁን ዓለም አቀፍ ተቋም ሊኖር የሚችል አይመስለኝም።

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በአፍሪካ ስትራቴጂክ የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን ያውቃሉ። ሽብርን ሀገሩ ውስጥ አምርቶ ወደ ጎረቤቶቹ ከሚያከፋፍለው ከኤርትራ መንግስት በስተቀር፤ ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር በዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ቁርኝትና ተሰሚነትን ያውቃሉ። ሀገራችን የጎረቤቶቿን ሰላም በማስከበርና ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ እንዳለች ይገነዘባሉ።

ሀገራችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ ተባብሮ ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑን ይረዳሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን የፖለቲካ መናኽሪያ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ በህብረቱ ወሳኝ ጉዳዩች ውስጥ ያላት አዎንታዊ ሚና እና ተሰሚነት በጋራ ለመስራት ከሚፈልጉት አካላት የተሰወረ አይመስለኝም። ታዲያ ይህን መሰል ተሰሚነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካለው ሀገር ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ተግባርን አብሮ ለማከናወን የማይፈልግ ሀገር ማነው?—ማንም።

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ገፅታዋን ለመገንባቷ እንዲሁም ተቀባይነቷን ለማጎልበቷ ዋነኛው ምክንያት ላለፉት 26 ዓመታት በሀገር ውስጥ የተሰራው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች ነው። አዎ! በእነዚህ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው አስተማማኝ ሰላም፣ የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንዲሁም ስር በመስደድ ላይ የሚገኝ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አሁን ለተገኘው የገፅታችንና የተቀባይነታችን ማደግ ምክንያት ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ስትከተለው የመጣችው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የትኛውንም ሀገር በጠላትነት የማይፈርጅና በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት አብሮ ማደግን መሰረት ማድረጉ ለገፅታችንና ለተቀባይነታችን መለወጥ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ርግጥ ኢትዮጵያ በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ከየትኛውም ሀገር ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ እንዲመሰረት ማድረጓ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የውስጥ ችግርን መፍታትና በዚያውም ልክ የውጭ ተቀባይነታችንን መለወጥ ይቻላል ብላ ማመኗ ለዛሬው ዓለም አቀፍ ተቀባይነታችን መሰረት ጥሏል። በተለይም የመንግስትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በህዝቡ እንዲደገፉና ሁሉን አቀፍ ርብርብ በማድረግ እያንዳንዱን ዜጋ ማሳተፍ መቻሉ ለውጤቱ መገኘት ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢፌዴሪ መንግስት ለገፅታ ግንባታችንና ለተቀባይነታችን መለወጥ የመሪነት ሚናውን በመወጣቱ ሊመሰገን ይገባል። ሆኖም የዲፕሎማሲ ስራ በሂደት እያደገ የሚገለብት መስክ በመሆኑ አሁን ከተገኘው የዲፕሎማሲ ማማ በላቀ ደረጃ ከፍ ማለት ያስፈልጋል። ተቀባይነት አንድ ቦታ ላይ የሚቆይ ባለመሆኑም፤ በማንኛውም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ (Time, Place and Condition) ተከታታይ ጥረትና ህዝባዊ ድጋፍ ሊታከልበት ይገባል። እናም በመንግስትና በህዝብ ጥረት ዛሬ ላይ የተገኘውን የተቀባይነት ደረጃ ሁሉም በየፊናው ሊረባረብ ይገባል። ታዲያ ይህን ለማድረግ መንግስትም ይሁን እያንዳንዱ ዜጋ በተገቢው ቦታ አስፈላጊውን ተግባራዊ ጥረት ተጨባጭነት ባለው መልኩ መከወን ይኖርባቸዋል እላለሁ።

 

     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy