Artcles

ጅማሮው ይበልጥ ይጠናከር!

By Admin

May 05, 2017

ጅማሮው ይበልጥ ይጠናከር!/ ወንድይራድ ኃብተየስ/

ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት በተንሰራፋበት ሥርዓት ውስጥ መልካም አስተዳደር ሊሰፍን አይችልም። መልካም አስተዳደር ከሌለ ደግሞ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ይረጋገጣሉ ተብሎ አይታሰብም።

ሦስቱም የማይነጣጠሉ ወሣኝ ጉዳዮች በመሆናቸው መልካም አስተዳደር በሌለበት ሠላምና ዴሞክራሲ እውን ሊሆን አይችልም። የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ባልተረጋገጠበትና የቡድን መብት ባልተከበረበት ሁኔታ በኢኮኖሚ የበለፀገች አገር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በርካታ መሰናክሎች እንደሚያጋጥሙት እውነት ነው።  

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሉባቸው አገራት ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የህልውና ጉዳይ እንደሚሆን በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ይፋ ካደረገና ይህንኑ ያገናዘበ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ ሁለት አሥርት ዓመታት አልፈዋል።

ለአገሪቱ የዕድገት ጎዳና ዋናው መሰናክል ተብሎ የተለየው ኪራይ ሰብሳቢነትን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀውና ራሱን ከእንዲህ ዓይነት አፀያፊ ድርጊት አርቆ በድርጊቱ የሚሳተፉትን ግለሰቦች ላይ በሚወሰድ ርምጃ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ በተለያየ ጊዜ ቀላል የማይባሉ የአስተምህሮ ተግባራት ተከናውነዋል።

ኅብረተሰቡ በሙሉ ኃይል እንዲታገል አመቺ ሁኔታ መፍጠር በማስፈለጉ ጉዳዩን በዋናነት የሚመሩ ተቋማት በየደረጃው ተቋቁመው አቅም በፈቀደ መጠን በበቂ የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራዎች ተከናውነዋል። ተቋማቱ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ወንጀሎች በመከታተል ይመረምራሉ፣ ያጠናሉ ከዚያም እንዳስፈላጊነቱ ወንጀለኞች  በሕግ  እንዲጠየቁ ያደርጋሉ።

በየደረጃው የተቋቋሙት የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማት የግዥ አፈጻፀምን፣ ብልሹ አሠራሮችን፣ ትላልቅ የልማት ተቋማት የገንዘብና የሰው ኃይል አጠቃቀምንና የመሬት አስተዳደርን በተገቢው መልክ በመከታተል መንግሥት በየደረጃው የሚመድበው በጀት ለተመደበለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የክትትል፣ የምርመራና በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥልጣን ኖሯቸው እንዲቋቋሙ ተደርጓል።

በዚህ መልክ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉትንም ሆነ በተለያየ የግል ሥራ ተሰማርተው ያለአግባብ ለመበልፀግ ሲሉ ሕገ ወጥ አካሄድን በመረጡ ተጠርጣሪ ባለሃብቶች ላይ ክስ ለመመሥረት በሂደት ላይ ይገኛሉ።

ከድህነት ማጥ ወጥታ ዘላቂና ቀጣይነት ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ መሰለፍ ትችል ዘንድ የግብርና መር የኢኮኖሚ ሥርዓቷን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር መሠረት ይጥላል በሚል የተነደፈውና እየተተገበረ ያለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በስኬት ጎዳና ላይ ቢሆንም ጉዞው አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይቻልም። ሆኖም

በርካታ ተግዳራቶች ቢያጋጥሙም በየደረጃው  መፍትሄ እየተሰጣቸው ይገኛሉ። ከእነዚህ ዐበይት  ችግሮች መካከል ኪራይ ሰብሳቢነትና መገለጫው የሆነው ሙስና በዋናነት ይጠቀሳሉ። ለዚህም ነው መንግሥት  መሰናክሎችን እየለየ የመፍትሄ ሃሳቦችን፣ የአፈታት  ሥልቶችንና አቅጣጫዎችን  እያስቀመጥ ያለው። በኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች ላይ ክትትልና ምርመራ ከማድረግ  ጎን ለጎን አስከፊነቱን በኅብረተሰቡ ዘንድ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር በመላው ህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ለተሰነቀው የጋራ ራዕይ  መሰናክል መሆኑን ሁሉም አውቆ የበኩሉን ድርሻ በመፈፀም  የጋራ ብልጽግናን ለማፋጠን ጥልቀት ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ነው።

አሁን…አሁን ቀንደኛ ጠላታችን ድህነት መሆኑ ላይ በብዙዎች ዘንድ  መግባባት ላይ ተደርሷል። ድህነትን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት በመግታት ለድህነት መንሰራፋት  ኪራይ ሰብሳቢነት የሚኖረው ድርሻ ቀላል አለመሆኑን በተገቢው መልክ መግባባት መፍጠር ሙስናን ለመሸከም የማይችል ኅብረተሰብ ለማፍራት ያግዛል በሚል እምነት መንግሥት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም ሙሰኝነትን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት በግላጭ አሳይቷል።

የተጀመረውን ተስፋ ዳር ለማድረስና የለማች አዲስቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት ላይ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ  ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ መዋጋት የሚያስችል መግባባት ላይ መድረስና ይህንኑ በቆራጥነት መተግበር ያሻል።

ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የነደፈቻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመተግበር ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አበረታች የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ብትችልም ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት የሥርዓቱ አደጋ ሆነው ተጋርጠውባታል። 

መንግሥት ኅብረተሰቡን  አስተባብሮ አገሪቱ የሰነቀችውን ራዕይ ዳር ለማድረስ  ኪራይ ሰብሳቢዎችንና ሙሰኞችን  በማጋለጥና ለህግ በማቅረብ ረገድ ጠንክሮ እየሰራ ነው። ኪራይ ሰብሳቢዎች በማንኛውም መንገድ ልማታዊ አካሄድንና ልማታዊ ባለሃብትን ለማቀጨጭ ይጥራሉ። የበርካቶችን ዕድል እያጨናገፉ በሃብት ላይ ሃብትን ማካበት ዋና ዓላማቸው በመሆኑ ምንጊዜም አይዘናጉም።

በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሥልቶች እየነደፉ ሥርዓቱን መፈታተናቸው የማይቀር ሃቅ ነው። ስለሆነም ይህንን እንቅስቃሴና የሥልቶች መቀያየር እየተከታተሉ ማምከንን ይጠይቃል።

በልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚና  በኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መካከል ያለው የከረረ ትግል በልማታዊ ባለሃብቱ ድል አድራጊነት ከተጠናቀ የአገሪቱ የልማት ጎዳና ስኬት ይረጋገጣል። 

ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢውን መድፈቅ ካልቻለ ግን አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና በዕድገት ጎዳና ለማሰለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ጥላሸት መልበሱ አይቀሬ ነው።

የማታ…የማታ ደግሞ የበላይነቱ ሥር እየሰደደ የሚሄድ ከሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት ወደ ከፋ ደረጃ ይደርሳል፤ ኅብረተሰቡ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት ስለማይችል የታየው የብርሃን ጭላንጭል ፈተና ላይ ይወድቃል።

የተባላሹ አሠራሮችን የመለየትና በተበላሹ አሠራሮች ውስጥ ገብተው የግል ተጠቃሚነታቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች፣ ደላላዎችና ሹመኞችን  በመከታተል፣ በመመርመርና በማጥናት ለህግ ቀርበው ተገቢውን ርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ በቢሊዮን የሚቆጠር የአገርና የህዝብ ሀብት ከብክነት የዳነበት አጋጣሚ በርካታ ነው።  

መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናንና ለመዋጋት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ዳር ለማድረስ የሚካሄደውን ትግል ህዝቡ በባለቤትነት ሊመራው ይገባል። እስካሁን ያለው ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ መጪው ትውልድ በሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ታንጾ  ሙስናን የማይሸከም ለማድረግ ጥረቶች ሊጠናከሩ የግድ ነው።

ኪራይ ሰብሳቢነትን በግላጭ የሚዋጋ፣ ራሱንም ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳና ሙሰኝነትን የሚፀየፍ ኅብረተሰብ መፍጠር የልማቱ መቀጠልና አለመቀጠል አንድ ወሣኝ አካል ነው። ይህንን መሠረት ለመፍጠር መንግሥት አመቺ ሁኔታ አዘጋጅቷል። ይህንን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ሁሉም በአንድነት  የተጠናከረ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል። ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለሙስና ትግሉ ስኬት ኅብረተሰቡ መገለጫዎቹን ለይቶ ማወቅና በዚያ ልክ መተግበር ይኖርበታል።  

ከእንዲህ ዓይነቱ የአገርና የህዝብ ጠንቅ ለመቆጠብና ሌሎችንም ለመከላከል መሠረታዊ ባህሪያቱንና የተለያዩ ገጽታዎቹን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት በትምህርት ቤቶች የሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ ትምህርቶች እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

የሙስና መሠረታዊያን  መገለጫዎች ከሚባሉት  አንዱ በየደረጃው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ሊያገለግሉት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ህዝብ ላይ ጉዳይ ለማስፈፀም በሚል የሚቀበሉት ጉቦ ነው፡፡

የዚህ ዓይነቱ ሙስና በአንድ አገር የፍትህ መጓደል ያለውን አደጋ ያሳያል። ሁሉም ዜጋ ነጻ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ሲገባው ያለአግባብ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረግበት ሁኔታ ይፈጥራል። ሌላው አስከፊ ገጽታ ደግሞ በኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች የሚፈፀም ነው። እነዚህ ባለሃብቶች በህገ ወጥ  መንገድ በሃብት ላይ ሃብትን ለማካበት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። እነዚህ ወገኖች ለሚያደርጉት መጠነ ሰፊ ህግን ያልተከተለ የገንዘብ እንቅስቃሴ ህጋዊ  ከለላን ለማግኘት ከመንግሥት አካላት ጋር የሚዋዋሉት ጉዳይ ነው።

ይኼኛው የኪራይ ሰብሳቢነት ገጽታ ወይም  የሙስና መረብ የህዝብ ኃላፊነት የያዙ ግለሰቦችን በገንዘብ ኃይል በማማለል በአገሪቱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴን በማስፋፋት ከሀብት ላይ ሀብትን የማደለብ ተግባር  ነው፡፡

ከሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ዋና ኦዲተር በጂቡቲና በደረቅ ወደቦች የተከማቹ ንብረቶችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ እንዲካሄድ መወሰኑ ይበል የሚያሰኝ ነው። የምርመራ ውጤቱ የሚለያቸው አጥፊዎችም በህግ ይጠየቃሉ ብሏል – ጅማሮው መልካም ነውና ይበልጥ ይጠናከር እላለሁ።