CURRENT

40 ሺህ ሰዎች ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ የጉዞ ሰነድ ወስደዋል

By Admin

May 27, 2017

ቁጥራቸው 40 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፥ የተመላሾችን ጉዳይ ለማፋጠን የሚያስችል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ተመላሾችን ጉዳይ በፍጥነት ለማከናወን ያስችል ዘንድም 12 ዲፕሎማቶች በዛሬው እለት ወደ ስፍራው መላካቸውንም ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

በስፍራው ለሶስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ውርቅነህ ገበየሁ ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል።

የአየር መንገዱ ስራ አስፈጻሚም ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመመደብ እንዲያስችል በስፍራው ያለውን ሁኔታ የሚያጠና የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው ለመላክ መስማማታቸውንም አቶ መለስ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እዛ ሀገር ለወለዱ እና ለልጆቻቸው የዘረመል (ዲ.ኤን.ኤ) ምርመራ ለሚያስፈልጋቸው ምርመራው በአጭር ጊዜ እንዲከናወን ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር ከስምምነት ላይ መድረሱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰራተኛ እና አሰሪ ስምምነት መፈረሙም አሁን ከሀገሪቱ እየወጡ ሰዎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ተመልሰው እንዲሄዱ የሚኖረው አስተዋዕኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይም መሰል ስመምነቶችን ለመፈፀም እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ እና ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ቃል አቀባዩ ጥሪ አቅርበዋል።