Artcles

ግንቦት 20 በብዝሃነት የደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን መሰረት ነው!!

By Admin

May 22, 2017

ግንቦት 20 በብዝሃነት የደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን መሰረት ነው!!

ዮናስ

ግንቦት 20 ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያብብ ምክንያት የሆነ፤   በመላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልብ ልዩ ስፍራ የተሰጠው ቀን ነው፡፡ይህ ቀን ፋሺስታዊው የደርግ ስርዓት በህዝባዊ ጥያቄዎች በተመሰረተ የትጥቅ ትግል እንዳይመለስ የተደመሰሰበትና ከመቃብር የወረደበት ቀን ነው፡፡  

ከዚህ ሥርዓት በኋላ የነበሩት ዓመታት በህዝቡ ሰፊ ተሳትፎ የሚተገበሩና በህዝቡ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረቱ ትክክለኛ ፖሊሲዎች ተቀርፀው ተግባር ላይ የዋሉበትና በርካታ ውጤቶችም የተመዘገቡበት ነው፡፡ ይህም የሆነው ግንቦት 20 1983ን ተከትሎ ከ1987ቱ የኢፌዴሪ ህገመንግሰት መጽደቅ በኋላ ነው፡፡በነገራችን ላይ ግንቦት 20 ወለድ የሆነው ስርዓት ከቀደሙት ስርአቶች ጋር ሲነጻጸር የማይዋጥላቸው ወገኖች ቢኖሩም ስለምን ? ሲባሉ ምክንያት አያቀርቡም ። ምክንያት በሌለውና ባልቀረበበት ጉዳይ ላይ መሟገት ተገቢም ምክንያታዊም ስለማይሆን በብዝሃነት ለደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ምንጭ ወደ ሆነው ግንቦት 20 እናምራ።

የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገመንግስቱ የሌሎች ህጎች መሰረትና ምንጭ ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ሰብአዊ መብቶች ከአምስቱ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎች አንዱ ነው፡፡ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፋፉ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ ከህገመንግስቱ 3 እጁ ወይም ከ106 አንቀጾቹ 36ቱ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ስለሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነፃነቶች ጥበቃና ዕውቅና የሚደነግጉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለምአቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ አካል መሆናቸው፣ የመሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ትርጉምም ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው አለምዓቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግጋት፣ ስምምነቶችና አለምዓቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችና መርሆዎች በተጣጣመ መልኩ የሚተረጎሙ መሆኑን ህገመንግስቱ ያስቀምጣል፡፡ ህገ መንግስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ለሆነው የሰብአዊ መብቶች መከበር ዋስትና ነው፡፡ የሰብአዊ መብቶች መከበርና ጥበቃ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ካለው ፈጣን ልማት ጋር ተሳስሮ የሚታይ ነው፡፡

በግንቦት 20 ድል የተገኘው ህገ መንግስት ካመጣው ውጤት አንዱ ሰዎች በፈለጋቸው ህጋዊ አመለካከት ዙሪያ ተደራጅተው በፖለቲካ  እንዲሳተፉ እድል መስጠቱ ነው፡፡ ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ እንዲወጣና ከተሃድሶው ወዲህም እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመዘጋገብ፣ መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ስለሚሰጥበት አሰራር፣ በፖለቲካ ፓርቲነት ስለሚመዘገቡ አካላት ህግ ማርቀቅና ማጽደቅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህግን መሰረት አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል፣ የመሳሰሉት ዴሞክራሲያዊ አሰራርን ከመዘርጋት እና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በአስተማማኝ መልኩ ለመገንባት እንዲቻል አሁን እየተደረገ ያለው የፓርቲዎች ውይይትም ሳይቀር ምንጫቸው ግንቦት 20 ነው።

የመረጃ ነጻነት ተግባራዊነት ለዜጎች መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ለሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ መሰረት ነው፡፡ የሰዎች የመናገርና ሃሳብን የመግለጽ መብት የሰዎችን መረጃ የመፈለግ፣ የማግኘት፣ የማደራጀትና የማስተላለፍ መብትን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በሌሉበት ዜጎች መብታቸውን በትክክል ሊጠቀሙ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥሰትን ሊያጋልጡ አይችሉም፡፡ ከዚህ ሌላ የመረጃ ነጻነት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ካለው ቁልፍ ሚና አንጻር መረጃን ለህዝብ ፍፁም ተደራሽ ማድረግ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ እሙን ነው፡፡ መረጃ ያለው ህብረተስብ በመንግስት አሰራር ላይ ግልጽ ግንዛቤ ስለሚኖረው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎው ይጎለብታል፡፡ ሙስናና በስልጣን አለግባብ የመጠቀም ብልሹ አሰራርን የሚያጋልጥ ኃይል ይሆናል፡፡ የመንግስት አሰራር ግልጽነት ከጎደለው ግን የህዝብ ተጠያቂነት የሌለው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ይነግሳል፡፡ በመንግስት አሰራር ላይም ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚመቹ መደላድሎች ይበረክታሉ፡፡

መረጃ ያለው ዜጋ በካርዱ  በሰጠው  የስልጣን ውክልና የሰጠው አካል ተግባርና ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን መከታተል ይችላል፡፡ መረጃ ያለው ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ጥቅሙን የሚያስከብሩ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች እንዲወጡና እንዲፈፀሙ ግፊት ማድረግ ይችላል፡፡ በህገ-መንግስቱ የሰፈረው የዜጎች የመናገርና ሃሳብን የመግለጽ መብት ከመረጃ ነጻነት ውጭ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡

በሀገራችንም በመረጃ ነጻነት ስርአቱ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን አስወግዶ ጤናማና ገንቢ ሚና ለሚጫወት የመረጃ ልውውጥ ስርአት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ህጋዊና ተቋማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ግንቦት 20 ነው፡፡ የግንቦት 20 ድል ውጤት በሆነው የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 ማንኛውም አይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶች ተቀምጠዋል፡፡  ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱር መወገዱም ተመልክቷል፡፡ በዚህም  ባሳለፍናቸው 26 አመታት በየአምስት አመቱ የተደረጉ 5 ሃገር አቀፍ ምርጫዎችን ማከናወን ተችሏል ።

በአንድ አገር የተረጋጋ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን የሚቻለው ፓርቲዎች በሚገነባው ሥርዓት መሰረታዊ ባህሪያት በተለይም በህገ መንግሥቱ ይዘት ላይ ተስማምተው  ሲያድሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ሰላማዊና በነፃ ውድድር ላይ የተመሰረተ ወይም ደግሞ በመጠፋፋት  እና ግጭት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ የተረጋጋ ወይም በሁከት የሚናጥና ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን የማድረግ ውጤት የሚያስከትል ነው፡፡

በአንድ በኩል ህገመንግሥታዊ ስርዓቱ ትክክለኛ በመሆኑ መቀጠል አለበት የሚሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ በውድም በግድም መፍረስ አለበት የሚሉ ፈፅሞ የማይቀራረቡ አቋሞችን የያዙ ፓርቲዎች በሚኖሩበት አገር የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም፡፡በአንፃሩ ሁሉም ፓርቲዎች ህገመንግሥታዊ ስርአቱን ተቀበለው በፖሊስና ስትራቴጂ ደረጃ የሚታዩ የአማራጭ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚገልፁበት ሥርዓት ደግሞ በተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና በሃገሮች ሰላማዊ ውስጣዊ ጉዞ እጅግ የተመቸ ሁኔታን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች  በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የላቀ ሚና መጫወት እንደሚችሉ እና መጫወትም እንደሚገባቸው  ግንቦት 20 ወለድ የሆነው ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ከመናገር አልፎ ለተግባራዊነቱ ያለ የሌለ አቅሙን ተጥቅሞ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የአንድን የህብረተሰብ ክፍል መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጭ ሃሳቦችን በማመንጨት፣ እነዚህ ሃሳቦች በህብረተሰብ ክፍሉም ሆነ በአጠቃላይ በህዝቡ ተቀባይነት እንዲያገኙ በመጣር፣ ሃሳቦቹ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ተግባራዊ እንዲሆኑ ግንቦት 20 መሰረቱን ጥሏል።እነዚህ ፓርቲዎች ከፍተኛ የአመራር ሚና መጫወት እንደሚችሉ እና በዚህ መልኩ የተደራጀ አመራር ሰጥተው የህዝብን ድጋፍ ካገኙ የመንግስት ሥልጣንን ይዘው ሃሳባቸውን ተግባራዊ በማድረግ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉበትን መደላድል፤ በሌላ አነጋገር በብዝሃነት ለደመቀው የዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት የሆነው ግንቦት 20 ነው።  

ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመጫወት የሚችሉት አመለካከታቸው፣ እምነታቸውና አሠራራቸው ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ነው ።የውስጥ አሰራሩ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትና ማበብ ፋይዳ ያለው አስተዋፅኦ ማበርከት አይችልም ሲል አፅንኦት በመስጠት በብዝሃነት ስለደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረቱን ያጸናል።  

በብዝሃነት ለደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት በሆነው ግንቦት 20 የተዘረጋው የፌዴራል ሥርዓት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ፣ ባህሎቻቸውን እና ቋንቋዎቻቸውን ማሳደግ ፣ ወደውና ፈቅደው ኢትዮጵያዊ ማንነትን መቀበል የሚያስችል የቡድን ማንነትን የተቀበለና ያከበረ ነው።ስለሆነም የቡድን እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ማስተናገድ እንዲችል ሆኖ የተዋቀረ የፌደራል ስርአት በመሆኑ ጭቆና ወይም እድልዎ ዳግም መፈጠር የማይቻልበት ሁኔታን ፈጥሯል።የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ በህዝቦች መካከል በመተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት እንዲጎለብት አድርጓል።ግንቦት 20ን መሰረት ያደረገው የፌዴራል ስርዓት በህዝቦች መካከል መተማመን የፈጠረ በመሆኑ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን አስፍኗል። ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በአገሪቱ ማስፈን በመቻሉ ህዝቦች አካባቢያቸውን እንዲያለሙ መልካም አጋጣሚዎችን ፈጥሯል።የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር በመቻላቸውና አካባቢያቸውን ማልማት በመቻላቸው  በአገሪቱ በሁሉም አካባቢ ፈጣን ዕድገት በመመዝገብ ላይ ነው። ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የማይባል መሠረተ ልማት ያልነበራቸው አርብቶ አደር አካባቢዎች  የተሟላ መሠረተ ልማት ማግኘት መቻላቸው አንዱ የፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ማሳያና በብዝሃነት ለደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት ለሆነው ግንቦት 20 ውጤታማነቱ ማሳያ ነው። በማህበራዊ መገልገያዎች ማስፋፋት ረገድም ባለፉት 26 ዓመታት ትልቅ ዕመርታ ተመዝግቧል። የትምህርት ሽፋንና የጤና አገልግሎት መስፋፋት በመቻላቸው አገራችን የተባበሩት መንግስታትን የልማት ግቦች ማሳካት ከቻሉ ጥቂት የአፍሪካ አገራት መካከል መመደብ ችላለች። በድርቅና ረሃብ ትታወቅ የነበረች አገር አሁን ላይ ለጎረቤት አገራት ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ አገራት ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ አገር ለመሆን መብቃቷም በብዝሃነት ለደመቀው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት የሆነው ግንቦት 20 ለዚህች ሃገር ያለውን ታሪካዊ ፋይዳ የሚያረጋግጥ ነው።መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ ባለፉት 26 ዓመታት በመንገድ ግንባታ፣ በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ /አገር አቋራጭና የከተማ ባቡር ልማት/ የተመዘገበው ስኬት፤ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በኢኮኖሚ ጥቅም ለማስተሳሰር በአውራ መንገዶች ግንባታ፣ በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ በአየር ትራንስፖርት ማስፋፋት ወዘተ እያደረገችው ያለው ስኬታማ ጉዞ ሁሉ መሰረቱ ግንቦት 20 ነው። የግንቦት 20 ነገር ታሪክና ውጤቱ ብዙ ነው ለመዘከር ያህል ግን መሰረታዊ የሆኑቱ እኒህ ናቸው።ሌላው ደግሞ በቀጣዩ የግንቦት ገጽ መተረኩ አይቀሬ ነውና እዚህ ይብቃን።