Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህገ መንግስቱን ማክበር ይገባል!

0 588

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህገ መንግስቱን ማክበር ይገባል!

                                                        ታዬ ከበደ

ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እያካሄዱ ነው። የፓርቲዎቹ ድርድር ለፖለቲካ ምህዳሩ መጎልበት ያለው ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ፓርቲዎቹ የሚደራደሩት በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኑ ይህን ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸውን ህገ መንገስት ሊያከብሩት ይገባል።

ዛሬ ህገ-መንግስቱን ማክበር ራስን እንደ ማክበር የሚቆጠርበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሠላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ሺህዎች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሠላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ ቆሟል፡፡

እነዚያ አስከፊ የህይወት ጉዞዎች ተገትተዋል፤ ጨቋኙ አምባገነናዊ ሥርዓት ምሱን አግኝቶ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ መንገስ አብቅቷል፤ የመንግሥት ሥልጣን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚረከቡባት ሀገር መፍጠር ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሠላምና ዴሞክራሲ መሠረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና እኩልነት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የፀና እምነት ተይዟል፡፡ ፍሬውንም መቋደስ፣ ፅዋውንም ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻ መሠረቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በደም ቀለም በተጻፈ ቃል ኪዳን ያፀደቁት የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ነው፡፡

እርግጥ ላለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማጎልበት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአንድነት ተነሳስተዋል፡፡ በብዝኃነት ላይ መሠረቱን የጣለው አንድነት ለህዳሴውም ስኬት መገለጫ ነውና የዜጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግሥት ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በፅናት ቆሟል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ሁለት አሥርት ዓመታትን ተሻግሯል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ህብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡

በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አኳያ ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡

ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ሕዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ  ይገኛል፡፡

የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም የመጀመሪያው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ህዝቡን  በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል። አጥጋቢ ውጤትም ተገኝቶበታል። እየተተገበረ ያለው ሁለተኛው የልማት ትልምም ይህንኑ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግር መልኩ ተቀይሶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። የላቀ ውጤትም ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ እያደረገ ያለው ህገ መንግስት በሁሉም የሀገሪቱ ትግበራዎች ሊከበር ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በህገመንግስቱ አግባብ የተቋቋሙ በመሆናቸው በድርድራቸው ህገ መንግስቱን ሊያከብሩ ይገባል እላለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy