NEWS

ግዙፉ ጄነራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

By Admin

May 18, 2017

በዓለም ግዙፉ የዲጂታል ኢንዱስትሪ ኩባንያ የሆነው ጄነራል ኤሌክትሪክ ትናንት በአዲስ አበባ ቢሮውን ከፍቷል።

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ በአፍሪካ የጄነራል ኤሌክትሪክ ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚ ጃይ አየርላንድ እና በኢትዮጵያ የጄኔራል ኤሌክትሪክ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ሃይሉ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ የጄነራል ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ ቢሮውን መክፈት፥ መንግስት ምቹ የቢዝነስ አካባቢን ለመፍጠርና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት አንድ ማሳያ ነው።

ይህም ጥረት መንግስት ሀገሪቱ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዛቸው አገራዊ ግብ አካል ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ጄነራል ኤሌክትሪክ የአፍርካ የኢንቨስትመንት አጋርነቱን ለማጠናከር በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ 33 ሀገራት 2 ሺህ 600 ሰራተኞችን ይዞ እየሰራ ነው።

በዚህ እንቅስቃሴውም ኩባንያው በ2016 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝቷል።

በኢትዮጵያ አዲስ በተከፈተው ቢሮው አማካኝነትም በሀገሪቱ ካሉ የግል ዘርፎች እና ኢንተርፕራይዞች ጋር በመቀናጀት የቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግር ስራን ያከናውናል ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ የጀኔራል ኤሌክትሪክ ስራ አስፈጻሚው አቶ ዳንኤል ሃይሉ፥ ኩባንያው በኢትዮጵያ ስራውን ከጀመረ ዘጠኝ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፥ የሰው ሃይሉን በማጠናከር ሀገሪቱ በሃይል፣ በትራንስፖርት እና በጤናው መስክ ስኬት ለማስመዝገብ በምትሰራው ስራ የበኩላችንን ለማበርከት እንሰራለን ነው ያሉት።