Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልዩነት ሊቀነቀን የሚችለው አገር…

0 657

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልዩነት ሊቀነቀን የሚችለው አገር…  

ወንድይራድ ኃብተየስ

አሰዋን  ግድብ  ለግብጻዊያን  ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ፋይዳነት  ባሻገር  የአንድነታቸው ማስተሳሰሪያ እና የአገራቸው ህልውና  አድርገው  ይቆጥሩታል።   ለእኛም   ለኢትዮጵያዊያኖች የታላቁ  ህዳሴው ግድብ  ከኤኮኖሚያዊ ጠቀመሜታው  ባለፈ  ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   የትብብር  መገለጫና የአንድነት ማሳያ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ እውነታ  ነው።   ከዚህም ባሻገር ታላቁ   የኢትዮጵያ  የህዳሴ ግድብ  የብሄራዊ  ኩራታችን  መገለጫና  የገጽታችን  መለውጥ ማሳያ ፕሮጀክት ነው።  

 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት የሚያደረገው በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና የህዝቦችን  የጋራ  ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ  የአገራዊ  ህልውናን   በማረጋገጥ ላይ ነው። የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የአገራችን  የውጭ  ግንኙነት  ፖሊሲ ባለፈው 15 ዓመታት  አገሪቱን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት እንድታስመዘግብ በማስቻሉ ኢትዮጵያ  ከራሷ አልፋ ጎረቤት አገሮች ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ችላለች።  

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት  ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ኤኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ በመቻሏ  የአገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የጎረቤት አገራት ህዝቦችም ጭምር  ከኢትዮጵያ  ዕድገት ቀጥታ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ዛሬ ላይ አገራችን ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን አስጠልላለች። ከቅርብ አመታት ወዲህ አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር የምትቆጠር ለመሆን በመብቃቷ በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን  ሙገሳን ተችሯታል። የኢፌዴሪ መንግስት ከራሱ ዜጎች አልፎ የአካባቢው አገራት ህዝቦችን  በሚችለው ነገር ሁሉ  ተጠቃሚ ለማድረግ  የሚያደርገው ጥረት ሊደነቅ የሚገባው ለሌሎች መንግስታት ተመሳሌት ሊሆን የሚገባው ተግባር ነው።  የውጭ ግንኙነት ፓሊሲ የውስጥ ግንኙነታችን ነጸብራቅ ነው። በውስጡ ሰላም የሌለው መንግስት ለውጩ ዓለም ሰላማዊ ሊሆን ከቶ አይቻለውም።

የአገራችን ኤኮኖሚ በፈጣን ሁኔታ ማደግ ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሰላም ማስከበር፣ ወዘተ  ትስስሩ እየጠነከረ  መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ እጅግ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ዛሬ ላይ አንዷ አገር ለሌላኛዋ የህልወና ምንጭ እስከመሆን መድረሳቸውን መመልከት ይቻላል።  በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም  ከደቡብ ሱደን፣ ሱዳን፣  ኬንያ እንዲሁም ሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጎልበት   የሚያስችሉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለአብነት ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር ማስመር ዝርጋታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣  የሃይል አቅርቦት ወዘተ  በማካሄድ  ነች።

 

ኤርትራ ህዝብም ቢሆን  ኢትዮጵያ ካስመዘገበችው የኤኮኖሚ እድገት ቀጥታ ተጠቃሚ መሆን የቻለበት ሁኔታዎች እንዳለ ማየት ይቻላል። አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት በህዝቡ ላይ በሚያደርሰው ከፍተኛ በደል ሳቢያ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ኤርትራዊያን አገራችን መጠጊያ መሸሺያ  ሆናለች። በምስራቅ አፍሪካ  ያለው  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት  እንዲጠናከር  የኢፌዴሪ መንግስት  ከሚያደርገው የመሰረተ ለማት ማስፋፋትና  ስደተኞች  አቅም በፈቀደ ሁሉ  ከመንከባከብ   ባሻገር  የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ አገራችን የአንበሳውን ድርሻ  በመወጣት ላይ ነች።

 

እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት ከህገመንግስታችን መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም። የኢፌዴሪ መንግስት  ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መሰረት ሲጥል ታሳቢ ያደረገው   በዋነኝነት  የኢትዮጵያን ህዝቦች ተጠቃሚነት ቢሆንም  የአካባቢውን አገሮች  ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትም  ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክትም ነው።  ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አገሪቱ ያለባትን ከፍተኛ የሃይ አቅርቦት እጥረት በመፍታት ለጎረቤት አገሮች በተመጣጣኝ ክፍያ  ሃይል በማቅረብ  የቀጠናው ህዝቦች  በኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲተሳሰሩ ማየድረግ  ዓላማን  ያነገበ ነው።   

 

የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ  ያራምደው የነበረው “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍተሃዊ የውሃ  ክፍፍል” የሚለው መርህ  አሁንም የአገራችን  ጠንካራ አቋም ነው። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለሃይል ማመንጫነት እንጂ ለመስኖ አትጠቀምም፤  ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግብጽ  ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ስፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ በመሆኑ  የህዳሴው ግድብ ለመስኖ ስራ እምብዛም የሚያገለግል ግድብ አይደለም። ይህን ጉዳይ  ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አሳውቃለች። ሱዳን ከኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች በተለይ ከተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት  በመቻሏ  የኢትዮጵያ የልማት ስራዎች  አካባቢውን ሊጠቅሙ የሚችሉና የቀጠናውን  የኢኮኖሚ ትስስሩን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ስትመለከት  ለታላቁን የህዳሴ ግድብ  ፕሮጀክትም  ድጋፉን በተገኘው መደረክ ሁሉ  አረጋግጣለች።

 

የኢትዮጵያ መንግስት ህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት  ይፋ ባደረገበት ውቅት እንደገለጸው አገሪቱ የጀመረችውን  ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት  ለማስቀጠል የሚቻለው  እየታየ ያለውን  ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ ሲቻል መሆኑን በማመን በርካታ የሃይል ማመንጫዎችን በመገነባት ላይ ይገኛል።  የአገራችን ኤኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ በሚያደርገው የመዋቅር ሽግግር  ሂደት ውስጥ ከፍተኛ  የሆነ የሃይል አቅርቦት ይፈልጋል።  በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት አካባቢን የማይበክሉ ትላልቅ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን፤  እንደ ጊቤ ሶስትና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎችን እንዲሁም በርካታ የንፋስ የሃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል። ታላቁ  የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ  ከ6 ሺህ 4 መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጭ ሲሆን ግብፅና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ የሃይል አቅርቦት ከማግኘታቸው ባሻገር  በየወቅቱ  የሚዋዥቀውን የወንዙን የወሃ መጠን በማስተካከል  ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን ላይ በመሆኗ የወንዙ ዘላቂ ህይወት እንዲረጋገጥ ከማድረጉም በላይ ደለልን መከላከል የሚቻልበት ሁኔታን ይፈጠራል።

 

ኢትዮጵያ ቀድማ ይዛ  የተነሳችውን  አቋም ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት አቋማቸው አድርገው ይዘውታል። ይህ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ስታቅድ ጀምራ እስካሁን ባለው ሁኔታ  የግብፅን ወይም ሱዳንን ወይም ሌላ አገርን ጥቅም  ለመጉዳት  አስባ እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። የወንዙ ዘላቂ ህይወት ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ፍተሃዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ሲዘረጋ ብቻ ነው። አንዳንድ  የግብፅ  ፖለቲከኞችና ምሁራን ስለ ህዳሴው ግድብ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው  ወይም  ሆኔታውን ሆን በለው  የፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ሲሉ  ሁኔታውን   አንጋደው ለህዝባቸው በማቅረባቸው   ሳቢያ  በበርካታ ግብጻዊያን ዘንድ ስለ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የተሳሳተ  አስተሳሰብ  እንዲፈጠር አድርገው  ነበር።  ይሁንና  አሁን ላይ  ሁኔታዎች ተለውጠዋል። የግብጽ መንግስትና በርካታ የግብጽ ዜጎች የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት አቋም ውሎ አድሮም ቢሆን በመረዳት ላይ ናቸው።

 

ግብፃዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን  የአገራቸውን  ጥቅም ለማሰጠበቅ     ፍትሃዊ ያልሆነ አካሄድን ህጋዊ ለማድረግ  ሲሯሯጡ አንዳንድ የእኛ አገር ጽንፈኛ ሃይሎች ደግሞ እውነታን በመደፍጠጥ ለመናኛ የፖለቲካ ትርፍ ተንበርክከው ተመልክተናል።  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ዓለም ዓቀፍ መርሆዎችን መሰረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ አንዳንድ ጽንፈኛ ሃይሎች  የአገርንና የህዝብን ጥቅም አሳልፈው  መስጠታቸው ማስተዛዘብ ብቻ ሳይሆን የሚያጠያይቅም ጉዳይ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ አይዲዮሎጂ ወይም የፖለቲካ አተያይ ሊኖረው ባይችልም በአገራችን ዘለቄታዊ ጥቅም ላይ ግን ከቶ ልንለያይ አይገባንም። ልዩነታችንን ልናራምድ የምንችለው  አገር ስትኖር መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው።   

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እቅድ ሲነድፍ የፋይናንስ ምንጭ  ብሎ የለየው የኢትዮጵያን  ህዝብ ነው። እስካሁንም ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በውስጥ ገቢ በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ ነው። ይህ ፕሮጀክት ከሌሎች ፕሮጀክቶቻችን ለየት የሚያደርገው  ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች የሚሸፈን መሆኑ ነው።  

 

እንደተመለከትነው  በአገራዊ ጉዳይና በብሄራዊ ጥቅማቸው ግብፃዊያን አንድ ናቸው። እንግዲህ እኛ ኢትዮጵያዊያን  ከግብጻዊያን ልንማራቸው የሚገቡ እንዳንድ ነገሮች  እንዳሉ ማየት ይቻላል። እስካሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ የግብጽ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ምሁራን ከመንግስታቸው ጎን በመሰለፍ የግብፅን ጥቅም ያስጠብቃል የሚሉትን ነገር ሲያራምዱ አይተናል።  በእኛ ሀገር ግን አንዳንድ ጽንፈኛ የፓርቲ አመራሮች እና የዳያስፖራ ፖለቲከኞች ብሄራዊ  ጥቅማችንን   የሚነካ  አካሄድን  ሲከተሉ ተመልክተናል። መንግስታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ስርዓትም ይለወጣል፤ ነገር ግን አገርና ህዝብ  ቋሚ ናቸው። ሁሉንም በማጃመል፣ በዳበሳና በማጥላላት የፖለቲካ በሽታ  የተዘፈቁ አካላት ራሳቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል። በሁሉም ነገረ ከመንግስት አቋም በተቃራኒው  መሰለፍ የሚቀናቸው የእኛ አገር ጽንፈኛ ሃይሎች አገራዊ ጥቅምንና መንግስትን  መለየት ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy