Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ነው!

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ነው!

                                                   ደስታ ኃይሉ

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ያውቃሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን የለበትም።

ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

ለነገሩ ፅንፈኞቹና ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ ለህዝቡ ያስገኙለት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለም። እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ የሚያመጡለት ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖርም ያውቃል።

የሀገራችን ህዝብ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል። የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም መቻሉ ማሳያ ይመስለኛል።

ከተሃድሶው ወዲህ ባሉት ዓመታት በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ምንም እንኳን በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ስንክሳሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ይገነዘባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በእነዚህ ዓመታት በከተሞች ውስጥ ሲከናወን የነበረው የአገልግሎት ዘርፍ ተደራሽነትም ዕድገት ማሳየቱ የሚታበይ አይደለም። የእነዚህ ሁሉ ዕድገቶች ድምር መሰረታዊ ውጤት ማምጣት ችሏል። ይህ የሚያሳየው መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ልማት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንቀሳቀሱን ነው።

ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለፉት 26 ዓመታት በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይመስለኝም። በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል። ይህም የህገ መንግስቱ ውጤት ነው።

እነዚህ ለውጦች የተገኙት ህገ መንግስቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው። እርግጥ እዚህ ላይ አንድ የማይካድ እውነታ ያለ ይመስለኛል። ይኸውም ባለፉት 26 ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ማደጉና በዚያውም ልክ የወጣቱ ሃይል ቁጥር በመጨመሩ የለውጡ ግዝፈት የተጠበቀውን ያህል ሊሆን ባይችልም፤ ውጤቱ ግን ከፍተኛ መሆኑን መካድ አይቻልም።

እርግጥ አስቸጋሪ ጉዳዮችን በህገ መንግስቱ አግባብ መፍታት ይገባል። ቀደም ካሉት ጊዜያት መማር የሚቻለው ዜጎች የሚደገፉበት መንገድ ካለ ማንኛውንም ጥያቄያቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማቅረብና ሁሉም ችግሮቻቸው እዚህ ሀገር ውስጥ የተገኘውን ለውጥ በባመጣው ህገ መንግስት አማካኝነት ብቻ እንዲፈታላቸው የሚሹ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እናም ይህን የዜጎችን ፍላጎት መደገፍና ማጠናከር የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ የህዝብን ድምፅ መስማትና የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ትላልቅ መድረኮችን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆንም ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን እየገለፀ ከመንግስት አስፈፃሚዎች ጋር ህጋዊ ትግል ውስጥ ይገባል። የሚፈጠሩ የአሰራር ማነቆዎችንም ማስወገድ ይቻላል። ይህም ትግሉ በቁርጠኛ አመራር ከታገዘና ህዝቡ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዩች ውስጥ የሚኖረው የተሳታፊነት ሚና ተጠናክሮ ከቀጠለ ሰላማዊ ትግሉን የሚያጎለብተው ይሆናል።

ሁሉንም ነገር በህገ መንግስቱ መሰረት የማስተዳደር ሁኔታም ሊጎለብት ይገባል። የህገ መንግስቱ መርሆዎች ውስጥ ከሚጠቀሱት አንዱ የራሱ የህገ መንግስቱ የበላይነት  ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ የህገ መንግስት የበላይነት ሲባል፤ በአንድ ሀገር የህጎች የስልጣን ተዋረድ ህገ መንግስት ከሌሎች ህጎች የላቀ ደረጃና ቦታ ያለው ህግ መሆኑን ለማመልከት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። እርግጥም በየትኛውም ሀገር ህገ መንግስት የሁሉም ህጎች ምንጭና ቁንጮ ነው። የህጎች ሁሉ የበላይ ነው። ሁሉም ህጎች ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርገው ነው የሚታወጁት። ህገ-መንግስቱን የሚቃረኑ ማናቸውም ህጎች ህጋዊ ውጤት የሚሰጣቸው አይደሉም፤ ተፈፃሚነትም አይኖራቸውም።  

በዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የህገ መንግስት የበላይነት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ህገ መንግስቱ የህዝብን ፈቃድና ፍላጎት ያዘለ ስለሆነ ነው። የዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት መሰረቱ የህዝብ ፈቃድ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ህገ መንግስት የመንግስት ስልጣን ይዘት ምን እንደሚመስል፣ ስልጣን እንዴት እንደሚደራጅና እንደሚከፋፈል፣ በስልጣን አካላት መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በመንግስትና በዜጎች በህዝብ መካከል ስለሚኖረው ትስስር፣ መንግስት ሊከተላቸው ስለሚገቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መርሆዎች የሚገልፅና በሌሎች ወሳኝ የህዝቡን ህይወት የሚነኩ ጉዳዩች ላይ የሚያጠነጥን ሰነድ ስለሆነ ነው። እናም ህገ መንግስቱን በማክበር የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች በዚያው  ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት ያስችላል።

በመሆኑም የህገ መንግስቱን የበላይነት ማረጋገጥ ማለት የህገ መንግስቱ ባለቤቶች የሆኑት ሕዝቦችን ፈቃድና ፍላጎትን ዕውን ማድረግ ነው። ህገ መንግስትንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን በስራ ላይ የማዋል ሚና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ዋነኛ አካል አካል በመሆኑ፤ የህገ-መንግስቱ መከበር የሁሉም ዜጎች፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተዋንያንን ፍላጎት ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም ከዚህ አኳያ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ናቸው። ይሁን እንጂ እንደ ጀማሪ የዴሞክራሲ ስርዓት አራማጅነታችን ሊቀሩን የሚችሉ ነገሮች መኖራቸው አይቀርም። እናም የሚቀሩንን ጉዳዩች በማስተካከል ህገ መንግስቱን የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ስኬታማነትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት መረባረብ ይኖርባቸዋል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy