Artcles

ፌደራላዊ ሥርአቱና የኢትዮጵያ አንድነት

By Admin

May 07, 2017

ፌደራላዊ ሥርአቱና የኢትዮጵያ አንድነት

ኢብሳ ነመራ

ከ40 ዓመታት በፊት ትምህርት የጀመርኩት በአንዲት 100 እንኳን የማይሞሉ ቤቶች ባሏት ትንሽ ከተማ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። ነዋሪዎቿ ከአንድ ሺህ የማይበልጡት ይህች ከተማ ከፖሊስ ጣቢያ፣ ፍርድ ቤትና አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጭ ምንም የመንግስት ተቋም የላትም። ከተማዋ ቢራና ለስላሳ መጠጦች የሚሸጡባቸው ሁለት ቡና ቤቶች፣ በርካታ ጠላና አረቄ ቤቶች አሏት። ከተማዋ በሳምንት አንድ ቀን የሚቆም ገበያ አላት። በዚህ የገበያ ቀን መንግድ አልባዋ ከተማ ከአስር ኪሎ ሜትር በላይ ራቅ ብለው ከሚገኙ ከፍ ከፍ ያሉ ከተሞች  ሸቀጦቻቸውን በአህያ ጭነው በሚመጡ ነጋዴዎች ትደምቃለች። አቡጀዲ፣ የተለያያ ቀለም ያላቸው ሞርዶፋ ባለገመድ፣ ካኪ፣ ቡሬ ሻማ ጨርቆች፣  ሻሾች፣ የሱዳን ሽቶ፣ የቡና ሲኒ፣ ከረሜላ . . .የቀለም ህብር ፈጠረው ከገበያተኞቹና እቃ ለመጫን ከመጡት አጋሰሶች ጋር ተዳምረው ሳምንቱን ሙሉ እረጭ በሎ የሰነበተውን አፈራማ የገበያ ሜዳ በህብረቀለማትና በሁካታ ያደምቁታል። ሌላ ከተማዋን ከተማ የሚያስመስሏት በአንድ ጥግ የተሰበሰቡ የእደ ጥበብ ባለሞያዎች ናቸው፤ በተለይ የቆዳ ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎች። የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን፤ አገልግል፣ ቁና፣ ኤለምቱ ወዘተ ጥሩ አድርገው በቆዳ ይለጉሙ እንደነበረ አስታውሳለሁ። እነዚህ የእደ ጥበብ ባለሞያዎች የአካባቢው ነባር ብሄረሰብ አባል አይደሉም።

የዚህች ሚጢጢዬ ከተማ ነዋሪዎች ዋነኛ መግባቢያ ቋንቋ ኦሮሚኛ ነው። ከተማዋ የኦሮሞዎች ሃገር ነች። ይሁን እንጂ ከተማዋ ጥቂት አማርኛ ተናጋሪዎችም አላት። በዚህ ምክንያት የከተማዋ እንብርት ላይ የተወለድነው ልጆች በመጠኑ አማርኛ ቋንቋ መናገር እንሞክራለን። የተቀረው ህዝብ ግን ከኦሮሚኛ ውጭ የሚሰማወም፣ የሚናጋረወም ቋንቋ የለውም። ታዲያ አንድ ዘመን ላይ መስከረም ጠባና ትምህርት ቤት ገባን። ለአንደኛ ክፍል ተመዝጋቢዎች የተሰጠን አንድ ክፍል መቀመጫ ወንበር አልነበረውም። ባዶ ክፍል ነው። ታዲያ ክፍሉ ከአፍ እስከገደፎ መሬት ላይ በተቀመጡ እድሜያቸው ከ7 እስከ 15 በሚሆኑ ህፃናት ተሞላ። ህጻናቱ የሚያወሩት፣ የሚጣሉት፣ የሚካሰሱት ወዘተ በኦሮሚኛ ቋንቋ ነው። አብዛኞቹ ህጻናት ከከተማዋ እንብርት ወጣ ካሉ አካባቢዎች የመጡ በመሆናቸው ከኦሮሚኛ ውጭ ሌላ ቋነቋ አይችሉም።

ትምህርት ተጀመረ። ከከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉ በተለየ የጸዳ የለበሱት፣ ቆዳ ጫማ የተጫሙት፣ ሰአት ያሰሩት መጀመሪያ የተዋወቅናቸው መምህራችን “እንደምን አደራችሁ ልጆች” አሉ። መምህሩ ምን እንዳሉ የሰማነው ግን ጥቂቶች ነን። ፊደሎችን እየጻፉ አስተማሩን፤ በአማርኛ ቋንቋ። ሌላ መምህር ገባ ቁጥሮችን እየጻፈ አስተማረን፤ ሂሳብ በአማርኛ ተማርን። ይሄው አስተማሪ ጥቂት ቆይቶ ሳይንስ አስተማረን፤ በአማርኛ እያወራ። እነዚህ መምህራን ስለምን እያወሩ እንደነበረ ያወቅነው ግን እጅግ በጣም ጥቂቶች ከከተማዋ እምብርት የመጣን ብቻ ነበርን። መምህሩ ጥያቄ ይጠየቃሉ፣ አማርኛ በመጠኑ የምንሞክረው አንድ አስር ልጆች እንመልሳለን። የተቀሩት ምን እንደተጠየቀና ምን እንደመለስን ያልገባቸው ተማሪዎች መምህሩ እንዳዘዛቸው ያጨበጭቡልናል። መምህሩ በድንገት ጥያቄ የጠይቃቸዋል። በእድሜ ገፋ ያሉትና ገበያ ውለው የሚገቡት 1 ሲደመረ 1 ለሚለውን ጥያቄ እንኳን መመልስ ይሳናቸዋል። መመልስ የሚሳናቸው 1 ሲደመረ 1 ስንት እንደሆነ ስለማያውቁ አይደለም። እንኳን መደመር፣ ማካፈልና ማባዛትም ይችላላ። ልብ በሉ ገበያ ውለው፣ ሸጠው ሸመተው የሚገቡ አስራ አምስት አመት የሚሞላቸው ልጆች ናቸው። ጥያቄው የሚያቅታቸው በአማርኛ ስለሚጠየቅቁ ብቻ ነበር።

በዚሀ ሁኔታ አንደኛ ክፍል ከገባነው ምናልባት 100 ከምንሆነ ህጻናት መሃከል ትምህርት ተጀምሮ አንድ ወር እንኳን ሳይሞላ 40 የማንሞላ የከተማዋ ልጆች ብቻ ቀረን። ጥቂት የከተማዋ ዳርቻና የገጠር ልጆችም ቀርተዋል። ከአማርኛ ጋር እየታገሉ፤ መምህሩ እየሳቀባቸው፤ እኛ አማርኛም በመናገራችን በመምህራችን ፊት ሞገስ ያገኘነውም እየሳቅንባቸው ከአማርኛ ጋር መታገሉን ቀጠሉበት። ይህን ሁሉ አሸነፈው የዘለቁ ነበሩ። ትግሉ ግን ቀላል አልነበረም። ታዲያ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ የማይሰጥበት ምክንያት እንደ ጥያቄ ውስጤ የተፈጠረው ያኔ ነበር።

ከከተማዋ ወጣ በለው የሚኖሩት ዘመዶቼ ከተማ የሚመጡት ለገበያ፣ እህል ለማስፈጨት ወይም እኛን ሊጠይቁን ብቻ ነው። ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ የሚወስድ፣ ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ጉዳይ ስላልነበራቸው ግን አይደለም። ጉዳያቸውን አቤት የሚሉበት፣ ችሎት ቆመው የሚሟገቱበት ቋንቋ ስለሌላቸው እንጂ። እነርሱ የሚግባቡት በኦሮሚኛ፤ ፖሊሶቹና ዳኞቹ የሚናገሩት አማርኛ። በዚህ ምክንያት ግብር በሚከፍሉበት ሃገር የሚገኙት የመንግስት ተቋማት ለእነርሱ ባዕድ ነበሩ። ጉዳያቸውን ተንትነው ማስረዳት በሚችሉበት፣ ተሟገተው መርታት በሚችሉባቸው ባህላዊ ስርአቶች ነበር የሚፈቱት። አፈርሳታ ይወጣሉ፣ ሸነቻ ይቀመጣሉ፤ ይሄው ነበር።

የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት ያከተመን ነገር ለምን ታስታውሳለህ፤ ያረፈ ሰይጣን ቀስቃሽ የምትሉኝ ትኖሩ ይሆናል። ያረፈውን ሰይጣን የመቀስቀስ፣ የዳነውን ቁስል የመቆስቆስ ፍላጎት የለኝም። ይሁን እንጂ አሁንም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ያረጋገጠውን ፌደራላዊ ስርአት፤ የጎሳ ፖለቲካ፣ እርስ በርስ የሚያጋጭ፣ ሃገር የሚበታትን፣ አንድነት የሚያጠፋ ምንትስ ቅብጥርስ እያሉ ወደ ኋላ ሊመልሱን የሚፍገመገሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ስላሉ፣ ስለእነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች ጥቂት የምለው ሰላለኝ ነው። እግረመንገዴንም ከቀናት በኋላ የምናከብረውን 26ኛ የግንቦት ሃያ በአል ለመዘከር።  ባለሃገሩን አፍእያለው አፍ አልባ አድርጎት የነበረው ሥርአት ታሪክ ሆኖ የቀረበት እለት በመሆኑ።

የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን፤ በመረጡት ወኪላቸው የመተዳደር፣ በቋንቋቸው የምንግስት አገልግሎት የማግኘት፣ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት የመጠቀም፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ፣ ባህላቸውን የማሳደግ . . .መብት የተረጋገጠበት ሥርአት የጎሳ ፖለቲካ ሥርአት አይደለም። ጎሳ የሚለው እሳቤ የሰዎች ብሄራዊ ማንነት ሳይሆን፣ የደም ትስስር ባላቸው ሰዎች የሚመሰረት እጅግ አናሳ ቁጥር ያለውን ማህበረሰብ የሚወክል ነው። ተመሰሳይ ብሄራዊ ማንነት ባላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ በርካታ ጎሳዎች አሉ። የጎሳ ማህበረሰብ፣ የመንግስት መዋቅር ባልተስፋፋበትና ማህበረሰቦች ደህንነታቸውን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን በራሳቸው መዳኘት በሚያስፈልጋቸው የእድገት ደረጃ የሚኖር ቡድን ነው። ከስልጣኔና ከመንግስት መዋቅር መሰፋፋት ጋር አስፈላጊነቱ እየቀነሰ የሚመጣ ነው። ጎሳ ከብሄራዊ የማንነት መገለጫ ጋር አየገናኝም።

ብሄር፣ ብሄረሰብ ግን ከአንድ ሰው ወይም ማህበረሰብ ህልውና ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው የማንነት መገለጫ ነው። ጎሳ በራሱ የተለየ መገለጫ የሌለው የደም ትስስር ባላቸው ሰዎች የሚመሰረት የአንድ ብሄር ወይም ብሄረሰብ ህዋስ ነው። በመሆኑም ብሄር ከስልጣኔ ጋር ጎልቶ እየወጣ ወደ መንግስት መዋቅርነት የሚያድግ ሲሆን፣ ጎሳ ደግሞ ከመንግስት እድገት ጋር እየከሰመ የሚሄድ ቡድን ነው።

እናም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት፣ የአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞች እንደሚያወሩት የጎሳ ፖለቲካ ወጤት አይደለም። የብሄራዊ ማንነት መብትና ነጻነት ጥያቄ የወለደው፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተረጋገጠበት ሥርአት ነው። የአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞቹ ፌደራላዊ ስርአቱን የሃገር አንድነትን የሚንድ፣ የእርስ በርስ ግጭት የሚቀሰቅስ ወዘተ ሲሉት መስማት የተለመደ ነው። ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት ጋር በተገናኘ፣  የአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞች ሥርአቱ ከተቀበረ ከሃያ ስድስት ዓመታት በኋላም እንደሰልስት ለቀስተኛ ድምጻቸው ተዘግቶ የሚያንቋርሩትን  አንድነትን ያጠፋል፤ የእርስ በርስ ግጭት ይቀሰቅሳል እያሉ የሚሰብኩትን ጉዳይ እንመልከት።

በመሰረቱ ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር ወይም ብሄረሰብ ሃገር አይደለችም። ከ80 በላይ የተለያየ የማንነት መገለጫ (ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግ . . .)  ያላቸው በየራሳቸው መልክዓ ምድራዊ ወሰን ውስጥ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ነች። እነዚህን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፈጠራቸው ኢህአዴግ ወይም የኢፌዴሪ ህገመንግስት አይደለም። እነዚህን ብሄሮችና ብሄረሰቦች እዚህች ኢትዮጵያ የምትባለው ምድር ላይ የፈጠራቸውና እንዲኖሩ ያደረጋቸው ምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ ነው። በመሆኑም ኢህአዴግን ወይም የኢፌዴሪ ሥርአትን በሃገር ከፋፋይነት ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ቂልነት ነው።

ኢህአዴግም በእነዚሁ በተለያዩ ብሄሮች የተገነባ ፓርቲ ነው። የኢፌዴሪ የመንግሥስት ሥርአትም እንዲሁ በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስምምነት የተገነባ ሥርአት ነው። ኢህአዴግና ሌሎቹም የፖለቲካ ቡድኖች እንዲሁም የኢፌዴሪ ህገመንግስት በፈጣሪ ፍቃድ በብሄር፣ ብሄረሰብ የተከፋፈለችውን ሃገር ለሁሉም ብሄራዊ ማንነቶች እውቅና በመስጠት ተስማምተው አንድነት እንዲመሰርቱ ነው ያደረጉት። አንድ ነገር አንድነት አይመሰርትም። አንድነት የሚመሰረተው በተለያዩ ነገሮች ናቸው። እናም ህብረብሄራዊት ኢትዮጵያ በኢፌዴሪ ፌደራላዊ የመንግስት ስርአት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የወሰን ሳይሆን የህዝብ አንድነት ያላት ሃገር ሆነች። ኢህአዴግንና የኢፌዴሪ ህገመንግስትን በከፋፋይነት መክሰስ የቂል ሃሳብ የሚሆነው ለዚህ ነው። እንደውም ጠንካራ አንድነት ያላት ሃገር እንድትፈጠር ነው ያደረጉት። ፌደራላዊ ሥርአቱ የመከፋፋል ሳይሆን የጠንካራ አንድነት ነው።

በኢፌዴሪ ህገመንግስት የተገነባው ፌደራላዊ ስርአት የእርስ በርስ ግጭት ይፈጥራል የሚለውም አመለካከት በተመሳሳይ ሁኔታ መሰረተ ቢስ ነው። በጽሁፌ መግቢያ ላይ የጠቀስኩተ የልጅነት ትውስታዬ አንድ የሚያሳየነ ነገር አለ። ይህም በአንድ ሃገር ውስጥ የአንዱ ቋንቋ፣ ባህልና ወግ የበላይ፤ የሌሎች ደግሞ የበታች የሆነበት ሥርአት ውስጥ እነኖር እንደነበረ ነው። በዚህ ምክንያት የአንዱ ማንነት የስልጣኔ፣ የትልቅነት መገለጫ ሲሆን የሌሎች ደግሞ ያለመሰልጠን የኋላ ቀርነት መገለጫ ተደርጎ የተወሰደበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ሁኔታ በአንድ ሃገር ላይ አንዱ በማንነቱ ሲኮራ ሌሎች ደግሞ እንዲሸማቀቁ ተደርጓል። ይህ ሁኔታ በብሄሮች መሃከል የተዛባ ግንኙነት በመፍጠር አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት አድርጓል። በመጨረሻም በአልገዛም ባይነት ብረት እንዲያነሱ ያስገደደን ሁኔታ ፈጥሯል።

በዚህ አንገዛም ብለው ብረት ባነሱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና በአሃዳዊ ሥርአቱ መሃከል በተቀሰቀሰ ግጭት ሃገሪቱ የጦር አውድማ ሆና መቆየቷ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን አካል በመሆኑ ብዙዎቻችን እናስታውሰዋለን። አሃዳዊ ስርአቱ የግጭት መንስኤ ነበር ማለት ነው። አሃዳዊው መንግስት ከሃይል ውጭ ይህን ግጭት መፍታት የሚያስችለው ህግና ሥርአት ስላልነበረው ሃገሪቱ የመበታተን ጠርዝ ላይ ደርሳ ነበር። አሃዳዊው ሥርአት የመበታተን አደጋ ነበር ማለት ነው። እርግጥ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በአንድነት በሚኖሩበት ፌደራላዊ ሥርአት ውስጥም ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል። ይህ በፌደራላዊ ሥርአት የሚፈጠር ግጭት ግን የሃገርን አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ መሰረታዊና ዘላቂ አይደለም። በዚህ ላይ የፌደራላዊው መንግስት ህገ መንግስት ግጭቶችን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ሥርዓት አለው።  

እናም የግጭት መንስኤና የሃገር መበታተን አደጋ ያለው የዘውዳዊ ሥርዓት ተስፈኞች እንደሚያወሩት ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህጋዊ እውቅና አግኝተው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት ለመኖር የተስማሙበት የህዝብ አንድነት ያለው ፌደራላዊ ሥርአት ሳይሆን፣ ለብሄራዊ ማንነቶች እውቅና የሚነፍገው አሃዳዊ ሥርአት ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርአት የመከፋፈልና የግጭት መንስኤ ሳይሆን ጠንካራ አንድነት የፈጠረና አንድነትን ያጸና ነው።