Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምሩቃኑ ስራ ፈጣሪዎች እንጂ ጠባቂዎች እንዳይሆኑ…

0 357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምሩቃኑ ስራ ፈጣሪዎች እንጂ ጠባቂዎች እንዳይሆኑ…

                                                     ደስታ ኃይሉ

ሀገራችን ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንዳላት ይገመታል። ከዚህ ህዝብ ውስጥ አንድ ሶስተኛው የሚጠጋው በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል። ይህም  ከሶስት ዜጎች ውስጥ አንዱ ተማሪ  መሆኑን ያመላክታል። መንግስትም ለትምህርት መስክ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ከበጀቱ ከፍተኛውን መድቧል። ለ2010 ዓ.ም የተመደበው በጀትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ሽፋን ከ95 በመቶ በላይ ደርሷል። የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋንም ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ነው። የዩኒቨርሲቲ  ትምህርት ዕድልን በተመለከተ በአገራችን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል።

አዳዲስ ከሚገነቡት 10 ዩኒቨርሲቲዎች ውጭ አሁን ትምህርት በመስጠት ላይ ያሉ 36 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በተለያየ መስክ እየሰለጠኑ ናቸው። ይህም ሀገራችን በቀጣዩቹ ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲኖራትና ለኢንቨስትመንት መስፋፋትም ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥር ያደርጋል። በራስ አቅም የልማት ስራዎችን ለማከናወንም ይረዳል። የልማት ስራዎቻችን ኢትዮጵያዊ እውቀት እንዲያርፍባቸው ያደርጋል።

ባለፉት ዓመታት በሃገራችን በተለያዩ ደረጃዎች ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተን አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናቸው ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በግዙፍነታቸው አልያም በዘመናዊነታቸው እንግዳ የሆኑብን የሚታጡ አይመስለኝም።

እዚህ ላይ ለማንሳት የምፈልገው ጥያቄ ታዲያ “እነዚህ ስራዎች የኢትዮጵያዊያን ዕውቀት አርፎባቸው ለውጤት የበቁ ናቸው” ብለን የምናስብ ስንቶቻችን ነበርን? የሚለውን ነው። እርግጠኛ ነኝ በርካቶቻችን እንደነዚህ ዓይነቶቹን ስራዎች ስንመለከት ቀድመን የምናስበው የውጭ ሙያተኞች እውቀት የፈሰሰባቸው እንደሆኑ ስንገምት ኖረናል። እርግጥ ዓይነቱ አመለካከት መኖሩ ተገቢ አልነበረም የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱም ለረጅም ጊዜያት በልማቱ መስክ ላይ ውጤት ማምጣት የሚችል በእውቀትና በክህሎት የዳበረ በቂ የሰው ሃይል ሳይገነባ በመቀየቱ ነው።

በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ  የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል።

በትምህርት መስክ በመጀመሪያው የልማት ዕቅድ የተገኙትን ውጤቶች ከሁለተኛው የልማት ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር ስራው እየተሳለጠ ነው። በሁለተኛው “ዕትዕ” የትምህርቱ ዘርፍ የህፃናትንና የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ የሚገድቡ ችግሮች ለመቅረፍ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ከሀገራችን የትምህርት ግቦች ጋር የሚጣጣሙ የድህረ 2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች የዕቅዱ አካል ተደርገው ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው።

ትምህርትን በተመለከተ ቁልፉ ጉዳይ ጥራት ቢሆንም፤ ቀጥሎ ትኩረት የሚያሻቸው ከሽፋን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ይህንኑ ጉዳይ ለማሻሻል እየተሰራ ነው። የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን የማስፋፋት ጉዳይ ነው። በያዝነው የዕቅድ ዘመን ይህን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ለቅድመ መደበኛና የጐልማሶች ትምህርት ትኩረት በመስጠት ስራው እየተሳለጠ ነው። እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የመምህራንና የትምህርት ቤቶችን ጥራትና ቁጥር ለማሳደግ የሚወሰዱ ርምጃዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

እርግጥ እቅዱ ከተጀመረ ገና አንድ ዓመት ከመንፈቅን እልፍ ያለ ቢሆንም መንግስት በየደረጃው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱና ለማህበራዊ ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ ዜጋ ማፍራት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ መጠን፤ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ተገቢውን ተግባር እየተወጣ ነው።

ለዚህም የግል ባለሃብቶች በትምህርት ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ድጋፍ መስጠትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ለመሆኑ ተገቢው ክትትልን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በመንግስት የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተመሳሳሳይ ተግባርን መከወን ይጠይቃል።

ያም ሆኖ ግን በመንግስት ጥረት ብቻ የትምህርት ጥራት ሊጠበቅ አይችልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል። በእስካሁኑ ሂደት ህብረተሰቡ የመማር ማስተማሩ አካል እንዲሆን በማድረግ ከጥራት አኳያ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም በቀሪዎቹ የዕቅዱ ዓመታት ተጠናክሮ ከቀጠለ በትምህርት ጥራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብዬ አምናለሁ።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት በርካታ ምሁራኖቿን ታስመርቃለች። ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁት ምሁራን በቀሰሙት እውቀት ሀገራቸው ከድህነት ጋር የተያያዘችውን ዘመቻ መደገፍ አለባቸው። ይገባቸዋልም። ስራ ጠባቂ መሆን የለባቸውም። ስራ ፈጣሪ በመሆንም ለሀገራቸው የዘመናት ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ይገባቸዋል።

እዚህ ሀገር ውስጥ አየተፈጠረው አመቺ ሁኔታ ስራን ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ተመራቂዎቹ ክህሎትን ወደ ተግባር መቀየር አለባቸው። ይህም ኢትዮጵያ ህዳሴዋን እውን ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy