Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለህዳሴያችን ጉዞ ሥምረት የጋራ ጥረት

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለህዳሴያችን ጉዞ ሥምረት የጋራ ጥረት

አባ መላኩ

 

ህዝብን የሚያማርሩ የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን ማስወገድ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። የመልካም አስተዳደር መጓደል ለበርካታ ችግሮች መፈልፈል ምክንያት ይሆናል። ጥቂቶቹን እንጥቀስ። የመልካም አስተዳደር መጓደል የኪራይ ሰብሳቢዎች ፖለቲካል ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ በር ይከፍታል፤ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር ሥጋት እየሆነ የመጣው አክራሪነትንና አሸባሪነትን እንዲስፋፋ ያደርጋል፤ ለትምክህትና ጠባብነት መስፋፋትም በር ይከፍታል። ወደአገራችን መለስ ስንል ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦት ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ እየተመዘገበ ላለው ኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ይሆናል።

አሁን…አሁን የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ከልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የሁሉም መነጋገሪያ አጀንዳ ሊሆን የግድ ይላል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በርግጥ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ይበልጥ ከፍ ሊል ይገባዋል። መልካም አስተዳደር የኢኮኖሚ ዕድገቱን ያህል ረጅም ርቀት አልተጓዘም ካልተባለ በቀር ጨርሶ ምንም አልተሰራም ለማለት ደግሞ ያዳግታል። በተለይ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በመደረጉ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ መብቱን የሚጠይቅ ኅብረተሰብ መፍጠር ተችሏል።

መልካም አስተዳደርን ማስፈንን በተመለከተ ኢሕአዴግ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በተደጋጋሚ ነግሮናል። ከመንገርም አልፎ እስካሁን የተጓዘባቸውን ሂደቶች መመልከቱ በቂ ነው። አምባገነኑን ሥርዓት ለመገርሰስ የተከፈለው መራራ ትግል የህዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ነው። ታዲያ ኢሕአዴግም ሊመሠረት የቻለው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነት በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ነውና።

አያሌዎች ለከፈሉት የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ምሥጋና ይግባቸውና ዛሬ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በተጨባጭ ልትመሰረት ችላለች። የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ከጊዜ ጋር የሚያድግ ነው፤ ሂደት ነው። ካለፉት ተሞክሮዎች ስንነሳ ኢሕአዴግ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ሰፋፊ ችግሮችንና የህዝብ ብሶቶችን ለይቶ የመቅረፍ ተሞክሮ ያለው ፓርቲ ነው።

የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ከታችኛው የመንግሥት እርከን አንስቶ እስከ ላይኛው ድረስ በርካታ ተግባራትን መከወን እንዳለበት ይታመናል። በዚህ ረገድ በርካታ በጎ  ርምጃዎች ተወስደዋል። ለመልካም አስተዳደር መስፈን ከላይ ያለው የመንግሥት አካል የቱን ያህል ቁርጠኝነት ቢኖረውም ከኅብረተሰቡ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው የታችኛው እርከን አስተዳደር ራሱን እያረመ ካልሄደ በቀር ዘላቂ መፍትሄ አይመጣም።

 

በዚህ ረገድ የታችኛው እርከን ላይ ያሉ የሕዝብ ምክር ቤቶች የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ በቅርበት የሚከታተሉበት ሥርዓት በመዘርጋት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው ስለመወጣታቸው በየወቅቱ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል።  

 

በሁሉም መስክ ዜጎችን ቅሬታ ውስጥ የሚያስገቡ እና የልማቱ እንቅፋት የሆኑ አድሎአዊ አሠራሮችንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመሳሰሉ ብልሹ አሠራሮችን መዋጋት ለነገ የሚባል አይደለም። የህዝቡን ተሳትፎ በሁለንተናዊ መልኩ በማሳደግ እየተመዘገበ ላለው ዕድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ የአገራችንን ህዳሴ ማፋጠን ይኖርብናል። እዚህ ላይ በዋነኛነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የአገራችን ህዳሴ እውን የሚሆነው በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ ሲታከልበት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል።

 

ኢሕአዴግ ከሌሎች የአገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚለይበት ዋነኛ ባህሪው ውጤት ያመጣባቸውን ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በታሰበው ልክ ውጤት ያልተመዘገበባቸውን ጉዳዮች ለኅብረተሰቡ በግልጽ የሚያሳውቅበት አሠራርን መከተሉ ነው። ድክመቶቹን ለይቶ በማውጣት፣ ጉድለቶቹን ለመድፈን የማያመነታ ፓርቲ ነውና።  

 

እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚገባው ቁም ነገር ኪራይ ሰብሳቢነት ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም የአንድነት ህልውና ሥጋት ላይ የሚጥል መሆኑ ነው። ዛሬ ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት የዓለማችን ችግር መሆኑ ቢታወቅም ከድህነት በፍጥነት ለመውጣት በርካታ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ላሉና ኢትዮጵያን ለመሰሉ አገሮች ውጤቱ የከፋ ነው። ባለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያ በተከተለችው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዜጋው ግዴታውን ብቻ ሳይሆን መብቱንም ጠንቅቆ በማወቁ ኢሕአዴግ በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ለተያያዘው ጉዞ መልካም ግብዓት ሊሆነው ችሏል።  

 

ኪራይ ሰብሳቢነት፣ አክራሪነት፣ አሸባሪነት ትምክህትና ጠባብነት ለአገራችንና ለህዝባችን የማይበጁ ሁሉም በጋራ ሊታገላቸው የሚገቡ የአገርና የህዝብ ጠላቶች ናቸው። በአገራችን መልካም አስተዳደር እንዲጎለበት ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ትልቅ ጉልበት ያለው በመሆኑ ችግር በገጠመ ጊዜ ሁሉ ተማርሮ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በያገባኛል ስሜት መታገል ይኖርበታል። ኅብረተሰቡ መብቱን ከማስከበር ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አጋልጦ የመስጠት ልምዱን በማጎልበት ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርበታል።

 

ባለፉት ዓመታት መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን በመላ አገሪቱ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ከመቻሉም ባሻገር ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ በአገሪቱ ይታይ የነበረውን የድህነት መጠን መቀነስ ተችሏል። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት ያህል በመልካም አስተዳደር ረገድ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ መሆን አልተቻለም። ይሁንና በመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በጥልቀት ፈትሾ በብቃት ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠው መተግበር ጀምረዋልና እሰየው ያሰኛል።  

 

በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ባለው ቁርጠኛ አቋም ሁሉም ዜጋ ከጎኑ በመሰለፍ ሊያግዘው ይገባል። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመንግሥት ቁርጠኝነት ወይም በመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ብቻ ሊፈቱ አይችሉምና። በመሆኑም የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን በመረዳት ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል።  

 

ምንም እንኳን አገራችን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጀማሪ ትሁን እንጂ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በርካታ መልካም ተግባራትን ማከናወን ችላለች። ይሁንና አሁንም የበለጠ ልናጎለብታቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ። የአገራችንን የለውጥ ጉዞ መሠረት ያስያዘውና ህዳሴያችንን እያፋጠኑ የሚገኙት የመጀመሪያው እና የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችና ትግበራቸው ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጦች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው። የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችሉ መሠረቶቻችን ናቸው።  

 

መንግሥት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚን በማጠናከር የህዳሴ ጉዟችን ዋነኛ አቅጣጫ በማድረግ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል። ውጤቶችም ተገኝተውበታል። በዚህም በገጠር የልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት እየያዘ ቢመጣም  በከተሞች አሁንም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ሙሉ ለሙሉ ማክሰም አልተቻለም። በዚህም የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ተስተውለዋል።

በከተሞች የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ሆነው የተለዩትን የመሬት፣ የግብር ኣሰባሰብ የመንግሥት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጿል። በእነዚህ ዘርፎች የተገኙ ልምዶችን በመቀመር ለመልካም አፈጻፀም ልንጠቀምባቸው ይገባል። የአገራችን ህዳሴ ከታሰበበት ሊደርስ የሚችለው በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ ጥረት ብቻ ሳይሆን በመላው ኅብረተሰብ ተሳትፎ ነውና ሁሉም ዜጋ ለዚህ ዓላማ መሳካት የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። ለህዳሴያችን ጉዞ ሥምረት የጋራ ጥረት!

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy