Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ምክር ቤቱ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ተወያየ

0 719

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየ።

ምክር ቤቱ የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክሮበት ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለምክር ቤቱ ማስተላለፉን ተከትሎ በዛሬው እለት ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት ረቂቅ አዋጁ መንግስት የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄዎች ለማሟላትና ለመመለስ ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የምክር ቤቱ የዚህ አመት የስራ ዘመን ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ረቂቁ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑንም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም አንድ ሳምንት በቀረው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ማብቂያ ላይ የቀረበው ረቂቅ፥ ከህዝብ ጋር ለመወያየት እንዴት ያስችላል ሲሉም ጠይቀዋል።

ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፥ በረቂቁ ላይ በፍጥነትና አጭር ጊዜ ውስጥ የመወሰን አካሄድ አይኖርም ብለዋል።

አንድ ሳምንት በቀረው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ረቂቅ አዋጁ ይፀድቃል ተብሎ እንደማይጠበቅም ገልጸዋል።

በ25 አንቀጾች እና በአራት ክፍሎች በቀረበው ረቂቅ ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ ዝርዝር ጉዳዮችና ጥያቄዎችም ጉዳዩ ለተመራለት የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተደራቢነት ለሚመለከተው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር ይታያልም ነው ያሉት።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚከተሉት ህገ መንግስታዊ ልዩ ጥቅሞች ይኖሩታል።

ከአገልግሎት አቅርቦት ልዩ ጥቅም አኳያ

በአዋጁ መሰረት ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር ለሚፈልጉ የክልሉ ተወላጆች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲያደራጅ ይደረጋል።

አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ በመሆኗ በከተማዋ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የክልሉ ተወላጆችን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል፤ ከዚህ ባለፈም ከአማርኛ በተጓዳኝ አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የስራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል።

የኦሮሞ ህዝብን ማንነት የሚያንጸባርቁ አሻራዎች በከተማዋ በቋሚነት እንዲኖሩ በከተማዋ፥ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደ አስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ይደረጋል።

የከተማው አስተዳደርም የኦሮም ህዝብን ባህልና ታሪክ የሚያንፀባርቁ የባህልና ታሪክ ማዕከላት፣ ቲያትር፣ ኪነ ጥበባትና የመዝናኛ ማዕከላት የሚገነቡበትና የሚተዋወቁበትን ሁኔታ እንዲያመቻች በአዋጁ ተደንግጓል።

የከተማዋ መጠሪያዎች “ፊንፊኔ” እና “አዲስ አበባ” በህግ ፊት እኩል እንደሚያገለግሉም በአዋጁ ሰፍሯል።

ከመሬት አቅርቦት፣ ከውሃ አገልግሎት አቅርቦት፣ ከፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች የማስወገድ አገልግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የስራ እድል አቅርቦት፣ በመንግስት ወጪ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አቅርቦት እንዲሁም ከገበያ ማዕከላት አቅርቦትና አርሶ አደሩ ለልማት ተነሺ ሲሆን፥ በቂ ካሳ የማግኘትና በዘላቂነት የማቋቋም አገልግሎትን ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል።

የመሬት አቅርቦትን በተመለከተም ተቋማት ለክልሉ የተለያዩ መንግስታዊ ስራዎች እና ህዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች የሚሰሩበትን መሬት ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙ ይደረጋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች፥ ምርቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን የገበያ ማዕከላት አቋቁሞ ለአርሶ አደሮች እና ማህበሮቻቸው እንዲያቀርብ ይደረጋል።

በልማት ተነሺ ለሆኑና በከተማዋ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከመኖሪያቸው ሲፈናቀሉ በቂ ካሳና በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ በዚህ ዙሪያ የተሰሩ የቀደሙ

ስራዎች ተፈትሸው ጉድለቶች እንዲስተካከሉና ስራዎችን የሚያስተባብር፣ የሚመራና የሚያስፈጽም ጽህፈት ቤትም ይደራጃል።

የኦሮሚያ ክልል በከተማው ስለሚኖረው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ልዩ ጥቅም አኳያ

አዋጁ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ ከተሞችና ቀበሌዎች ደህንነቱ ሳይጠበቅና ቁጥጥር ሳይደረግበት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በህግ አግባብ ከአስተዳደሩ ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸውም አስቀምጧል።

ከዚህ ባለፈም የአዲስ አባበ ከተማ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያና ማስወገጃ ቦታዎች እንዲሁም መልሶ መጠቀሚያ ስፍራዎች፥ አስተዳደሩና ክልሉ በጋራ ባጠኗቸው ቦታዎችና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን ባሟሉ ሁኔታዎች እንዲተዳደሩ እንደሚደረግም በአዋጁ ተጠቅሷል።

ተቋማትን ከማደራጀት አኳያ

በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ የክልሉን አርሶ አደሮች በተመለከተ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት የሆነና ከከተማ አስተዳደሩና ከኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት የሚቋቋምም ይሆናል።

ምክር ቤቱ ከኦሮሚያ ልዩ ጥቅም አንጻር የሚነሱና ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ፥ በአዋጁ የተዘረዘሩ ልዩ ጥቅሞች ተግባራዊ እንዲሆኑ በመከታተልና በመገምገም ድጋፍ ያደርጋል።

አባላቱም ከአስተዳደሩ እና ከክልሉ ምክር ቤት እኩል የሚወከሉ ሆነው፥ አጠቃላይ የምክር ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ዝርዝር ጉዳዮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እንደሚወሰን በአዋጁ ተጠቅሷል።

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅምን ለማስጠበቅ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በማጸደቅ ሂደት ላይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።

በዳዊት መስፍን

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy