Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

0 382

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የኢትዮጵያን አፍሪካዊ ሚና የሚያሳይ ዩኒቨርስቲ
ዳዊት ምትኩ
በቅርቡ በታሪካዊቷ አድዋ ላይ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል። ቀደምት አባቶቻችን በነጮች በጥቁር አፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፋሽሽቶችን ድል ባደረጉበት አድዋ ላይ ይህ ዮኒቨርስቲ እንዲገነባ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎችና ተወካዮቻቸው ተገኝተዋል። የግንባታው መሰረት ድንጋይ እንዲጣል መደረጉ ሀገራችን ለአፍሪካ ያበረከተችውና እያበረከተችው ያለውን አስተዋፅኦ የሚያሳይ ይመስለኛል።
ይህም በቀደምት ዘመናት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ መሆኗ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ እንዲወጡ በፋና ወጊነት መንቀሳቀሷና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካዊያን ድምፅ በመሆን እየተጫወተች ላለችው ሚና እውቅና የሰጠ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የሆነውን ድርጅት ከማዋለድ ጀምሮ በማሳደግና ወደ ኅብረትነት እንዲቀየር በማድረግ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች።
ሀገራችን እንደ መስራችና እንደ ዋና መቀመጫነቷም የትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ይሁን የቱም በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። አለመግባባትና ግጭቶች ሲከሰቱም በማብረድ ረገድ ተሳትፎዋ ቀላል አልነበረም።
ይህ ብቻ አይደለም። በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ ኖራለች። ኢትዮጵያ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በማውጣትና አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግም መቀየቷ አይዘነጋም።
ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ እንደነበር ይታወቃል። በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት ታደርጋለች። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች።
ሀገራችን ከላይ በተገለፀው መልኩ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቷ ሲወሳ መሪዎቿም አብረው መነሳታቸው አይቀሬ ነው። እንደሚታወሰው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውልደቱ በአፄ ኃይለሥላሴ የስልጣን ዘመን ነበር። መንግስቱ ኃይለማሪያም በሚመራው አምባገነናዊው የደርግ ስርአት ወቅትም ድርጅቱ የራሱን የታሪክ ሂደት አሳልፏል።
ታዲያ በእነዚህ የመንግስት ስርአቶች የነበሩት እውነታዎች በሚታወሱበት ወቅት ያለፉት ገዢ መደቦች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው የማይመቹ፣ በጨቋኝነታቸውና በበዳይነታቸው ይታወቁ የነበሩ ቢሆኑም፤ በአፍሪካ ጉዳይ ግን ጠንካራ አቋም እንደነበራቸው አይዘነጋም።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጠንካራ አህጉራዊ ድርጅት እንዲሆን ወደር የሌለው ሚና እየተጫወተች ነው። በህብረቱ ውስጥ በሚነሱ ወሳኝ አጀንዳዎች ዙሪያ አባል ሀገራት በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገች ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በፈጠሩት ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት የተጫወቱት ሚና እንዲሁም የአፍሪካ ድምፅ በዓለም መድረኮች እንዲሰማና አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰላም እና የፀጥታ እንቅስቃሴዎች ተገቢውን ትኩረት እንድታገኝ ማድረግ የቻለች የአፍሪካ ባለውለታ ናት።
ዓለማችንን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ የሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥና ጫናውን በፍጥነት ከመግታት አኳያ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ መስመር እየተመራች መላው የአፍሪካና የዓለም ሀገራት በዚህ መስመር እንዲጓዝ ማመላከት ችላለች። ለዓለም ሙቀት መጨመር የአፍሪካ ሀገራት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አነስተኛ መሆኑን በየመድረኩ በማስታወቅ የጉዳት ካሳ እንዲያገኙ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከማስተጋበት እስከ መምራት የደረሰች ሀገር ናት፡፡
የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ማረጋጋት ቀላል ነገር ባይሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ አካሄዶችን በብቃት በመወጣት ያጋጥሙ የነበሩ ፈተናዎችን በድል እየተወጣች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጰያ አሸባሪነትና አክራሪነት በቀጣናው እንዳያቆጠቁጥና ምሥራቅ አፍሪካ ከጽንፈኞች ሥጋት ነፃ እንዲሆኑ ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ናት።
ከዚህ በተጨማሪ ከደርግ ግብዓተ-መሬት በኋላ ሰላም መርሁ የሆነው መንግስታችን አፍሪካዊ አስተዋጽኦውንና ሃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ ዛሬም ድረስ እየተወጣ ነው። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሠላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን አስችሏል።
እ.ኤ.አ. አዲሱ ሚሌኒየም ሲጀመር በቡሩንዲ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ውስጥ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሠላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ ባለፈው የአውሮፓውያን አስርት መጨረሻ ዓመታት ላይ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ተሳትፎ ወደር አልነበረውም። በሀገሪቱ ሠላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሚናውን ተጫውቷል።
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሠላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በማሰማራት በዓለም- አቀፍ ደረጃ የአፍሪካን ስም ያስጠራች ናት። በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትንና አክራሪነትን እንዲሁም አሸባሪነትን በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች። ዛሬ በዘያች ሀገር መንግስት እንዲመሰረት የሀገራችን ጥረት ከፍተኛ ነው።
እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ከዚህ ባለፈም በሞሮኮና በአልጄሪያ፣ ናይጄሪያ ውስጥ የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲሁም በሱዳን የቤኛኛ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ መንግሥታት ጋር የነበራቸውን ግጭት በመፍታት ታሪካዊ አስተዋጽኦ ማበርከቷም የሚዘነጋ ሃቅ አይደለም። ሀገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህም በአርአያነት የምትታይ ሀገር ሆናለች። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው። የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማ ወደ ማጽደቅ ሂደት በመግባት ላይ ነች። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም መጥቀም መሆኑ ታውቆላታል።
በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልት (ኔፓድ) በንቃት ተሳታፊ ናት። በታላቁ መሪያችን በአቶ መለስ ዜናዊ ወቅትም ይሁን በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት ኔፓድ ውስጥ ወሳኝ ተሳታፊ ናት። ይህም አፍሪካውያን የረሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ያደረገ ነው። በጥቅሉ ከቀደምት አባቶቻችን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችው አስተዋፅኦ፤ በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ለጠቀስኳቸው ሚናዎቿ እውቅና መስጠት ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy