Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አይደሉም፤ ግን ሰርቶ መለወጥ ይቻላል!

0 475

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አይደሉም፤ ግን ሰርቶ መለወጥ ይቻላል!

                                                        ደስታ ኃይሉ

ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዊያን  እንደሚኖሩ መረጃዎች ያስረዳሉ። በርካቶች ህጋዊ የስራ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ የለሌላቸው ናቸው። እነዚህ ዜጎች በሳፁዲ መንግስት የተሰጣቸው የምህረት ጊዜ አዋጅ በአግባቡ ተጠቅመውበታል ለማለት አያስደፍርም። በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ሰብዓዊ ክብራቸው ሳይነካ፣ ንብረታቸው ሳይወረስ፣ የከፋ እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው መመለስ መቻል ይኖርባቸዋል።

ዛሬ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ ሁኔታ አለ። እንደማንኛውም ታዳጊ ሀገር አገራችን ውስጥ ያለው ሁኔታ ምንም እንኳን አልጋ በአልጋ ነው ባይባልም፤ መንግስትና ህዝቡ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። መንግስት ማንኛውም ዜጋ በአገሩ ሰርቶ መቀየር እንዲችል ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሰርቶ መለወጥ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በርካታ ዜጎች ከምንም በመነሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እየቀየሩ ነው። ከሳዑዲ ተመላሽ ወገኖቻችንም አገራችን ውስጥ ያለውን ሰርቶ የመለወጥ ነባራዊ ሁኔታ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ስደት ዜጎችንና አገርን የሚያዋርድ ተግባር ነው። እንደሚታወቀው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለየ መልኩና በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ የሚቻልበት መንገድ እያለ ስደትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸው የሚታበይ አይደለም። እርግጥ ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር የሁሉም ታዳጊ ሀገሮች ችግር ነው። እናም ሀገራችንም በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷ እንዲሁም የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ ናት። በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ- ወጥ የስዎች ዝውውር ወይም ስደት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የዜጎቻችን መዳረሻ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል።

የህገ-ወጥ ዝውውሩ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ወጣት ሴቶችና ወንዶች በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እነዚህ ዜጎች ውጭውን እንጂ ውስጣቸውን በቅጡ ማማተር ያልቻሉ ይመስለኛል። በዓለማችን ካለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የትኛውም ሀገር ማርና ወተት የሚዘንብበት አለመሆኑን በበቂ ሁኔታ የተገነዘቡ አይመስለኝም። እርግጥ በህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከፊል ዕውነታ ያለው እሳቤ ሊሆን ይችላል። የተሟላ አስተሳሰብ ነው ማለት ግን አይቻልም።

እርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ይገባኛል። ይሁንና የችግሩ መንስዔ ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻሉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ-ወጥ ደላሎች ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡

በላቡና በወዙ ጥሮ…ግሮ ህይወቱን ለመለወጥና ሀገሩን ለመጥቀም የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ ሲቻል ህገ- ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ አግባብነት ያለው ተግባር አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ዕድገቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ልማታዊ ሥራዎች ላይ በመሳተፋቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ለመዳን ችለዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየረዱ ነው። ይህ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ነው።

ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ ግልፅ ነው።

ባለፉት ጊዜያት የመንግስትን ጥረት በማድነቅ ለተግባራዊነቱ ‘ጨርቄን ማቄን’ ሳይሉ ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ዜጎች እንደነበሩ ሁሉ፤ ጥረቱን በማንቋሸሽ ስራ ላይ ተጠምደው የከረሙም ጥቂት ወገኖች መኖራቸው አይካድም፡፡

በእርግጥ የእነዚህ ወገኖች አሰላለፍ ይለያል። ምክንያቱም ከአሮጌውና ከኋላ ቀሩ የስራ ጠባቂነት መንፈስ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው። ይህ እሳቤ ግን በዘመነ አስተሳሰብ በሚጓዘው ወጣት ትውልድ ውስጥ ቦታ ያለው ሆኖ አልተገኘም።

እናም መንግስት የቀየሰውን አዲስ የስራ ባህል በተግባር በመተርጎምና ያገኙትን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር ለመሆን የበቁ ዜጎቻችን ሊፈጠሩ ችለዋል። በአንፃሩ ደግሞ ለጥቂት አፍራሽ ሃይሎች አሉባልታ ተንበርክከውና ወደ ውጭ በማየት የማያውቁትን ሀገር ሲናፍቁ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

እርግጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅቶ በሀገር ሰርቶ ማደግና መለወጥ እየተቻለ የአጭበርባሪ ደላላዎች ሲሳይ ሆኖ ለችግር መጋለጥ አሳዛኝ ቢሆንም፤ አሁንም አልረፈደምና ዕውነታውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለአብነትም ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውጭ ባሉ መደበኛ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 840 ሺህ የሚሆኑ እንዲሁም በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ በድምሩ 1 ነጥብ 4 ሚሊዩን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ይህ ዕድልም ወደፊት ወጣቶችንና ሴቶች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። ይህ ማለት ግን ከስደት ተመላሾችም ይሁኑ ወጣቶች እዚህ አገር ውስጥ ያለው ሁኔታ አልጋ በአልጋ አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ስራ ለመጀመር የወኔ ቁርጠኝነትና በራስ ስራ ፈጠራ ለማደግ ፍላጎቱ ሊኖር ይገባል። ሆኖም መንግስትና ህዝብ የፈጠሩት ምቹ ሁኔታ ሊያሰራና ራስን መቀየር የሚያስችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy