‹‹የግለሰቦች ኩርፊያ እንጂ የአስፈጻሚው ተፅዕኖ የለም››
አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስፈጻሚው እየተጠመዘዘ ከመሆኑም በላይ፣ አስፈጻሚውን ተጠያቂ ማድረግ አልቻለም ተብሎ የቀረቡበትን ትችቶች ተከላከለ፡፡
ፓርላማው የሚቀርቡበትን ትችቶች የተከላከለው የሕዝብ ክንፍ ከሚላቸው ከሚዲያ፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምርና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ዓርብ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በተወያየበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ውይይት ላይ የተጠቀሱት ተቋማት አመራሮች ተገኝተው የፓርላማውን የቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ላይ፣ እንዲሁም የአስፈጻሚው ፓርላማውን የመጠምዘዝ ዝንባሌዎችን አስመልክቶ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ‹‹አስፈጻሚው ለዚህ ምክር ቤት ተጠያቂ መሆኑ በተግባር አይታይም፡፡ ተጨማሪ ርቀት መሄድ የለብንም ወይ?›› ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ የአስፈጻሚው አካላት አመራሮች ፓርላማው በሚሰጣቸው አስተያየቶች ካልታረሙ እንዲባረሩ ይደረጋል ቢልም፣ በተግባር አለመታየቱና ከተባረረ በኋላ የሚመጣው አስፈጻሚ ተመሳሳይ ስህተት የሚፈጽም ቢሆን ምን ዓይነት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሚሰጥ የተቀመጠ ነገር አለመኖሩን እንደ ክፍተት አንስተዋል፡፡
የሚዲያና ኮሙዩኒኬሸንስ ሴንተር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ፣ እንዲሁም የዛሚ ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፣ ፓርላማው በአስፈጻሚው ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ዘልቆ እንደማይታይና አስፈጻሚው ደግሞ የሥልጣን ምንጭ የሆነውን ፓርላማ ዝቅ አድርጎ የማየት ዝንባሌ መኖሩን በጥያቄ አንስተዋል፡፡
ለቀረቡት ጥያቄዎች በቅድሚያ ምላሽ የሰጡት የምክር ቤቱ አባልና በሥራ አስፈጻሚው ውስጥ የካቢኔ አባልና በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት እንደመሆኑ መጠን፣ በፓርላማው አብላጫ መቀመጫ የሚይዘው ገዥው ፓርቲ እንደሆነና ገዥው ፓርቲ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚውንም ሥልጣን እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ ሁለት አካላት መካከል የሚኖረው ክትትልና ቁጥጥር ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት እንደሚከተሉ አገሮች መሰዳደብና ጫማ መወራወር ውስጥ እንደማይገባ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ለክትትልና ለቁጥጥር ተብሎ የሚደረግ የፖሊሲ ክርክር በእኛ ሥርዓት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ክትትልና ቁጥጥሩ የሚሆነው አፈጻጸም ላይ ነው፡፡ ይህ ያለ ገደብ የፓርቲ ዲሲፕሊን የሚባል ነገር ሳይኖር መከናወን ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያም ቢሆን ፓርላማው ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርገው ለማሳጣትና ለማጋለጥ አለመሆኑን፣ ዋናው ዓላማም መደጋገፍ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የተቀናጀ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዕውን እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ በሥራ ድርሻችን ተለያይተናል እንጂ አንድ ፕሮግራም ይዘን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ አስፈጻሚውም፣ ፓርላማውም፤›› ብለዋል፡፡
ዋና ዓላማው ሥራ አስፈጻሚውን መደገፍ ይሁን እንጂ፣ በተደጋጋሚ እንዲያስተካክል ተነግሮ መሻሻል ያልቻለ ሚኒስትር እንዲነሳ የሚደረግበት ሥርዓት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
‹‹ፓርላማው ሚኒስትር ማባረር አይችልም፤›› ያሉት አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግር የታየበትን ሚኒስትር እንዲያነሳው ውይይት ይደረጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ካላደረገ፣ ፓርላማው በአመኔታ ማጣት ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲነሳ የሚደረግበት ሥርዓት ተዘርግቷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የእኛ (የፓርላማው) ውስንነት ሊኖር ይችላል፡፡ ከአቅም ጋር ከልምድ ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
አስፈጻሚው ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት አለው የሚባለውን በተመለከተ ግን፣ የተሳሳተ እንደሆነና ፓርላማውም እንዳልገመገመው ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአስፈጻሚው አካል በአጠቃላይ የሚታይ ባይሆንም፣ የሚያኮርፉ ግለሰቦች እንዳሉ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ጠቁመዋል፡፡
ይህንኑ ጉዳይም አቶ አስመላሽ ይስማሙበታል፡፡ ‹‹ጥያቄ ሲነሳባቸው የሚያኮርፉና ተደራጅተን እንደጠየቅናቸው አድርገው የሚወስዱ አሉ፡፡ ለምን ተነካን? የሚሉ ግለሰቦችም አሉ፡፡ ፈጻሚው አካል ነው ግን ማለት አይቻለም፤›› ብለዋል፡፡