Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መፍትሔው ከሀገር ነው!

0 233

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መፍትሔው ከሀገር ነው!

ዳዊት ከበደ

የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የበርካታ ታዳጊ ሀገሮች ችግር ቢሆንም፤ ሀገራችን በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷና የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ ወጥ የስዎች ዝውውር ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የዜጎቻችን መዳረሻ እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገርም ለስቃይና ለችግር እየዳረጋቸው እንደሚገኝም እንዲሁ፡፡

በዚህ ፍልሰት ተዋናዮች በአብዛኛው ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲሁም ህጻናት በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ተገደዋል፡፡ ምንም እንኳን የተደራጀና በቂ ጥናት ባይደረግም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከአንድ መቶ ሠላሳ ሺህ እንደሚደርስ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ጥናት ያመለክታል፡፡

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንደሆነ ሲገልፁ ይደመጣል፡፡ በእርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ጠንቅቄ የማውቅ ብሆንም፤ የችግሩ መንስዔ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻለና ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለደላላ ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን በዓይናችን የምናየውና በጆሯአችን እየሰማን ያለነው ሃቅ በመሆኑ ነው፡፡

እርግጥ ማንም ሰው በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ አባባሌ መላው ህዝባችንና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልጽግናና ኑሮ መሻሻል መሆኑን በአስረጅነት ማጣቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ታዲያ ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን  እጅጉን የሚያስቆጭ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ መበልጸግ ሲቻል ህገ ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ ተገቢ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። በዚህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በግንባታ ሥራዎች ላይ በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው በመሥራታቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ከመዳናቸውም ባሻገር፤ ራሳቸውን የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ማውሳቱ ነገን የምናይበት መነጽር እንደሚሆን የሚያመላክት አንድ ጉዳይን ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።

በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን ነው፡፡

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት፣ ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም “አይኔን ግንባር ያድርገው” ከሚሉ አንዳንድ ሃይሎች በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕውነታውን በገሃድ ስለሚያውቀው ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን የመንግስትን ጥረት በማድነቅ ለተግባራዊነቱ “ጨርቄን ማቄን” ሳይሉ ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ዜጎች እንደነበሩ ሁሉ፤ ጥረቱን በማንቋሸሽ ስራ ላይ ተጠምደው የከረሙም ጥቂት ወገኖች ነበሩ፡፡ በርግጥ የእነዚህ ወገኖች አሰላለፍ ለየቅል መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ከቆየው ኋላ ቀር የሥራ ባህላችን አስተሳሰብ መላቀቅ አቅቷቸው በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትን የሞት ያህል ቆጥረው አሉታዊ ምላሽ የሰጡ ወገኖች የመኖራቸው ሃቅ የሚካድ ባይሆንም፣ የመንግስትን ጥረት በማጠልሸት ተግባር ላይ የተሰማሩ ሃይሎችም ተስተውለዋል፡፡

ህገ ወጥ ደላሎች በሚያካሂዱት ቅስቀሳ ለህገ ወጥ የሰው ዝውውሩ መበራከት እንደ አንድ ምክንያት መውሰዱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ ድህነትን ለማስወገድ የምታካሂደውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚደረግ የተሳሳተ ቅስቀሳ ስለባ ሆነው ውጪውን እንዲያማትሩ የተገደዱ ዜጎች በርካቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተሻለ ስራ ለመፈለግ በሚል ለህገ ወጥ ዝውውር ድርጊት ተጠቂ የሆኑ ዜጎች ምስክርነትን ማድመጥ የቻልን ይመስለኛል፡፡

በዚህ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ኪሳቸውን በማደለብ ተግባር ላይ የተሰማሩ፣ አንዳንድ በስራና ሰራተኛ አገናኝ ስም ቢሮ የከፈቱ፣ በኤምባሲ ሰራተኝነት የተቀጠሩና አየር በአየር በሚል ህገ ወጥ ድለላ ስራ የሚያካሂዱ አካሎች መኖራቸው አይካድም። ታዲያ እነዚህ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሃይሎች ከመበራከታቸውም በተጨማሪ፤ የዜግነት ርህራሄ ያልፈጠረባቸው ወገኖችም ችግሩን አሳሳቢ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

በህገ ወጥ ዝውውር ሁሉም የሀገራችን ክልል ዜጎች የችግሩ ሰለባ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ታዲያ እዚህ ላይ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት አብይ ጉዳይ ለችግሩ መባባስ በዋናነት የሚጠቀሰው ግለሰባዊ ቤተሰብ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለችግሩ ሰለባነት የሚጋለጠው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከዕድሜ ጋር ተይይዞ ለሚመጣ ያልሰከነ ውሳኔን ለመቀልበስ የቤተሰብ ድጋፍ እጅጉን ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በሌላ በኩልም ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግ እንደሚቻል ከወጣቱ ይልቅ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ታዲያ ይህንን እውነታ አሳምኖና አስረድቶ “የላም አለኝ በሰማይ” አስተሳሰብን ከማስረፅ ይልቅ፤ የጉዳዩ ተባባሪ በመሆን የአጋዥነት ሚና ሲጫወት ይታያል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሪታቸውን ሸጠው ሲያንስም ተበድረው ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች በርካታ መሆናቸው ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ የሚገኙ ዜጎች ለከፍተኛ የስነ-ልቦና ችግር ከሚያጋልጣቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውም ይህ ጉዳይ መሆኑ ሲታሰብ ለችግሩ መስፋፋት የቤተሰብ ሚና ግንባር ቀደም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የሳኡዲ መንግስት በሰጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ በመንግስት አኩሪ ጥረት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት ዜጎቻችን መካከል የብዙዎቹ ጭንቀት ‘አገኛለሁ’ ብለው የቤተሰብን ንብረት ሽጠውና ቤተሰብን አስበድረው በባዶ እጅ ወደ ቤተሰብ መቀላቀሉን እንደ ጦር የሚፈሩት ጉዳይ መሆኑን ሲናገሩ በገሃድ ስላደመጥን ነው፡፡

በመሆኑም የችግሩ መንስኤ ከቤተሰብ የሚጀምር በመሆኑ፤ ሁሉም ቤተሰብ የህገ ወጥ ስደትን አደገኛነት ተገንዝቦ መፍትሔው ያለው ከሀገር መሆኑን ማስገንዘብ ይጠበቃል፡፡ እዚህ ሀገር ውስጥ ዛሬ ወጣቶች ሰርተው መለወጥ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ምቹ ሁኔታውን ሊጠቀሙ ይገባል። መፍትሔው ያለው ከሀገር ስለሆነ በሀገር ውስጥ ባለው ምቹ ሁኔታ መለወጥ እንደሚቻል ማስተማር የሚገባ ይመስለኛል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy