Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለምን እንከተላለን?

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለምን እንከተላለን? /ቶሎሳ ኡርጌሳ/

        የዓለማችን ህዝቦች የተለያዩ የመንግስት አወቃቀር ሥርዓቶችን ይከተላሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አሃዳዊና ፌዴራላዊ ሥርዓቶች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አንድ አገር የምትከተለው ሥርዓት ከአጠቃላይ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ሁኔታዋ አኳያ የሚታይ ቢሆንም፤ ሥርዓቱ በዚያች ሀገር ውስጥ እንዲሰፍን የህዝቦች ይሁንታና ሁሉን አቀፍ ፈቃድ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዛሬ ላይ በርካታ አገራት ፌዴራሊዝምን በተመራጭነት ሲከተሉት ይስተዋላል፡፡

ርግጥ ለፌዴራላዊ ሥርዓት ተመራጭነት በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ለሚጠቀሱ ቢሆንም፤ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በዓለማችን የተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ያሉት ተከታታይ ክስተቶች የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዙ ናቸው፡፡ ክስተቶቹ ቀደም ሲል በቅኝ ግዛትነት ተይዘው የነበሩ ሀገራት ነፃ ለመውጣትና በአሃዳዊ አገዛዝ ሥር የነበሩትም በአንድነት ለመሰባሰብ እንዲሁም አምባገነናዊና ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ የመንግስት መዋቅር ራሳቸውን ለማላቀቅ ያደረጉት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክስተቶቹ የእነዚህ ሁነቶች ድብልቅ ሆነው በየሀገራቱ መታየታቸው ፌዴራሊዝም ተመራጭ እንዲሆን እንዳስቻሉት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች ወካይ መሆናቸው የሚነገርላቸው የእነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች ድምር ውጤትም በአሁኑ ወቅት በመንግስታቱ ድርጅት በአባልነት ከሚታወቁት አገሮች ውስጥ 28 የሚሆኑት ፌዴራላዊ መዋቅርን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል፡፡ ርግጥ የሀገራቱ ቁጥር ትንሽ ይምሰል እንጂ፤ ከህዝብ ብዛት አንጻር ውጤቱ ሲለካ ከዓላማችን ህዝብ ውስጥ 49 በመቶ የሚሆነው በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ታቅፎ የሚኖር መሆኑን ስንመለከት የሥርዓቱ ተመራጭነት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

እዚህ ላይ ከላይ “ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለምን እንከተላለን?” ለሚለው ጥያቄያዊ ርዕሴ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት፤ ጥቂት ጥቅል እውነታዎችን ለመንደርደሪያ ያህል ባነሳ ወደ ምላሹ ይወስደናል፡፡ ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር በህዝቦች ተመራጭ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት እያንዳንዱ ህዝብ በሚፈጠረው የራሱ ፌዴራላዊ ማህበረሰብ ውስጥ የጋራ ጥቅሞችን እየተጋራ የየራሱን የራስ ገዝነት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለው ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም በጋራ ማዕቀፉ ውስጥ ያለው ህዝብ ከተመቸው የፌዴራል ሥርዓቱ አካል የመሆን፤ ካልተመቸው ደግሞ ከአባልነቱ ራሱን ሊያገል የሚችልበት ልዩ መብት እንዲኖረው የሚያደርግ በመሆኑ የተመራጭነቱን ደርዝ ያሰፋዋል፡፡ በመሆኑም ሥርዓቱ የሚሰጠው መብት ለተመራጭነቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

እነዚህን መሰሎቹ የሥርዓቱ የተለዩ ሁኔታዎችን የማስተናገድ ብቃትና ባህሪ በዓለማችን ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው አስር ሀገራት ውስጥ ስድስቱ እንዲሁም ከአስሩ የዓለማችን ሰፋፊ ሀገራት ስምንቱ በፌዴራላዊ ስርዓት እንዲታቀፉ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

እርግጥ በዓለማችን ላይ ፌዴራሊዝምን የሚከተሉ አገራት ‘ሥርዓቱን በዚህ ሁኔታ መከተል አለባቸው’ የሚል አንድ ወጥ እሳቤ የለም፡፡ በየአገራቱ ያሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ክልላዊ አሰፋፈር፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና ሰፊ ግዛት ያላቸው እንዲሁም ብዙሃነትን አካትተው ለያዙ አገራት ሥርዓቱ በተመራጭነት እንዲያዝ አድርጎታል፡፡

ፌዴራሊዝም መሰረቱን በህገ መንግስታዊነትና በህግ የበላይነት ላይ ያደረገ በመሆኑ አንድ አገር ሥርዓቱን ሲመርጥ ብዙሃነትን የያዘ ቢሆንም፤ የተመሰረተው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ መሆኑንም ማረጋገጥ የውዴታ ግዴታው ይሆናል፡፡ ይህም ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚከተል አገር ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ሊሸከም የሚችልበት ትከሻ የሌለው መሆኑን ያሳየናል፡፡

እስቲ አሁን ደግሞ ‘ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለምን እንከተላለን?’ ወደሚለው ጥያቄ ምላሽ ላምራ፡፡

እንደሚታወቀው የህዝቦችን የዘመናት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አፍኖ ከነበረው አምባገነናዊው የደርግ ሥርዓት ውድቀት በኋላ፤ በሀገራችን የነበረው ሁኔታ በጥልቀት መፈተሹ የግድ ነበር፡፡ በመሆኑም የዛሬ 26 ዓመታት በቅድሚያ የተወሰደው ርምጃ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብረት አንስተው ያለፉት ሥርዓቶችን ያስወገዱበት መነሻ ጥያቄዎቻቸው በአግባቡ እንዲመለሱ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ ሆነ፡፡ ከ1983 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው የሽግግር መንግስቱ ቻርተር ለእነዚህ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄዎቹ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ቻርተሩ ተጨባጭ ለሆኑና አፍጥጠው ለመጡት የህዝብ ሉዓላዊነት እንዲሁም ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች ብሎም ሰር ሰደው ለቆዩት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መሰረታዊ መፍትሔ ሊሰጥ ችሏል፡፡ ቀደምት አሃዳዊ ሥርዓቶች ለእነዚህን ቁልፍ የህዝቦች ጥያቄዎች መልስ የማይሰጡ በመሆናቸው፤ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙት በቻርተሩና ኋላ ላይም በ1987 ዓ.ም በህዝቦች ውይይትና ሙሉ ፈቃደኝነት በፀደቀው ህገ መንግሥት ነው፡፡

በወቅቱ በራሳቸው የትግል ፍሬ ምላሽ ያገኙት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከ80 በላይ ስለሆኑ እነዚህን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩነታቸውን አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ለማድረግ ፌዴራሊዝም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር፡፡ እናም ሀገራችን የፌዴራል የመንግስት አወቃቀርን ለመከተል ችላለች፡፡ ብዝሃነታችን ሥርዓቱን እንድንመርጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ በእኔ እምነት በወቅቱ የሀገራችን ህዝቦች ይህን የመንገሥት አወቃቀር ባይመርጡ ኖሮ፤ በወቅቱ ከነበሩት የታጠቁ የብሔር ሃይሎች አኳያ ዛሬ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ለመኖሯ ማንም በርግጠኝነት መናገር የሚችል አይመስለኝም።

እዚህ አገር እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት የአገሪቱን ፖቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መነሻ ያደረገ እንጂ እንዲሁ ዝብ ብሎ የተመረጠ አለመሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ መነሻ ሁኔታዎችም በህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ ስፍረዋል፡፡ ላለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታትም በተግባር ውለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሀገራችን ለዘመናት ምላሽ ሳይሰጣቸው ለኖሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስፋት ባለው ህዝብ ተሳትፎ ምላሽ እንዲሰጣቸው ያደረገ በመሆኑ የፌዴራል ሥርዓቱ መገለጫ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት ሆነዋል፡፡ ይህም የመንግስት ቅርፀ- መንግስትነት ከሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመነጨ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ዕውነታም ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የሆኑት የአገራችን ህዘቦች የፌዴራሉን ስርዓት በራሳቸው ይሁንታና ስምምነት መፍጠራቸውን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ካላቸው ስልጣን ቆርሰው ለፌዴራል መንግስቱ በመስጠት የሀገሪቱ አስተዳደር በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት እንዲንቀሳቀስ ፈቅደው ተስማምተዋል፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማስረጃ ህገ መንግስቱ በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች …”  በሚል ሐረግ መጀመሩ ነው፡፡

የእኛ አገር ፌዴራላዊ ሥርዓት በህብረ ብሔራዊነት ቀለም ያሸበረቀ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት የየትኛውም ዓይነት ፌዴራሊዝም ዋነኛ ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩነታቸው ውስጥ ያለውን አንድነት አቻችሎ በጋራ እንዲኖሩ ማድረግ በመሆኑ፤ በውስጧ ከ80 በላይ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የያዘችው ኢትዮጵያ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖራት የሚችል አይመስለኝም፡፡

ይህ በመሆኑም እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የአብሮነት ዋስትናቸው ሆኖ እነሆ ላለፉት 26 ዓመታት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያድጉ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ርግጥ አገራችን ለምን ፌዴራሊዝምን እንደምትከተል ምላሽ ለመስጠት ሲታሰብ፤ የህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 ሳይወሳ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይህ አንቀፅ አገራችን እንድትበተን የሚሹ ወገኖች በተዛባ ትርጓሜ የሚያራግቡት በመሆኑ አብሮ በምራራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ አንቀፅ ከአገር ብተና ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ የለም፡፡ እንዲያውም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በአንድነት መኖር የሚያስችላቸውን ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ዕድልን የሚሰጥ አንቀፅ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው ተረጋግጦ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል፡፡

እናም በአንቀጹ አማካኝነት የእኩልነት መብት ማረጋገጫ የሆኑት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች ወዘተ ተከብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፖለቲካዊ አስተዳደር በኩል እኩል የመሳተፍ መብት ያገኙ ሲሆን፤ በልማት ስራው ላይም እኩል ዕድል እዲያገኙና በውጤታቸው መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ማንም ሰው እነዚህን መብቶች ያረጋገጡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊበታተኑ ይችላሉ ብሎ ማሰብ የሚችል አይመስለኝም። የትኛውም ህዝብ እነዚህ መብቶች እስከተሰጡት ድረስ ጥቅሞቹን እያጣጣመ የፌዴራል ሥርዓቱን ያጠናክራል እንጂ ለመበተን ይፈልጋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል፡፡

እንዲያውም በእኔ እምነት በግጭት ውስጥ እየታመሱ ያሉት አንዳንድ አገራት ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር አንቀፅ ቢኖራቸው ኖሮ እስካሁን ድረስ የተከሰተው ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ እናም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለምንም ገደብ ያረጋገጠ ቢሆንም ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን በሀገሪቱ ላይ ለማምጣት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የምንከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አባሎቹ የሚናቆሩበትና የሚባሉበት ሳይሆን አብረው በፈቃዳቸው በጋራ የሚያድጉበት መሆኑም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተባብረውና ተጋግዘው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተደርጎ የተቀረጸው የፌዴራሉ ሥርዓት በህገ መንግስቱ ላይ በግልጽ መንጸባረቁ የጥንካሬው መገለጫ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ የህገ መንግስቱን መግቢያ ቆንጥረን ብንወስድ እንኳን “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነፃነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ መገለጫ ህብረ ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን የሚያመለካክት ነው፡፡ እነዚህ ነባራዊ ሃቆች ፌዴራላዊ ሥርዓትን እንድንከተል ያደረጉን ናቸው፡፡ መፃዒ የህዳሴ ጉዟችንንም እንደሚያሳኩልን በርግጠኝነት እንድንናገር የሚያደርጉን መሆናቸውም እንዲሁ።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy