የአጎራባች ሕዝቦች ሁለተኛዋ አገር/ ዘአማን በላይ/
የምስራቅ አፍሪካ አገራት በጦርነት ውስጥ ያለፉ ናቸው። አንዳንዶቹም ዛሬም ድረስ የጦርነት ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ነው። በዚህም ሳቢያ የእነዚህ አገራት ህዝቦች ትውልድ ቀያቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። ነው። እንደ ኤርትራ ያሉ ህዝቦች ደግሞ በውስጣቸው ካለው የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ እጦት ሳቢያ አገራቸውን በመተው በየብስና በባህር ይነጉዳሉ። ይሁንና የቀጣናው አገራት ህዝቦች ዛሬ ላይ ሩቅ ከማለም ይልቅ በአጎራባቻቸው አስተማማኝ ሰላም ያላትን ሀገር እየመረጡ ነው—ኢትዮጵያን።
ይህ የሆነበትም ምክንያት ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የምትጨነቅ ብቻ ሳይሆን፤ በተግባርም የኢፌዴሪ መንግስት የህዝቦችን ሰላምና ደህንነትን የሚያስጠብቅ የስደተኞች ፖሊሲን ስለሚከተል ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ800 ሺህ በላይ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ይህ የሀገራችን ተግባርም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላታል።
እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡና የሚጨነቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።
ይህ ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ሀገር የምትቆጠር ሆናለች። የህዝቦችን ችግር የሚገነዘብ መንግስትና እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ ያለባት ሀገር በመሆኗ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች መጠለያ ሆናለች።
ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ ማንኛውም መንግስት ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ውጭ የሚያስበው ነገር የለውም። ይህ በመሆኑም የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች የራሱ ህዝቦች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ሳይቀር እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ለዚህም የኤርትራ ስደተኞችን በምሳሌነት ማንሳት እችላለሁ። የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት በሚያደርስበት ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በገዛ ሀገሩ ውስጥ የመኖር ዋስትና በማጣቱ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋል። ከእነዚህ ውስጥ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ ህፃናትና ወታደሮች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጠባቸው በገዛ ህዝቡ ላይ “ተኩሰህ ግደል” የሚል ፖሊሲን የሚከተለውና የቀጣናውን ሀገራት የሚያሸብሩ ኃይሎችን በጉያው ውስጥ አቅፎ አካባቢውን ከሚያተራምሰው ከአስመራው አስተዳደር ጋር እንጂ፤ ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ጠብ የለውም።
ይህ በመሆኑም ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማር እየተደረገ ነው። በእኔ እምነት ይህ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አቋም፤ ምን ያህል የህዝቦችን መከራና ስቃይ እንደሚገነዘቡ፣ ምን ያህል የጎረቤታቸው ህዝቦች የሰላም እጦት የራሳቸው ጭምር መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ምን ያህል ለጎረቤቶቻቸው መድህን ሆነውና የቀጣናው ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ ያላገኙትን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያገኙ በጋራ እናድጋለን ብለው በቁርጠኝነት እንደሚያምኑ የሚያሳይ ነው።
ምዕራባውያን የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ አገራችን እንዳይገቡ በማለት በሚከለክሉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ባይኖራቸውም ባላቸው አቅም የህዝቦችን ችግር እየተጋሩ መሆኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት አድናቆት ቢቸራቸው የሚገርም አይደለም።
ህዝብና መንግስት ‘ስደተኞቹ ባይቸገሩ አገራቸውን ጥለው አይመጡም’ በሚል ሚዛናዊና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያለውን ከማካፈል ባሻገር፤ ስደተኞቹ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲሳተፉ እያደረጉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊነት ከውስጣዊ ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች እያደረጉ ያሉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከመደነቅ ባሻገር፣ ተገቢው ትብብርም ሊደረግላቸው የሚገባ ይመስለኛል።
ያም ሆኖ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ችግር የሚካፈሉት ድጋፍ እንዲደረግላቸው አይደለም—ለህዝቦች ካላቸው ፅኑ ፍቅርና የአገራቱ ዜጎች በየአገራቸው የተፈጠረው ችግር እስኪረጋጋ ድረስ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመቁጠር ቢኖሩ ቀጣናውን የማረጋጋት አካል ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ እንጂ። በመሆኑም ሀገራችን ለውስጧ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት የቀጣናውን ሀገራት ህዝቦች የሰላም እጦትን ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው። በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በየብስ፣ በባቡርና በሌሎች የመሰረተ-ልማት አውታሮች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው። እናም መንግስት የቀጣናው ህዝቦች መቸገር አገራችን እንዲኖር የምትሻው ቀጣናዊ የልማት ትስስር እንዳይኖር ያግዳል ብሎ ስለሚያምንም ጭምር ይመስለኛል።
ታዲያ ይህን የትስስር ሁኔታ ሲከውን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሁለት መሰረታዊ ሁነቶችን ተከትሎ ነው—ውሰጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን። መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።
በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል። በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም የማስገን፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን እውን የማድረግ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ተግባሮችን ከውኗል።
አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።
ታዲያ ይህ እንዲሆን መንግስት ከራሱ አገር ህዝቦች አልፎ ለአጎራባች አገራት ህዝቦች ማሰብ ይኖርበታል። በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበት ሰፊ ጥረት አድርጓል። በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የቀጣናውን ዜጎች በስደተኝነት ተቀብላ በማስተናገድ ጊዜያዊ እፎይታን እንዲያገኙ ትብብር በማድረግ ላይ ትገኛለች።
አገራችን በምትከተለው ይህ የትብብርና የህዝባዊነት ማዕቀፍ አብዛኛዎቹ አጎራባች አገራት ኢትዮጵያን እንደ ራሳቸው አገር እንዲቆጥሯት አድርጓል። በእርስ በርስ ጦርነትም ይሁን አገራቸው ውስጥ ባለው የግፍ አገዛዝ ምክንያት በቀዳሚነት የሚመርጧት አገር ሆናለች። በዚህም ሳቢያ ስደተኞቹ ኢትዮጵያን “ሁለተኛዋ አገራችን” ሲሏት ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር በገዛ አገራቸው ውስጥ የመኖር ያህልም ይቆጥራሉ። መጪ ተስፋቸውንም ከዚህችው ባለ ተስፋ ሀገር ጋር የሚያቆራኙ ጥቂት አይደለም።
ምንም እንኳን ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞችን መያዝ ለኢትዮጵያ ቀላል ባይሆንም፤ ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ ክቡር ነውና የአገራችን መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች የሚያደርጉት ክብካቤ ይበል የሚያሰኝ ነው። እናም ነገም ቢሆን ኢትዮጵያ ለአጎራባቾቿ የክፉ ቀን መጠለያ ብቻ ሳትሆን፤ እንደ አገራቸው የሚሰሩባትና የሚማሩባት ከፍ ሲልም ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር መሸጋገሪያ ሆና እንደምትቀጥል በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።