Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማረፊያችሁ እሾህ አይደለም

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማረፊያችሁ እሾህ አይደለም

ብ. ነጋሽ

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን ዘንድ የትኩረት ማረፊያ የሆነችው ሳኡዲ አረቢያ ከመጨረሻዎቹ የዓለማችን ደሃ ሃገራት አንዷ ነበረች። ሳኡዲ አረቢያ የሃብትን ጭላንጭል ማየት የጀመረችው በ1930ዎቹ ነበር። ሳኡዲ አረቢያ አሁን ላለችበት የሃብት ማማ ያበቃት ነዳጅ የመፈለግ ስራ የተጀመረው በዚህ ዘመን ነበር። ሳኡዲ አረቢያ የእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ ስፍራ መገኛ በመሆኗ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በድህነት ጊዜዋም ያወቋታል። ታዲያ በድህነት ጊዜዋ ለሃጅ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለሳኡዲ አረቢያ ምስኪኖች በርከት ያለ ዘካ ጭነው ነበር የሚሄዱት። እናም ኢትዮጵያውያን የሃጅ ተጓዦች ለሳኡዲ ምሰኪኖች ሲሳይ ነበሩ። ኢትዮጵያ ከሳኡዲ አረቢያ ዜጎች ጋር ያላት ትውውቅ ከዚህም የቀደመ ነው። እስልምና በሳኡዲ አረቢያ ሲጀመር የነቢዩ መሃመድ (ሶ ወ ሰ) ተከታዮች ከሚያሳድዷቸው ጠላቶቻቸው ለማምለጥ  ወደኢትዮጵያ ሸሸተው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ አረቢያ ዜጎቸ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ነበራቸው።

ከኢትዮጵያውያን ጋር ይህን የሚመስል ትውውቅና ዝምድና ያላት ሳኡዲ አረቢያ በ1970ዎቹ ነዳጅ በገፍ የሚወጣባት ሃገር ሆነች። ሳኡዲ አረቢያ በፔትሮ ዶላር የበለጸገች ሃገር መሆን የጀመረችው በዚህ ዘመን ነበር። ሃብቷ ልክ አጣ፤ ዜጎቿም ናጠጡ። እናም ድሮ ለምስኪኖቿ ዘካ ጭነው ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ ለመመጽወት ይጓዙ ጀመር። ድሮ እንደተስፋ ይታዩ የነበሩት መጽዋች ኢትዮጵያውያን፣ የቤት ሰራተኛ ሆነው ለማገልገል በገፍ ይጎርፉ ጀመር። ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ አረቢያ ዜጎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከዚህ በኋላ መልኩን ቀየረ። ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ አረቢያውያን ዘንድ ዝቅ ተደርገው ይታዩ ጀመር።

ኢትዮጵያውያኑ ግን የስራ እድል ፍለጋ፣ የተሻለ ገቢ በማግኘት ተስፋ ወደሳኡዲ አረቢያ መጉረፋቸውን አላቆሙም። አብዛኞቹ ወደዚያ የሚሄዱት መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ በሚያስቸግር አኳኋን ነው፤ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት እንኳን መብታቸውን ሊያስከብርላቸው የት እንዳሉና ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነም በትክክል አያውቅም።

ከጥቂተ ዓመታት ወዲህ ግን የሳኡዲ አረቢያ ፔትሮ ዶላር እያማለላቸው ወደሃገሯ የሚጎርፉት የውጭ ሃገር ዜጎች እንደቀደሞው አልተመቿትም። በአንድ በኩል በተለይ በአገልግሎት የስራ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩት በርካታ የውጭ ሃገር ዜጎች እያደገ የመጣውን የሃገሪቱን ህዝብ የስራ እድል የሚሻሙ ሆኑ። በሌላ በኩል በተለይ ባለፉ ሶስት አራት ዓመታት የነዳጀ ዋጋ በመውደቁ ምክንያት ሳኡዲ አረቢያ የውጭ ሃገር ዜጎችን መሸከም እየከበዳት ሄዷል። እናም በህገወጥ መንገድ ወደሃገሪቱ ገብተው በህገወጥነት የሚኖሩ የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲወጡላት የሚጠይቅ አዋጅ አውጥታለች። ይህ የውጡልን አዋጅ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም የሚመለከት ነው። የመጀመሪያው አዋጅ ከአራት ዓመት በፊት የወጣ ነበር። ዘንድሮም ተመሳሳይ አዋጅ ወጥቷል። የዘንድሮው አዋጅ በህገወጥነት የሚኖሩ የሌላ ሃገር ዜጎቸ በ90 ቀናት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው። አዋጁ መጋቢት 20፣ 2009 ዓ/ም ነው የታወጀው። በአዋጁ የተሰጠው የጊዜ ገደብ የፊታችን ሰኔ 20፣ 2009 ዓ/ም ያበቃል። አሁን የቀረው ሃያ ቀናት ገደማ በቻ ነው።

በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ250 ሺህ እስከ 400 ሺህ እንደሚደርሱ ይገመታል። የሳኡዲ አረቢያ መንግስት አዋጁን ይፋ ካደረገበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን በክብር ወደሃገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ ወደሃገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው የጉዞ ሰነድ የወሰዱት ሃምሳ ሺህ እንኳን አልሞሉም። ተሳፍረው ወደሃገራቸው የተመለሱት ደግሞ ከአስራ አምስት ሺህ አይበልጡም። እርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጉዙ ሰነድ ወስደው ወደሃገራቸው ለመመለስ በብዛት እየቀረቡ መሆኑ ተነግሯል። የጉዞ ሰነድ ለመውሰድ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መበራከቱን ተከትሎ በወቅቱ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ተጨማሪ ዲፕሎማቶችን ልኳል።

ከዚህ በተጨማሪ የክልል መንግስታት ሰሞኑን የስራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ተወካዮቻቸውን ወደሳኡዲ አረቢያ ይልካሉ። የኤጀንሲዎቹ ተወካዮች ወደሳኡዲ አረቢያ የሚሄዱት በዚያ በህገወጥነት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወደሃገራቸው ቢመለሱ ተዘጋጅቶ ስለሚጠብቃቸው አቀባበልና የስራ እድል ለማሰረዳት ነው። ክለሎች ከሳኡዲ አረቢያ ተመላሾችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት የሚሰራ ግብረ ሃይል አቋቁመዋል። ይህ ግብረ ሃይል እስከቀበሌ የተዘረጋ ነው። በመሆኑም በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ስለሚኖሩት ዜጎች ፍላጎት፣ ስጋትና አጠቃላይ ስነልቦናዊ ሁኔታ በቂ መረጃ አላቸው። በሃገር ቤት የተዘጋጀላቸውን የስራ እድል ስምሪት የሚያስፈጽሙ በመሆናቸው ተጨባጩን ሁኔታ በየትኛውም እርከን ላይ ከሚገኝ የስራ ሃላፊ በተሻለ ያውቁታል። ከዚህ በተጨማሪ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው  ከገጠር አካባቢ የሄዱ የተለያዩ ብሄሮች ተወላጆች በመሆናቸው፣ ከአካባቢያቸው ቋንቋ ውጪ በአግባቡ መግባባት አይችሉም። ይህ ቋንቋ የፈጠረውን የግንኙነት መሰናክል በማለፍ በቋንቋቸው ወደሃገር ቤት እንዲመለሱ የማድረጉን ስራ ሊያሳልጡ ይችላሉ የሚል እመነትም አለ።

በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ሃገሪቱን ለቀው ካልወጡ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል። በዚህ እርምጃ ኢትዮጵያወያኑ ላይ ክብረ ነክ የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንግልት መፈጸሙ አይቀሬ ነው። ከአራት ዓመት በፊት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ባልወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ይህን ያረጋግጣል። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፣ ዜጎቻቸው በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ውስጥ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየተረባረቡ ነው። መንግስት ይህን የሚያደርገው የዜጎቹን የሰብአዊ መብት የማስከበር ሃላፊነት ስላለበት ነው።  የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ፣ በወገኖቹ ላይ ሊፈጸም የሚችለው የሰበአዊ መብት ጥሰትና እንግልት ራሱ ላይ እንደሚፈጸም የመብት ጥሰት ስለሚሰማው፣ ውርደታቸው ውርደቱ በመሆኑ  ከጥቃትና ከውርደት እንዲድኑ ነው። እናም በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ይህን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ፍላጎትና ስሜት ተረድተው ወደሃገራቸው ለመመለስ መነሳት ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ወደሳኡዲ አረቢያ ሄደው በህገወጥነት ሲኖሩ እንደማይደላቸው በሃገር ቤት የሚኖሩት ወገኖቻቸውና መንግስት ያውቃሉ። በሃገራቸው የስራ እድል ማግኘት ስላልቻሉ ወይም ማግኘት የሚችሉ ስላልመሰላቸው ወይም የተሻለ ገቢ እናገኛለን በሚል ተስፋ የሚጠበቃቸውን አስቸጋሪ ፈተና ተቋቁመው ለመኖር የተጓዙ መሆናቸውን ያውቃሉ። በዚህ ሁኔታ ወደሃገራቸው መመለስ ሊያስፈራቸው እንደሚችልም እንዲሁ። መኖር እንችልም ወይም አይመቸንም ብለው ወደሚያስቧት ኢትዮጵያ ከመመለስ ማንኛውንም ከዚህ የሚያስቀር አማራጭ ለመሞከር እንዲመርጡ የሚያደርግ ስሜት ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉም ይገመታሉ።  በመሆኑም ወደሃገር ቤት ተመለሱ የሚለው ውትወታ በስነልቦናም በቁሳዊ ኑሮም የማይጎዱበትን ሁኔታ ከማደላደል ጋር ካልተጣመረ እንደማይሳካም ይገነዘባሉ። እናም በዚህ ረገድ መንግስት ዝግጅት አድርጓል። ለማሳያነት ያህል ከብዙ ጥቂቶቹን እንመልከት።

ወደሃገራቸው የሚመለሱት ኢትዮጵያውያን ወደመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትና ቀጣይ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት መንግስት ዝግጅቱን አጠናቋል። ሃገር በቀልና ዓለምአቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ወደሃገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን ተቀብለው በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ቃል ገብተዋል።

የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ልማት ኤጀንሲ በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልምድ ያላቸው የሳኡዲ አረቢያ ተመላሾች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ ይገኛል። የተለያየ ክህሎትና ልምድ ይዘው የሚመለሱ ዜጎች በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሥራ የሚያገኙበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ኤጀንሲው አረጋግጧል። ተመላሾቹ በሳኡዲ አረቢያ ባካበቱት ልምድ ሀገራቸው ላይ በአነስተኛ ካፒታል አምራች የሚሆኑበት እድል እንደሚመቻችም ኤጀንሲው አስታውቋል። ክህሎትና ልምድ ኖሯቸው የመነሻ ካፒታል ለሌላቸው ተመላሾች ተጨማሪ ስልጠና፣ የማምረቻ ቦታና የማምረቻ መሳሪዎች በብድር የሚያገኙበት ዕድል እንደሚመቻችም አመልክቷል።

የክልል መንግስታት የስራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲዎችም ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቹ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እናም ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱት ኢትዮጵያውያን ማረፊያቸው መከራ አይደለም። ቢያንስ እንደ አንድ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሰርቶ አዳሪ ኢትዮጵያዊ መኖር የሚያስችላቸው መደላድል ተጎዝጉዞላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሰብአዊ መብታቸውና ክብራቸው በነበረበት ይጠብቃቸዋል። እናም ወደሃገራቸው የሚመለሱት ኢትዮጵያውያን እሾህ ላይ አይደለም የሚያርፉት፤ መኖር የሚያስችል መደላድል ላይ እንጂ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy