Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግንቦት 20-የመብቶች ሁሉ መሰረት

0 364

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግንቦት 20-የመብቶች ሁሉ መሰረት

ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ ህዝቦች በግንቦት 20 ያልተጎናፀፏቸው መብቶች የሉም፡፡ የሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ከእነዚህ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለመብቶቹ መረጋገጥ የበርካታ ህዝብ ልጆች ህየወት አልፏል። አካል ጎድሏል። ንብረትም ወድሟል፡፡ የሀገራችን ህዝቦች አምባገነናዊ ስርዓቱን ለመጣል ባደረጉት ትግል የመብቶቹ ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡ በዚህ ፅሑፍም ከመብቶቹ አንዱ የሆነውን የሃይማኖት እኩልነትንና የእምነት ነፃነትን እንመለከታለን፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተለያዩ ገዥዎች ይደርስባቸው የነበረውን የሃይማኖትና የእምነት ጭቆናና መድሎ በማስወገድ በእኩልነትና በመቻቻል የመኖር ራዕያቸውን ለማሳካት ባካሄዱት ህዝባዊ ትግል አዲሲቷ ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ችለዋል፡፡  የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት የግልና የቡድን መብቶችን የሚያስከብር በመሆኑ የሃይማኖት ጉዳይ በዚሁ አግባብ ምላሽ ማግኘት ችሏል፡፡ እናም  በህገ-መንግስቱ ስፍረው የሚገኙት ሦስቱ መርሆዎች ማለትም የእምነት ነጻነት፣ የሃይማኖት እኩልነትና የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ማደግና ማበብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

በመሆኑም ዛሬ በሀገራችን መንግስታዊ ሃይማኖት የለም። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ማንኛውም ግለሰብ የመረጠውን ሃይማኖትና እምነት የመያዝና የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የማምለክ፣ የመከተል፣ የማስፋፋት መብቱም በይፋ ተረጋግጧል፡፡

በዚህም ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩበት፣ የመንግስታዊ ሃይማኖት አመለካከት የከሰመበት ሁኔታን ዜጎች የቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው ህገ – መንግስታቸው አማካኝነት የሃይማኖት እኩልነትን ያስከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመቻላቸው፤ የሃይማኖት ብዝሃነትን ማስተናገድ የምትችል አዲሲቷ ኢትዮጵያን ማየት ተችሏል፡፡  እናም ሀገራችን በእኩልነትና በመቻቻል ባህል የሃይማኖት ብዝሃነት የሚስተናገድባት ሀገር በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ማትረፍ ችላለች፡፡

በእርግጥ በአይናቸው ያዩትንና በጆሯቸው የሰሙት ማመን የሚያዳግታቸው የከሰሩ ፖለቲከኞች በሀገራችን ውስጥ ያለውን ሃይማኖታዊ እውነታ ጠንቅቀው የሚያውቁት ቢሆንም፤ ለድብቅ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ስልትነት ከመረጡት አንዱ የሃይማኖት ጭምብልን ማጥለቅ በመሆኑ ሃቁ ሊዋጥላቸው እንደማይችል እሙን ነው— ከተግባራቸው ማረጋገጥ የተቻለ ኑባሬ ነውና፡፡ በመሠረቱ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሃይማኖት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡

የሃይማኖት እኩልነት በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሲካሄድ የነበረው የከሰሩ ፖለቲከኞች እንቅስቃሴ ፋይዳ ቢስ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም፤ ጥረታቸው ግን ሳይወሳ በቀላሉ መታለፍ ያለበት አይመስለኝም፡፡ በሃይማኖት ሽፋን የኪራይ ሰብሳቢነት ሱሳቸውን ለማስታገስ የሚራወጡት እነዚህ ሃይሎች በሀገራዊው የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን የሚፈታተኑ ሙከራዎች ያካሄዱበት ሁኔታን ማስታወሱ ተገቢነቱ የላቀ ነው። እናም ትናንትን በዛሬ መነፅር መመልከት ለንፅፅር የሚረዳ ይመስለኛል፡፡

መቼም እነዚህ ሃይሎች ለፖለቲካ ንግድ ፍጆታነት የሚውል ዘዴን መቀየስ የዘወትር ተግባራቸው በመሆኑ የከሰሩ ፖለቲከኞቹ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በሽፋንነት የሚጠቀሙበት በዋነኝነት በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች አማካኝነት ነው፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንድ ሀገር አንድ ጥምቀት” በሚል ቅኝት ያረጀ አስተሳሰብን የሰነቀና የትናንቱን ዓለም የሚናፍቅ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ቀደም ሲል በመንግስታዊ ሃይማኖትነት የበላይነትን ተጎናጽፎ የቆየው የኦርቶዶክስ እምነት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ የሚካሄድ ትግል እንደሆነ በማስመሰል የእምነቱ ተከታዮችን በማደናገር ሁከትና ብጥብጥን የማንገስ ዓላማን የሰነቀ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦርቶዶክስ እምነት የበላይነት የሚያምኑና እምነቱ ከሌሎች ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚታይና የሚከበር መሆኑን ያልተቀበሉ አንዳንድ ወገኖች ዛሬ ላይ ሆነው ትናንትን እንደሚያማትሩ በተግባር በመስተዋሉ ነው፡፡

እንደሚታወቀው መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ መግባትን በኢፌዴሪ ህገ- መንግስት አንቀፅ አስራ አንድ የተደነገገ ከመሆኑም በላይ፤ ለተግባራዊነቱም መንግስት ጠንካራ አቋምን አራምዷል። ሆኖም እነዚህ ሃይሎች የተለያዩ አጀንዳዎችን ቀርጸው መንግስትን የሚወነጅሉት ለክርስትና እምነት ክብር ስላላቸውና ተቆርቋሪ ሆነው ሳይሆን የሃይማኖትን ጭምብል አጥልቀው የፖለቲካ ንግድን ለማጧጧፍ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት መሆኑን ለመገንዘብ የሚከብድ አይመስለኝም፡፡

የከሰሩ ፖለቲከኞች ሌላኛው ዘዴ በእስልምና ሽፋን የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባለፉት ጨቋኝ ሥርዓቶች ከፍተኛ የሃይማኖትና የእምነት በደል ሲደርስባቸው ቆይቷል፡፡ ይሁንና የዕምነቱ ተከታዮች ከሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በመሆን ዴሞክራሲያዊ ትግል በማካሄድ የሃይማኖትና የእምነት እኩልነት የሰፈነባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ መገንባት መቻላቸውም የትናንቱ ትውስታችን ነው፡፡

እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሀገሪቱ በተረጋገጠው የሃይማኖት እኩልነት ላይ በመመስረት ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በእኩልነትና በመቻቻል በሚኖሩበት በአሁኑ ወቅት፤ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ይህን ሃቅ አለመገንዘባቸው አሊያም ለማወቅ አለመፈለጋቸው ነው፡፡    

በርግጥ በእስልምናና በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የሰፈነውን የመከባበርና የመቻቻል ባህል ለማደፍረስ የሚደረገው ጥረት የዓመታት ዕድሜን ከማስቆጠሩም በላይ፤ ለውጤት መብቃት የተሳነው መሆኑን ከድርጊቶቹ በመነሳት ድምዳሜ ላይ ለመድረሱ አዳጋች አይሆንም፡፡ እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ካካተታቸው መሰረታዊ መርሆዎች መካከል በሃይማኖቶች መካከል የማበላለጥና የልዩነት ሥራ መስራት ከፍተኛ የመብት ጥሰት ነው፡፡

የሃይማኖት እኩልነት አማራጭ የሌለው የዴሞክራሲ ጉዳይ መሆኑን ካለፉት ሥርዓቶች አካሄድና የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ መማር እየተቻለ ሃይማኖትን ለፖለቲካ ትርፍ ማስገኛነት መጠቀሙ እነዚህ ሃይሎች ምን ያህል የህልም ቅዥት በሆነ ቀቢፀ-ተስፋ ውስጥ እንደሚገኙ ያመላክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከሰሩ ፖለቲከኞች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ክፍፍል በመፍጠር አንዱን “ትክክለኛ” ሌላውን ደግሞ “ትክክለኛ ያልሆነ” የሚሉ ታፔላዎችን እየለጠፉ በተለይም የሱፊ አስተሳሰብን በሚከተለው ወገኖች ላይ ጥቃት ለማድረስ መንቀሳቀሳቸው የኪሳራቸው ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል፡፡ ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ውድመትም መፈፀማቸውም እንዲሁ፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ የአሸባሪዎች መጠለያም ሆኖ ነበር። በተለይም የአሸባሪውን ግንቦት ሰባት በየአጀንዳው እየተንጠላጠለ የምኞት ዓለም ሁከት ናፋቂነት ረብ የለሽ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች በግንቦት 20 መሰረትነት እውን የሆነ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዓይነት ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ ችግሮቹ ግን የግንቦት 20ን ድል ሊቀለብሱ የሚችሉ አይደሉም። እናም መሰረቱ የህዝቦች ትግል የሆነን መብት መቀልበስ ስለማይችል በዕለቱ የተገኙት ድሎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy