ፌዴራሊዝምና የህዝቦች አንድነት
ዳዊት ምትኩ
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ ገጥመው ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ነው። በሥርዓቱ ውስጥ ዜጎች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል። ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትም ተሸጋግረዋል። ውጤቱን ከማጣጣም ባለፈ የህዳሴያቸውን ፈር ቀዳጅ መንገድ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ሥርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ አድርጓቸዋል። እርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ በመሆኑ ይህ ውጤት ከተገኘ 25 ዓመታት ሆኗል።
እናም ይህ ሁኔታ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዳንድ ወገኖች ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ’ በማለት ሲገልጡ የነበሩትን የተሳሳተ መፅሐፍ ግምት ፉርሽ አድርጎታል።
እርግጥ እነዚህ ወገኖች በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አይመስለኝም—የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ። ያም ሆኖ ግን እነርሱ ያሻቸውን ቢሉም የሆነው ሃቅ አሁን ከ26 ዓመት በኋላ ያለው ዓለም ያደነቀው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ነው።
የሀገራችን ህዘቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።
ከዚህ ዕውነታ የሚነሳው የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።
ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።
ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ከ26 ዓመታት በኋላም ቢሆን በሚገባ ማረጋገጥ ስለቻሉ ነው።
ለነገሩ አንዳንዶቹ ይህን ሃቅ እያዩ እንኳን በማንኛው በማደግ ላይ በሚገኝ ሀገር ውሰጥ እንደሚፈጠረው በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ነባራዊ ክሰተቶችን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ፌዴራሊዝሙ አደጋ ተደቅኖበታል ይላሉ። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን የዚህን ሀገር ፌዴራሊዝም ካለመገንዘብ የሚመነጭ ነው።
ይሁን እንጂ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ ክስተት ነው። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በሥልጣኔ በገፉ ሌሎች ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ ነባራዊ ክሰተት ነው። ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሀብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስዔ የሚታይ ነው። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም። እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ስላለባት ነው።
ነገር ግን ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም። ምክንያቱም ጥልቅ አስተምህሮትን ስለሚጠይቁ ነው። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።
ሥርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል። በእኔ እምነት የኢፌዴሪ መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም። ባለፉት 26 ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራቶች ስንቃኛቸው የሚያሳዩን ዕውነታዎች ይህንኑ ነውና።
የብሔረሰቦች መብት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለትና ለተግባራዊነቱ ህዝቦች በሙሉ የተረባረቡበት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ ገዥው ፓርቲም ይሁን የሀገራችን ህዝቦች ያላቸው አቋም የሚዛነፍ አይመስለኝም። ሥርዓቱን ዕውን ለማድረግ ሲሉ የወደቁ የህዝብ ልጆችን መርሳት ስለማይቻል ነው። ከዚህ ውጭ ሥርዓቱ በልዩነት ውስጥ ላለ አንድነት ዋስ ጠበቃ ሆኖ ይቀጥላል።
ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወቱና አንድነትን ከማጠናከር አኳያም ረጅም ርቀት መጓዙን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ሥርዓቱ ራሱን እያረመና እንደ ማንኛውም ጀማሪ የፌዴራል ስርዓት ያሉበትን ችግሮች እየነቀሰ እንዲሁም ካለፉት ክስተቶች እየተማረ በሀገሪቱ ህዝቦች በመታገዝ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል። ይህ አስተማማኝ ቁመናም የህዝቦችን አንድነት በማፅናት የዚህችን ሀገር መፃዒ የህዳሴ ተስፋ ቅርብ ያደርጋል።