Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማንም ገንዘቡን በቀዳዳ ከረጢት ማኖር አይፈቅድም!  

0 332

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማንም ገንዘቡን በቀዳዳ ከረጢት ማኖር አይፈቅድም!  

አባ መላኩ

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከተለያዩ የብድር አገልግሎቶች የምታገኝ አገር ናት።  የኢትዮጵያ መንግስት ብድርን  ማግኘት  ብቻ ሳይሆን ብድርን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በመመለስም ጠንካራ መንግስት ነው። ማንም ገንዘቡን በቀዳዳ ከረጢት ማኖር አይፈልግም፤ ለጽድቅ  ብድርን የሚሰጥ አካል እስካሁን አልተመለከትንም።  ይህ እውነት ነው። ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ አገራት ለኢትዮጵያ የብድር አገልግሎት ማቅረብ የፈቀዱት የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መገንዘብ በመቻላቸው ገንዘባቸውን ከነወለዱ ውሎ አድሮ  ማግኘት እንደሚችሉ ስለሚያውቁ  ነው።  ከሁሉም አካላት ብድርና ዕርዳታ ማግኘት የተቻለው  ዋንኛ ምክንያት መንግስት ብድርና ዕርዳታን በአግባቡ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ብድር መመለስ  ስለቻለም  ጭምር መሆኑ መሰመር የሚገባው ጉዳይ ነው።

ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ብድርም ሆነ ዕርዳታ ማቅረብ የፈቀዱት፣  የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህ ተቋማት የሚያስቀምጧቸውን  የብድር መስፈርቶች ማሟላት የሚችል  መሆኑን በማረጋገገጣቸው ይመስለኛል።  በአሁኑ ጊዜ እንኳን ገንዘብን የሚያክል ነገርን ይቅርና የዓለም መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታን ለማቅረብ በርካታ ሁኔታዎችን በደንብ መርምረው  ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው መሆኑን እየተመለከትን ነው። ሁሉም አበዳሪ አከላት ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ብድር ሊያቀርቡ አይችልም። ብድርንም ሆነ እርዳታን  በተመለከተ  ሁሉም  አበዳሪ አካላት  የየራሳቸው መስፈርቶች አሏቸው። የመጀመሪያው መስፈርት የተበዳሪው የብድር የመክፈል አቅም ነው። ከዚህም ባሻገር ብድሩ ለታለመለት ፕሮጀክት በተያው የጊዜ  ገደብ መዋሉን፣ የፕሮጀክቱ ጥራት፣ በህዝቦች ላይ ያመጣው አዎንታዊ ተጽዕኖ ወዘተ  ናቸው። በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ መንግስት  ውጤታማ  ስራዎችን  ማከናወን ችሏል። በአበዳሪ አካላት አመኔታን ማትረፍ የቻለ መንግስት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ልማታዊ መንግስት ነው።  በመሆኑም ሁሉንም ነገር ገበያ ይምራው ብሎ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። የኢትዮጵያ መንግስት ልማታዊ አካሄድን  ባይከተል  ኖሮ በአገራችን ምን ይከሰት እንደነበር መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም አሁን ላይ ልማታዊ ያልሆኑ  በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የተከሰተውን ነገር እየተመለከትን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት  በተመረጡ   የኢኮኖሚ  ዘርፎች ጣልቃ በመግባቱ ህዝቦች የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። እንደእኔ እንደኔ ለኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ስኬት አንዱ ምክንያት ነው ብዬ የማስበው በተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚያደርገው ቀጥተኛ ተሳትፎ ይመስለኛል። ለዚህ ጥሩ ዓብነት የሚሆነው  በአገራችን መንግስት የሚያስተዳድረው ባንክ በመኖሩ ልማታዊ ባለሃብቶች ብድር በቀላሉ እንዲመቻችላቸው  ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። መሬት በህዝብና መንግስት ባለቤትነት እንዲተዳደር ማድረጉም ትርፍ የሆነ መሬትን በመለየት ለባለሃብቶች ማቅረብ እንዲችል አድርጎታል።    

መንግስት በተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጣልቃ መግባቱ  የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በፈጣን የዕድገት ምህዋር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ትርፋማ በሆኑ የመንግስት ድርጅቶች  በሚገኝ  ገቢ ለአብነት እንደኢትዮ ቴሌኮም  ካሉ ተቋማት በሚሰበሰብ ገቢ  ሌላ የልማት ስራዎችን እንዲያከናውን አስችሎታል።  መንግስት ኢንቨስት  እያደረገባቸው ያሉ ዘርፎች በአብዛኛው የብዙሃኑን ጥቅም ሊያረጋግጡ የሚችሉ፣ አገራዊ ስኬትን ሊያሳድጉ ወይም ሊያጎለብቱ የሚችሉ ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው የማይችል የኢኮኖሚ ዘርፎችን ላይ በመሆኑ በግሉ ሴክተር ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ የለም።

መንግስት ጣልቃ እየገባባቸው ያሉ ዘርፎች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እጅግ እስፈላጊ የሆኑና ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው በማይፈልግ ወይም መንግስት ጣልቃ ቢገባበት የህብረተሰቡን ጥቅም ያሳደጋል  በሚባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች  ላይ ነው።  ባለሃብቱ ቢሰማራባቸው በአጭር ጊዜ ትርፋማ  የማያደርጉ  ወይም  ትርፋማነታቸው አነስተኛ የሆነ  የኢኮኖሚ ዘርፎች  ላይ ባለሃብቱ  መሰማራት አይፈልግም። በእነዚህ ዘርፎች መንግስት ጣልቃ መግባት በመቻሉ ክፍተቶችን መድፈን ችሏል።       

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  አበዳሪዎች  ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይመረምሩ  ገንዘባቸውን  በከንቱ የሚያፈሱበት  ሁኔታ አይኖርም። የኢትዮጵያ መንግስት በብድር አጠቃቀሙም ይሁን አከፋፈል  ረገድ  ውጤታማ  በመሆኑ ዓለም ዓቀፍ  የፋይናንስ ተቋማትም ይሁኑ  የተለያዩ  መንግስታት  ለአገራችን  ብድርና እርዳታ  በማቅረብ ላይ ናቸው።  የኢፌዴሪ መንግስት ከተለያዩ ድርጅቶችና አገሮች ያገኛቸውን ብድሮች በሙሉ የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥኑ   መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ነው። ይህም በመሆኑ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለተከታታይ ዓመታት ፈጣን ዕድገት እንዲመዘገብ አድርጎታል። መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚውል ብድር የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያጎለብት እንደሆነ ይታወቃል። እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስት የብድር ገንዘብን ለፖለቲካ ፍጆታ አያውልም፤ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ አይከፍልም።     

በርካታ  የተለያዩ  ዓለም ዓቀፍ  ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት በብድር አጠቃቀም ረገድ ውጤታማ  እንደሆነ  ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።  በመሆኑም ነው ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራትና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች   ብድሮችን በቀላሉ  ማግኘት  የቻለችው። ብድርን  በተመለከተ  በበርካታ ሰዎች ዘንድ ብዥታ እንዳለ ይሰማኛል። የመንግስት ብድርና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድሮች አንድ ላይ በማየት የኢትዮጵያ መንግስት ብድር  እንደሆኑ  አድርጎ የመውሰድ አዝማሚያ አስተውያለሁ።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ንብረትነታቸው የህዝብ ይሁን እንጂ እንደማንኛውም የትርፍ ድርጅቶች ናቸው። ለአብነት ያክል  ሚድሮክ የግል ኩባንያ ነው። ይህ ኩባንያ ህልውና የሚኖረው  ትርፋማ እስከሆነ  ጊዜ ድርስ ብቻ ነው። በተመሳሳይ ኢትዮቴሌኮምም ሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ህልውናቸው  ትርፋማነታቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት። እነዚህ ድርጅቶች የሚፈጽሟቸው ብድሮች ከራሳቸው የመክፈል አቅም ጋር በተገናዘበ መልኩ እንጂ ከመንግስት ጋር የሚያገናኘው አንድም መገር የለም። አበዳሪው ተቋምም ሆነ አገር ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር ሲያቀርብ  ታሳቢ የሚያደርገው የድርጅቶቹን ወይም የፕሮጀክቶቹን  አዋጭነት እንጂ የመንግስትን የብድር መክፈል አቅም አይደለም። በመሆኑም ነው የመንግስት ብድርና የልማት ድርጅቶች ብድሮች ተለያይተው መታየት አለባቸው ያልኩት።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት  የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቀጣይነት የሚረጋገጠው ትርፋማ እስከሆኑ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ… ካልሆነ…” እንደሚባለው አሁን ላይ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ተወዳዳሪ ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነው። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስራቸውን ለማስፋፋትና  የበለጠ ውጤታማ ለመሆን  የሚፈጽሟቸው ማንኛውም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ብድሮች ከመንግስት ብድር ጋር የሚያገናኛቸው አንድም ነገር አይኖርም።

የኢትዮጵያ መንግስት ብድር በመክፈልም ረገድም ጥሩ ደረጃ ላይ ያለ መንግስት ነው። ባሳለፍነው ሳንምት  ፊች የተባለ ዓለም ዓቀፍ ተቋም የኢትዮጵያ የመበደር አቅም አሁንም በ“ቢ” ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማስታወቁን ሮይተርስ የተባለው የዜና አውታር የተቋሙን ዘገባ ጠቅሶ አውጥቷል። ይሁንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች  ዕዳ እያደገ እንደመጣ  እንዲሁም በአገሪቱ የገቢ እና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን የውጭ ምንዛሬ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ዘገባው  አመልክቷል። ይሁንና የዜና አውታሩ ኢትዮጵያ እጅግ ስኬታማ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንዳለች  አስታውቋል።

አበዳሪ  አካላት  ማለትም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም  ይሁኑ አገራት ለማንኛውም ተበዳሪ አካለት ብድር ሲያበድሩ የየራሳቸው  መስፈርት እንደሚኖራቸው  በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በአገራችን የተረጋጋና ጠንካራ መንግስት ያለ በመሆኑ አስተማማኝና ዘላቂ  ሰላም ሰፍኗል በመሆኑም አበዳሪዎች በኢፌዴሪ መንግስት ላይ  አመኔታ እንዲያጎለብቱ አድርጓቸዋል። መንግስት  የውጭ ቀጥታንም ሆነ የውስጥ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በርካታ አዎንታዊ እርምጃዎች  በመውሰድ ላይ ነው። ለአብነት የመሰረተ ለማት ማስፋፋት (የትራንስፖርት ዝርጋታ፣ የሃይል አቅርቦት፣  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ) በከፍተኛ ሁኔታ በማካሄድ ላይ ነው።  መንግስት እንዲህ በማድረጉም  ባለፉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ  ዕድገት ማስመዝገብ  እንድትችል አድርጓታል።

የኢፌዴሪ መንግስት ገለልተኛ አቋምን በማራመዱና በማንኛው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባቱ  በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማ  እንዲሆን  አድርጎታል። ከምዕራቡም ይሁን ከምስራቁ ዓለም መልካም ግንኙነትን መመስረት የቻለ መንግስት በመሆኑ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ተጨማሪ እሴቶችን በየጊዜው መጨመር ችሏል።  በቅርቡ እንኳን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በቻይና በተገኙበት ወቅት ኢትዮጵያ  የኢዥያ የመሰረተ ልማት የኢንቨስትመንት ባንክ አባል እንድትሆን ከስምምነት ደርሰዋል። ይህ ለአገራችን ሌላ አማራጭ ይዞ የመጣ ትልቅ ዕድል ነው። ኢትዮጵያ የኢዥያ የመሰረተ ልማት የኢንቨስትመንት ባንክ  አባል አገር በመሆኗ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ተጨማሪ ብድሮችን ማግኘት የሚያስችላት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የዓለም ባንክ Global Economic Prospects በሚል ርዕስ ባለፈው ሳምንት በድረገጹ ባስነበበው ሪፖርት ኢትዮጵያ በያዝነው የፈረንጆች  ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚዋ  8.3 በመቶ የሆነ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ  እንደምትችል ትንበያውን አስቀምጧል። ሪፖርቱ አክሎም የኢትዮጵያን ተከትሎ ታንዛኒያ 7.2 በመቶ፣ አይቮሪኮስት 6.8 በመቶ፣ የሴኔጋል 6.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት ተንብዯል። ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ውጤት ታስመዘግባለች ተብሎ እየተጠበቀ ያለው በከባድ ድርቅ በተመታችበት ወቅት መሆኑ ደግሞ የበለጠ አግራሞት የሚጭር ነው። ምክንያቱም  በምስራቅ አፍሪካ  በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች  የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተደረገላቸው ነው። ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች  በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ዕርዳታ  እያቀረቡ ባለመሆናቸው  መንግስት በአብዛኛው  በራሱ አቅም  ዜጎችን በመታደግ ላይ ነው።  

 

በአሁኑ ወቅት መንግስት ድርቅን ለመቋቋም   ከፍተኛ በጀት ለመመደብ በተገደደበት ወቅት ነው። የድርቅ ተጎጂዎችን ለመታደግ  መንግስት   15 እስከ 16 ቢሊዮን ብር መድቧል። መንግስት ይህን ገንዘብ  ለልማት አውሎት  ቢሆን ኖሮ ኢኮኖሚው ላይ ተጨማሪ ዕድገት መፍጠር እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይሆንም።  እንግዲህ እንዲህ  ያለ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ለሚችል አገር ብድርና እርዳታ ቢጎርፍ ብዙም የሚገርም ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምትታወቀው የብድርና ዕርዳታ ገንዘብን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም በመቻሏ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy