Artcles

26 አንፀባራቂ ሻማዎችን የምንለኩስበት ዕለት

By Admin

May 15, 2017

26 አንፀባራቂ ሻማዎችን የምንለኩስበት ዕለት

                                                    ዘአማን በላይ

ወርሃ- ግንቦት በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪክ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ነው። ወሩ በገባ በ20ኛው ቀን፣ አሊያም ሰኔ ‘ግም’ ሊል 10 ቀናት ሲቀሩት በኢትዮጵያ ህዝቦች ህይወት ውስጥ ደማቅ፣ አንፀራቂና በድል የታጀበ ታሪክ ተመዝግቧል። የታሪኩ ባለቤቶች፣ የድል ብስራት ነጋሪዎችና የድሉ ባለቤቶች እነርሱው በመሆናቸው፤ ዛሬ ላይ ዕለቱን ለማክበር ከወዲሁ እየተዘጋጁ ነው‒26 ሻማዎችን ለመለኮስ።

ይህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲስ ውልደት ታሪክ የሁላችንም ነው‒የእርስዎም፣ የእነርሱም፣ የእኛም፣ የእርሱም፣ የእርሷም፣ የእኔም፣ የ…ሁላችንም። ግንቦት 20 ቀን። ይህ ዕለት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ የለውጥ አብነትና ብርሃን የፈነጠቀበት ነው። ይህ ቀን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሚዘገንን ሁኔታ ላያቸው ላይ ተጭኖ አላላውስ…አላንቀሳቅስ ያላቸውን አስከፊውን የአምባገነንነት ቀንበር ዳግም ላይመለስ ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው የጣሉበት ነው።

ይህ ቀን የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የነበሩትን ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን በእጃቸው ውስጥ ያስገቡበት ነው። ይህ ቀን በኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አስተሳሰብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ነው። ይህ ዕለት በንጉሱና በደርግ ስርዓቶች መዝገበ ቃላት ውስጥ ተሰርዘውና ተፍቀው የነበሩት የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ መሰረት የተጣለበት ነው። በጥቅሉ ዕለቱ ዛሬ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ተጠቃሽ ቁመና ፈር የቀደደ ነው። ታዲያ ጥቂት ቀናቶች ለሚቀሩት ይህ  የለውጥ አብነት ዕለት እኛ ኢትዮጵያዊያን 26 ሻማዎችን ለመለኮስ በዝግጅት ላይ እንገኛለን። ሆኖም ዕለቱን ስናስብ፤ በግንቦት 20 የተገኙትን ጥቂት ለውጦች ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል። እናም በዚህ ፅሑፌ ከተገኙት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ለውጦች ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ተገቢ ያልሆነ ምስል ስለሚሰጠው የልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የተገኘውን ድል በጥቂቱ ብቻ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

እንደሚታወቀው ሀገርን አዋርዶ፣ ህዝብን እያሸማቀቀ ለተመፅዋችነት የዳረገን ብሎም ለዘመናት እንደ ክት ዕቃ በዚህች ሀገር ተጎልቶ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ መክፈታቸው አይዘነጋም። ይህን ጠላት ለመዋጋት በመንግስት ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ መጀመራቸውም ይታወሳል።  

ርግጥ በእነዚህ ከህገ መንግስቱ ማግስት እስከ የመጀመያው ተሃድሶ ወቅት በነበሩት የአምስት ዓመት ጊዜያት የበርካታ ፖሊሲዎች መነሻና ሀገሪቱ ውስጥ የነበሩ የተዛቡ አስተሳሰቦች እንዲቀየሩ ጥረት የተደረገባቸው ወቅቶች ስለነበሩ ይህን ያህል የጎላ ለውጥ የመጣባቸው ጊዜያት አልነበሩም።

ይሁንና ላለፉት ተከታታይ 15 ዓመታት ከድህነት ጋር በተደረገው ትንቅንቅ ኢትዮጵያዊያን ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል። በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም ተስፋ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አስመስክረዋል። ታዲያ ይህ ተከታታይና ፈጣን ልማት የተመዘገበው ግንቦት 20 ባስገኘው ዘላቂ ልማት መሆኑ የሚካድ አይደለም። ርግጥም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አስተማማኝ ሰላም ባይኖር ኖሮ ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም። ያም ሆኖ ግን በአስተማማኝ ሰላም ሳቢያ የተገኘው ልማት ሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

ግንቦት 20 በዚህ ሀገር ውስጥ በማህበራዊ ልማት መስክም ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ነው። በተለይም በትምህርትና በጤና አገልግሎት ረገድ በሁሉም የሀገራችን ቀበሌዎች ውስጥ ዜጎች በቅርበት አገልግሎቶቹን አግኝተዋል። በተለይም በሀገራችን በመጀመሪያ ትምህርት መስፋፋትና በእናቶችና ህፃናት ሞት በመቀነስ ረገድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስቀመጠው የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች ማሳካት የቻለች ሀገር ሆናለች። ይሀም እዚህ ሀገር ውስጥ የልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በሌላው ዘውጉም የግንቦት 20 ድል ካስገኛቸው ለውጦች ውስጥ የመሰረተ ልማት መስክ ተጠቃሽ ነው። በመስኩ ባለፉት 26 ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል።  የባቡር ሃዲድ መስመር ዝርጋታ፣ ሀገር አቋራጭ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች፣ ወረዳን ከቀበሌ እንዲሁም ቀበሌን ከቀበሌ የሚያስተሳስሩ ክረምት ከበጋ የሚያገለግሉ መንገዶች ግንባታ ተከናውነዋል። እነዚህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚመለከቱ ናቸው። ጠቀሜታቸው በእኩልነት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚዳረስ ነው። እናም በዚህ ረገድ ረጅም ርቀት መጓዝ መቻሉ የልማቱን ፍትሐዊነት አቅም በፈቀደ መጠን ለማዳረስ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።

ከግንቦት 20 ድሎች ውስጥ ሊጠቀስ የሚችለው ሌላኛው ጉዳይ ሀገራችን በሃይል አቅርቦት ላይ ያከናነችው ተግባር ነው። በዘመነ ደርግ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የነበረው የሃይል አቅርቦት ከ300 ሜጋ ዋት የማይበልጥ ነበር። ይሁንና የኢፌዴሪ መንግስት በቀረፀው የኢነርጂ ፖሊሲ ይን ዕውነታ እጅግ መቀየር ችሏል። እንደሚታወቀው በመንግስት በኩል ኃይልን ለማቅረብ የየወቅቱን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ፤ የዘርፉን ሥራ በማስፋትና በማቀላጠፍ ከድህነት የሚያላቅቅና የሀገሪቱን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተቃኘ የኢነርጂ ፖሊሲ መነገፉን እናስታውሳለን፤ በ1986 ዓ.ም።

ርግጥ የፖሊሲው ዓላማ የሀገሪቱን የኢነርጂ ሀብት ከአጠቃላይ የመንግሥት የልማት ስትራቴጂ አኳያ ማጎልበትና ሥራ ላይ ማዋል፣ ሌሎች የየአካዳሚ ዘርፎች የዘረጉትን የልማት አቅጣጫ የሚደግፍ ግልጽና ውጤታማ የኢነርጂ ኃይል እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል ውጤታማ የኢነርጂ አጠቃቀም እንዲኖር ማስቻል ብሎም ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት በመፍጠር ኢኮኖሚውን መታደግ የሚሉ ዓላማዎችንም ጭምር አንግቦ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑበት ነው።

እነዚህን ዓላማዎች ለማካት የኢነርጂ ፖሊሲው ቀጣይነትና አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም ዘርፉን የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ፈጣን ኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር እንዲኖር መመሪያዎችን ለመዘርጋት ከፍ ሲልም ሀገር በቀል የሆኑና የአየር ንብረት ብክለትን የሚያስወግዱ የኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።

በዚህ መሠረት ፖሊሲው ለውሃ ኃይል ልማትን እንዲሁም የኢነርጂ አጠቃቀም ስብጥር በማበረታታት ለታዳሽ የኢነርጂ አጠቃቀም፣ ለፀሐይ ኃይል፣ ለንፋስ እና ጂኦተርማል ልማት እንዲሁም ለዋጋ ተወዳዳሪነት ትኩረት የሰጠ ነው። ይህን ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ነው— የህዳሴው ግድብም ይሁን ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ግንባታቸው በመከናወን ላይ የሚገኙት።

ታዲያ በፖሊሲው መሰረት የዛሬ 26 ዓመት ገደማ ከ300 ሜጋ ዋት የማይበልጠውን የሃይል አቅርቦት ዛሬ ከአራት ሺህ ሶስት መቶ ሜጋ ዋት በላይ ማድረስ ተችሏል። ይህ አመርታ በመጀመሪያ የፖሊሲውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ያደረገ ነው። ሆኖም ፖሊሲው አሁንም በሀገራችን የሚታየውን የሃይል አቅርቦት ሁኔታ ለማሻሻል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅና በሙሉ አቅሙ ማመንጨት ሲጀምር ወደ 11 ሺህ ሜጋ ዋት የሚጠጋ ሃይል ለማግኘት ታስቧል። ይህ ሲሆንም እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል።

በጥቅሉ እነዚህ በምሳሌነት ያነሳኋቸው ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ጉዳዩች 26 ሻማዎችን ልንለኩስ የተዘጋጀንለት ዕለተ ግንቦት 20 ያስገኘው ለውጥ ነው። ለውጡ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው እንዲጠቀሙና የአኗኗር ዘይቤያቸውም እንዲቀየር ያደረገ ነው። ታዲያ የዚህ ለውጥ ፈር ቀዳጅ የሆነውን ዕለት ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በየዓመቱ ቢያከብሩት ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም።