Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጠባብ ብሔርተኝነት እንደ አሳሳቢ አደጋ!

0 357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ጠባብ ብሔርተኝነት እንደ አሳሳቢ አደጋ!
ሰለሞን ሽፈራው
በኢህአዴግና በአብዛኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚስተዋለው መካረር ለየትኛውም ወገን የሚበጅ ድምር ውጤት ይኖረዋል ተብሎ አይታመንም፡፡ እናም ከዚሁ የተነሳ ነው ብዙውን ጊዜ ህዝቡ ፓርቲዎቹ አላስፈላጊ ፍጥጫቸውን አቁመው በመወያየት ችግራቸውን እንዲፈታ የሚያሳስብ ምክሩን ሲለግስ የሚደመጠው፡፡ ስለሆነም፤ የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ከያዝነው የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ዋና ዋና የስራ ዕቅዶቹ አንዱ በኢህአዴግና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መቀራረብን ለመፍጠር ያለመ ሀገር አቀፋዊ የውይይት መርሐ-ግብርን ማስፈፀም እንደሚሆን ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ፤ ጉዳዩን በጉጉት ስሜት ከመከታተል ያልቦዘንን ዜጎች ጥቂት አይደለንም ማለት ይቻላል፡፡
በእርግጥም ደግሞ የዚች አገር ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት አለመቃናት ጉዳይ ያሳስበኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ፤ በገዥውና በተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚስተዋለውን አላስፈላጊ የአመለካከት ገመድ ጉተታ የሚያስቀር መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል መሰል የውይይት መድረክ መከፈቱን በጉጉት ስሜት ቢከታተለው የሚገርም አይሆንም፡፡ ስለዚህ እኔም ከ20 በላይ የሚሆኑ ሕጋዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ተቀራርበው ለመወያየትና ለመደራደርም ጭምር የሚችሉበት መርሐ-ግብር መነደፉን የሚያወሳው መልካም ዜና ከተደመጠ ጀምሮ፤ ጉዳዩን በተስፋ ስሜት ከመከታተል ቦዝኘ እንደማላውቅ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡
እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ የማልፈውም፤ለመሆኑ ግን፤ ከተጀመረ ወራትን ያስቆጠረው የኢህአዴግና የተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካዊ ውይይት፤ አልያም ደግሞ ድርድር ሂደት ለሀገራችን ህዝቦች የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት አለመቃናት ስለሚኖረው ፋይዳ በቅጡ የምንገነዘብ ስንቶቻችን ነን? የሚል ጥያቄ አንስቼ ምላሽ ይሆናሉ በምላቸው አንዳንድ ተያያዥ ነጥቦች ላይ የራሴን ትዝብት አዘል አስተያየት ለመሰንዘር ወደምሞክርበት ሃሳብ ነው፡፡ እናም ከዚህ አኳያ በቅድሚያ መነሳት የሚኖርበት ቁልፍ ነጥብ ሆኖ የሚሰማኝ፤ የሀገራችንን አጠቃላይ ችግሮች እንዲባባሱ በማድረግ ረገድ የማይናቅ አሉታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ከሚታመንባቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰደው፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ በመባል የሚታወቅ ፓርቲ ከውይይቱ ሂደት ራሱን ያገለለበት ምክንያት ነው፡፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፤ እኔን ራሴን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ዜጎች አስቀድመን የገመትነውና የኋላ ኋላ ሲሆን የተስተዋለው የፓርቲዎች ውይይት መድረክ ሂደት ተጨባጭ እውነታ፤ ምን ያህል የስሌት ስህተት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንደነበረን የሚያመለክት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ በአንፃራዊ መልኩ ለዘብ ያለ አቋም የሚያራምዱ ተደርገው ከሚወሰዱት የተቃውሞው ጎራ አንጋፋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት መድረክ፤ ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎቹ የውይይት ወይም የድርድር ሂደት ራሱን እስከማግለል የደረሰባቸውን ጥቃቅን የቅድመ ሁኔታ ጥያቄዎች እያነሳ ዕክል ለመፍጠር ሲሞክር የተስተዋለበት አግባብ የሚጠበቅ አልነበረምና ነው፡፡ በእርግጥ የበርካታ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ እንደሆነ የሚነገርለት መድረኩ፤ ይሄን አፈንጋጭ አቋም የወሰደው ፕሬዚዳንቱ ፕሮፌሰር በየነ ስለፈለጉ እንዳልሆነ የሚናገሩ ታዛቢዎች አሉ፡፡
እናም እነዚሁ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚያስረዱት ከሆነ፤ ፕሮፌሰሩ የአሁኑን ያልተለመደ ዓይነት ግትር አቋም ይዘው እንዲገኙ የተገደዱበት ዋነኛ ምክንያት ወዲህ ነው፡፡ ማለትም፤ የመድረኩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር መረራ ጉዲና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገጉ ሕጎችን ጥሰው ስለተገኙና በሌሎችም የሽብር ተግባራት ተሳትፎ እንደነበራቸው ተጠርጥረው ከመታሰራቸው ጋር በተያያዘ ምክንያት፤ በተለይም የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የሆኑ የመድረክ አባላት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በማያፈናፍን ተፅእኗቸው ስር እንዲወድቁ አድርገዋቸዋል የሚል አስተያየት የሚሰጡ ታዛቢዎች ጥቂት አይደለም፡፡
በተለይም ደግሞ፤ ባህር ማዶ እየኖሩ ኢትዮጵያን በህዝቦቿ የዕርስ በርስ ግጭት ሌላዋ ሶሪያ ሊያደርጓት የሚፈልጉት ፅንፈኞቹ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ መሪ ተዋናይ ዲያስፖራዎች “ዶክተር መረራን የመሳሰሉት የሰላማዊ ትግሉ ግንባር ቀደም መሪዎች በወያኔ ኢህአዴግ የአፈና ግብረ ሃይል ለእስር ተዳርገው ባሉበት ሁኔታ ደሞ የምን ውይይት ይኖራል? ፕሮፌሰሩ ዶክተር መራራን ሳያስፈታ በፓርቲዎቹ የድርድር ሒደት ለመቀጠል ከወሰነማ የለየለት ክህደት ነው!” ወዘተ የሚል ጠንካራ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙበት አግባብ ለመድረክ ፕሬዚዳንት በቀላሉ የማልፋት ፈተና ሳይሆንባቸው እንዳልቀረ ይታመናል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይትና የድርድር ሂደት ራሱን ለማግለሉ እንደሁነኛ ምክንያት እየተወሰደ ያለ ሰሞነኛ የህዝብ አስተያየት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሌላም የጉዳዩንም እውነትነት አምነን እንድንቀበል የሚያደርግ ተያያዥ ነጥብ ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም፤ ረቡዕ ሚያዚያ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “አራት የኦሮሞ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ድርድር የሚገኘውን ውጤት እንደማይቀበሉት አስታውቁ” በሚል ርዕስ የተዘገበውን ዜና ለአብነት ያህል ማስታወስ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ በሚያዝያ 18 ቀኑ የረቡዕ እትሙ ገፅ 3 ላይ የፃፈውን ዜና ማየት እንደሚቻለውም፤ የጋራ መግለጫውን ያወጡት አራት ፓርቲዎች፤ ኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦ.አ.ነ.ግ) የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦ.ነ.አ.ግ)፤ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦ.ብ.ኮ) እና እንዲሁም ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ (ኦ.ነ.ብ.ፓ) ናቸው፡፡ እነዚሁ ፓርቲዎች በሰጡት የጋራ መግለጫ እየተካሔደ ካለው የኢ.ህ.አ.ዴግና የበርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት አልያም ደግሞ ድርድር ላይ የሚገኘው ውጤት “ምንም ይሁን ምን እንደማይቀበሉት” በማሳወቅ ገና ከወዲሁ አቋም መውሰድን ለምን እንደመረጡ ብዙ የሚያነጋግር ሆኖ ነው ያገኘሁት እኔ በግሌ፡፡
ይህን ስልም ደግሞ፤ አራት በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች በሰጡት ሰሞነኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ኢህአዴግና ሌሎች ሀገር አቀፋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያካሄዱት ያለውን ውይይት ወይም ድርድር አስመልክተው ያቀረቡት ስሞታ እንብዛም ግልፅ አለመሆኑ ብቻም ሳይሆን፤ ስለሀገራዊ መግባባት አስፈላጊነት የሚያወሳውን አጀንዳ አብዝተው የፈሩት ጭምር ያስመስልባቸዋል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ሪፖርተር ጋዜጣ በፃፈው ሰሞነኛ ዜና ላይ ስማቸው የተጠቀሰው አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ እየተካሔደ ባለው የሀገር አቀፋዊ ፓርቲዎች ፖለቲካዊ የውይይትና የድርድር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ያልፈለጉት “የኦሮሞ ህዝብ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እንዲገለል እየተደረገ ነው” ብለው ስለሚያምኑ እደሆነ ቢገልፁም፤ አጠቃላይ ነገረ ስራቸው የሚያረጋግጥልን ጥሬ ሀቅ ግን፤ ቡድኖቹ የተሰሩበት የጠባብ ብሔርተኝት ፅንፈኛ አስተሳሰብ ጣራ እየነካ መምጣቱን ነው ብሎ ማጠቃለል ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
ከተጠቃሾቹ አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድች መካከል፤ ሶስቱ ለኦሮሞ ነፃነት የሚታገሉ መሆናቸውን ለመግለፅ ያለመ ስያሜያቸውን ምን ያህል በሚያስቅ ድግግሞሽ አመሳስለው እንደ ያዙት ልብ ለሚል ታዛቢ ጉዳዩ አንድ ሆነው ሳለ እንደ ሶስት መቆጠርን ለምን ፈለጉት? ማለቱ እንደማይቀርም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ እንዲያውም ስለዚሁ ጉዳይ ያነሳሁበት አንድ ወዳጄ “የኦሮሞ ህዝብ እኮ ኦ.ነ.ግ በአዲስ መልክ ስራ እንዲጀምር አልጠየቀም” ብሎ እንዳሳቀኝ ሳልነግራችሁ ማለፍ አይኖርብኝም፡፡
በእርግጥም ደግሞ እነዚህን ኦሮሞን ነፃ ስለማውጣት የሚያወሳውን ስያሜ በሚያስተዛዝብ መመሳሰል እየተኮራረጁ የተግባር ወይም ደግሞ የአቋም ልዩነት ሳይኖራቸው ብዙ መስለው ለመታየት ሲሞክሩ የሚስተዋሉ አዳዲስ ቡድኖች ከአንጋፋው የጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብ ፊታውራሪ (ከኦ.ነ.ግ) የሚለያቸው ምክንያት ምን እንደሆነ የምናውቅበት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህም እንደኔ እንደኔ ጉዳዩ፤ ለወትሮው በተለይም ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” እያለ ከሚጠራው ኦ.ነ.ግ ጋር ብቻ የሚያያዝ የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ችግር ተደርጎ ይቆጠር የነበረው የጠባብ ብሔርተኝት ፅንፈኛ አመለካት፤ አሁን አሁን እዚሁ አገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል ሽፋን የምርጫ ቦርድን ሕጋዊ ፍቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱትን ቡድኖችም ጭምር በደንብ የሚገልፃቸው አደገኛ አቋም ሆኖ እየተስተዋለ ነው የሚለው ነጥብ ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ለዚህ መከራከሪያ የተሻለ አብነት ሊሆነኝ ይችላ የምለውም ደግሞ፤ ከላይ በስም የተጠቀሱት አራት “ለኦሮሞ ነፃነት እንታገላን” የሚሉ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ቡድኖች፤ ኢህአዴግና ሌሎች አገር ቀፍ ፓርቲዎች የጀመሩትን ለብሔራዊ የጋራ መግባባት በር ይከፍታል ተብሎ የሚጠበቅ የውይይት (የድርድር) መድረክ ገና ከወዲሁ ለማጥላላት የሞከሩበት ሰሞነኛ መግለጫ ነው፡፡ እንዴት ቢባልም ተጠቃሾቹ አራት ጠባብ ብሔርተኛ ቡድኖች በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ፤ አንድም እንኳን መላውን የኢትዮጵያ ህዝች የሚመለከት ሀገራዊ ርዕሰ-ጉዳይ ካለማንሳታቸውም ባሻገር፤ ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ጥቅም መከበር የሚታገሉ መስለው ለመታየት የሞከሩበት አግባብም በራሱ ከተራ የኩርፊያ ስሜት የመነጨ ጎጠኝነትን ለማባባስ ሲባል የቀረበ ፕሮፖጋዳ እንጂ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃን አላጣቀሰምና ነው፡፡
ይልቁንም ደግሞ፤ ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ እስከ 2009 ዓ.ም መጀመሪያ፤ በአንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች አካባቢ ከተስተዋለው የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ጋር በተያያዘ መልኩ ስለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቋቋመው አጣሪ ቡድን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ሪፖርትም ጭምር እንደማይቀበሉት አራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገለፁበት አግባብ “በተለይም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ኮሚሽኑ ያቀረበው ግኝት ገለልተኝነት የጎደለው ስለሆነ” የሚል ሆኖ ማግኘቴ ይበልጥ አስገርሞኛል፡፡ ስለዚህም በኔ እምነት የሪፖርተር ጋዜጣው ሰሞነኛ ዜና ላይ የተመለከተውን የጋራ መግለጫ የሰጡት አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ያሳዩት አቋም፤ እኛ ትምክህተኝነት እያልን የምንነቅፈውን የአስተሳሰብ ፅንፍ ወክለው ከሚንቀሳቀሱት የተቃውሞው ጎራ ሃይሎችም በበለጠ መልኩ፤ ጠባብ ብሔርተኞቹ ወገኖች እንደ አሳሳቢ የስርዓቱ አደጋ ሊወሰዱ ይገባል የሚያሰኝ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡
በተለይም ደግሞ፤ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ያለመ ውይይት እያካሄዱ የሚገኙት ከ20 በላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ሊበረታታ የሚገባውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በጎ ጅምር ነው” ሲሉ የደገፉትን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑን ሪፖርት አራቱ ጠባብ ብሔርተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች “ኮሚሽነሩ ገለልተኛ አይደሉም” በሚል መሰረተ ቢስ ምክንያት እንደማይቀበሉት መግለፃቸው ብዙ የሚያስተዛዝብ አንድምታን ያዘለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም፤ ከሞላ ጎደል በዚህ መጣጥፍ ላይ የተነሱትን ነጥቦች መሰረት አድርገን የሀገራችንን ፖለቲካ ወቅታዊ የኃይል አሰላለፍ እንገምግመው ከተባለ፤ እነ ኦ.ነ.ግ. እና እነ ኦ.ብ.ነ.ግ የሚታወቁበትን የጠባብ ብሔርተኝነት ፅንፈኛ አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች፤ በኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ላይ አሳሳቢ አደጋ የሚጋርጥ እንቅስቃሴያቸውን ከማጧጧፍ እንደማይቦዝኑ የሚያረጋግጥ እውነታ ነው ያለው፡፡ ለማንኛውም ግን፤ የነውጠኝነትን መንገድ ለመረጡት ወገኖች ሁሉ ፈጣሪ ልቦና ይሰጣቸው ዘንድ እየተመኘሁ የዛሬውን ፅሁፌን እነሆ እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡ መዓሰላማት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy