Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ራዕዩ ተምኔታዊ አይደለም

0 267

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ራዕዩ ተምኔታዊ አይደለም

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ከድህነት ጋር ተቆራኝቶ ኖሯል። ከድህነት ጋር ከመኖርም ባለፈ፣ የድህነት ደረጃው እያሽቆለቆለ ሄዷል። ታዲያ ከዚህ ጋር ኑሮውም እየዘቀጠ ዘልቋል፤ ለዘመናት። ድህነት እጦት ነው፤ መሰረታዊ ፍላጎቶችን በወጉ ማሟላት የማይቻበት፣ ነገ የማይታሰብበት፣ ዛሬና አሁን ብቻ ህይወትን ለማትረፍ የሚፍጨረጨሩበት የኑሮ ሁኔታ ነው። ድህነት ውስጥ ተስፋ የለም። እናም ድህነት አስከፊ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ጋር ተቆራኝቶ የኖረው ድህነት ስለሞቀው አልነበረም። የድህነትን ቀንበር ሰብሮ ማምለጥ አቅጦት እንጂ። ይህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ሰነፍ መሆኑ አይደለም።  የኢትዮጵያ አርሶ አደር ሰርቶ የማይደክመው፣ የማያንቀላፋ፣ የማይታክት ባተሌ ነው። በስንፍና አይታማም። ችግሩ የነበረው ሃገሪቱን የሚመሩት የመንግስት ስርአቶች የሚከተሉት የኢኮኖሚና የልማት ፖሊሲዎች ናቸው። የባለፉት ስርአቶች የኢኮኖሚ መርኸና ፖሊሲዎች ሰርቶ ያፈራውን የሚነጥቁ፣ እንዳይሰራ የሚገፉ ነበሩ።

ከአራት አስርት ዓመታት በፊት የነበረው ፊውዳላዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ከሃገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 90 በመቶ ገደማ ይሆን የነረውን አርሶ አደር ከዋናው የምርት ሃይል (factor of prodaction) – መሬት ነጥሎ ገባር ጪሰኛ አድርጎት ኖሯል። ይህ ገባር ጭሰኛ በሙሉ ሰአት የግብርና ስራው ሰርቶ የሚያፈራው ሃብት ባለቤት አልነበረም። የምርቱ ባለቤት ባለርስትና ባለጉልቶች ነበሩ። አርሶ አደሩ ከነቤተሰቦቹ የሚገብረውን እንዲያመርት ህይወቱን ማቆየት የሚያስችለው ምርት ብቻ ነበር የሚተርፈው። ይህ የእለት ጉርሱ ብቻ የሚተርፍለት፣ ተፈጥሮ ስትከፋ ደግሞ የእለት ጉርሱንም የሚያጣ አርሶ አደር ምርታማነቱን የማሳደግ ፍላጎት አልነበረውም። የምርታማነት ማደግ ለባለርስት ፊውዳል ጌቶቹ እንጂ ለእርሱ ምንም አያስገኝለትም፤ “ሺህ ቢታለብ ያው በገሌ” እንዲሉ።

ፊውዳል ባለርስቶች የተትረፈረፈ ምርት ቢያጋብሱም፣ ይህን ያስገኘላቸውን ገባርና መሬታቸውን ይዘው ከመኖር ያለፈ ሃብታቸውን እንደረቢ ሃብት (capital) በመጠቀም በሌላ የስራ መስክ ላይ የመሰማራት ፍላጎት አልነበራቸውም። እንኳን ከግብርና የተለየ ስራ ላይ ሊሰማሩ፣ ራሱን ግብርናውንም የማዘመን ፍላጎታቸው ደካማ ነበር። እርግጥ ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ልጆቻቸው ገባር ጭሰኛውን አፈናቅለው ወደ ሰፋፊ የንግድ እርሻ (commercial farm) ለመሸጋጋር ሙከራ አድርገዋል።

በዚህ ምክንያት የዘውዳዊ ፊውዳላዊው ስርአት ኢኮኖሚ የማይላወስ ነበር። ህዝቡም በዚህ በማይላወስ ኢኮኖሚ ምክንያት ከድህነት ጋር ተቆራኝቶ ለመኖር ተገዷል። ይህ ፊውዳላዊ ስርአት በተወሰ ደረጃ የካፒታሊዝም ባህሪ ዘልቆት ነበር። በተለይ ከአውሮፓ ተሰደው በቋሚነት ኑሯቸውን በኢትዮጵያ አድርገው የነበሩ አርመኖች ከንግድ ባሻገር ፋብሪካዎችን ያቋቋሙበት ሁኔታ ነበር። በአዲስ አበባ የኤሊያስ ፓፓሲኖስ የአልኮል መጠጥ ፋብሪካ፣ የዳርማር ጫማ ፋብሪካ፣ የአስኮ ጫማ ፋብሪካ . . . በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ። እንዲሁ ጥቂት የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በጨርቃጨርቅ፣ በቢራና ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች ላይ የተሰማሩበትም ሁኔታ ነበር። በተለይ በወንጂና መተሃራ በሆላንድ ባለሃብቶች የተቋቋሙት የስኳር ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች በአክሲዮን ሽያጭ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንንም አሳተፈው ስለነበረ ጥሩ መነቃቃት ፈጥረዋል ማለት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ አረቦች፣ ህንዶች፣ በንግድ ስራ ላይ ተሰማረተው ኢትዮጵያውያኑንም ያነቃቃ ተሳተፎ ነበራቸው።

ያም ሆነ ይህ በፊውዳላዊው ስርአት የኢንደስትሪው ዘርፍ ፈቅ ሊል ሳይችል ቀርቷል። የዚህ ምክንያት በርካታ ቢሆንም 90 በመቶ የሚሆነውን የሃገሪቱን ህዝብ የሚወክለው አርሶ አደሩ እጅግ ደሃ በመሆኑ የገበያ አቅም ሊሆን አለመቻሉ፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።

ያም ሆነ ይህ ወታደራዊው ደርግ ወደስልጣን ሲመጣ ብቅ ማለት ጀምሮ የነበረው የኢንደስትሪ እደገትና የእድገቱ ገፊ የነበረው የውጭ ኢንቨስትመንት ጨለመ። በመሆኑም የኢንደስትሪው ዘርፍ ባለበት ደረጃም መቆየት ሳይችል ቀርቷል። ወታደራዊው ደርግ በንግድ፣ በቤት ልማትና በአገልግሎት ዘርፎች እጅግ በተወሰነ ደረጃ በጎጆ ኢንደስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩና እያደጉ የነበሩ ሃገር ባለሃብቶችን ወርሶ ደብዛቸውን አጠፋው። የውጭ ሃገር ባለሃብቶችንም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ካሳ ከፈሎ ፋብሪካቸውን ወርሶ ከሃገር አባረራቸው። ሌሎች የውጭ ባለሃብቶችም ወደሃገር ውስጥ እናይገቡ መንገዱን ዘጋው። በወታደራዊው ደርግ ስርአት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ዜሮ ነበር።

በዚሀ ሁኔታ መንግስት ብቸኛው ነጋዴ ( ጅምላ ሻጭ፣ ቸርቻሪ፣ ላኪ አስመጪ)፣ አምራች፣ አገልግሎት ሰጪ ሆኖ ብቅ አለ። መንግስት ህዝቡን ከድህነት ማጥ አውጥቶ ኑሮውን መቀየር በሚያስችል ልክ ኢንቨስት የማድረግ አቅም አልነበረውም። ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡ ላይ ጭኖ በነበረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ምክንያት በየአቅጣጫው የተከፈተበትን ህዝባዊ የትጥቅ ትግል ለማክሸፍ ያወጀውን ጦርነት ወጪ ለመሸፈን መገደዱ የኢንቨስትመንት አቅሙን የባሰ ደካማ አድርጎት ነበር። በዚህ ምክንያት መንግስት ማህበራዊ አገልግሎትንም ማስፋፋት አልቻለም፤ ኢኮኖሚያዊ ልማትም ላይ የሚፈለገውን ያህል ሃብት ማፍሰስ አልቻለም። በወታደራዊው ደርግ አስራ ሰባት የስልጣን ዘመናት ተገነቡ ተብለው የሚጠቀሱት ፋብሪካዎች ሙገር የሲሚንቶ ፋብበሪካ፣ የናዝሬት ትራክተር ፋብሪካ፣ ሃረር ቢራ ፋብሪካ፣ በዴሌ ቢራ ፋብሪካ  ናቸው።

ገባር ጪሰኛ የነበረው አርሶ አደርም ኑሮ አልተሻሻለም። ወታደራዊው ደርግ አርሶ አደሩ የመሬት ባለቤት መሆን እንዲችል ቢያደርግም፣ በመሬቱ ላይ ሰርቶ የሚያገኘው ምርት ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው አድርጎ ነበር። አርሶ አደሩ ምርቱን እጅግ በአነስተኛ ዋጋ ለመንግስት የመሸጥ ግዴታ ነበረበት። ከዚህ በተጨማሪ ምርታማነቱን ለማሳደግ የፋይናንስ፣ የሞያ፣ የግብአት ወዘተ ድጋፍ የሚያገኝበት ስርአት አልተዘረጋም ነበር።

በእነዚህ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮት ከኖረው ድህነት ጋር ለመዝለቅ ተገዷል። የድህነት መጠኑም ከእለት ወደእለት እየባሰ ኑሮው ከድጥ ወደማጥ ሆኖበት ነበር።

ከደርግ ውድቀት በኋላ ይህን የህዝቡን ድህነት የመለወጥ ጉዳይ ቀዳሚ የመንግስት አጀንዳ ሆነ። ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ መጀመሪያ የተወሰደው ርምጃ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ማረጋገጥ ነበር። በሃገሪቱ ነጻ ገበያ መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስርአት ስራ ላይ እንዲውል ተደረገ። አርሶ አደሩ በምርቱ ላይ ያለው የባለቤትነት መብት ከመረጋገጡ በተጨማሪ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገውለታል። የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሻሻል የተከናወነው ተግባር በአመዛኙ ውጤታማ ሆኗል። ይህም የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ አስችሏል። በሺህ የሚቆጠሩ ሚሊየነር አርሶ አደሮችም ተፈጥረዋል።

ይህ ሁኔታ አርሶ አደሩን ከነበረበት ድህነት ማጥ እንዲወጣ ማድረግ ከመጀመሩ ባሻገር አርሶ አደሩን ትልቅ የሃገር ውስጥ የገበያ አቅም በማደረግ የኢንደስትሪና የአገልግሎት ዘርፉን አነሳስቷል። ከፍተኛ የገበያ አቅም የሆነው አርሶ አደር የኢንደስትሪና የአገልግሎት ዘርፉን ትርፋማነት በማሳደግ የሃገር ውስጥ የካፒታል (የኢንቨስትመንት) አቅም ፈጥሯል። ይህ በርካታ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት የተከተለው ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ለባለሃብቶች ያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ማበረታቻና በሃገሪቱ ያለው አስተማማኝ ሰላም ሃገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትምንት እንድትስብ አድርጓል።

እነዚህ ሁኔታዎች ተዳምረው ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በአማካይ ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቧል። አሁን በተጨባጭ ያለው የሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ያመለክታል። ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት የ2009 በጀት ዓመት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ 10 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ትንበያ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2017 የ8 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ አመልክቷል። ባንኩ የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዓለም ላይ ከሚመዘገቡ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገቶች አንዱ መሆኑንም ጠቁሟል። ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት አንጻር፣ የኢትዮጵያ እድገት ፈጣኑ እንደሚሆንም በትንበያው ሪፖርት ላይ ገልጿል። ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ባለው ንጽጽር ደግሞ ኢትዮጵያ ቀዳሚ እንደምትሆን የዓለም ባንክ ትንበያ ያመለክታል። “ታንዛኒያ በ7 ነጥብ 2፣ አይቮሪ ኮስት በ6 ነጥብ 8 እንዲሁም ሴኔጋል በ6 ነጥብ 7 ይከተላሉ” ይላል የባልኩ ትንበያ።

ኢትዮጵያ እስካሁን ያለውን እድገት በማስቀጠል መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ኢንደስትሪው በኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነቱን ድርሻ እንዲይዝና ከስምንት ዓመት በኋላ ማለትም በ2017 ዓ/ም መካከለኛ ገቢ ደረጃ የመደረስ እቅድ አስቀምጣለች። መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ መድረስ ለኢንደስትሪው ዘርፍ የሚውል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይሻል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ካስቀመጠቻቻው ማበረታቻዎች በተጨማሪ ለኢነቨስትመንት ምቹ የሆኑ የውጭም ሆኑ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን በአጭር ጊዜ ወደምርት ስራ መግባት የሚያስችላቸው የኢንደስትሪ ፓርኮች በመገንባት ላይ ትገኛለች። የቦሌ ለሚና የሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ የውጭ ኢንቨስተሮችን ተቀብለው በመስራት ላይ ይገኛሉ። ሌሎች በቅርቡ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደስራ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ የኢንደስትሪ ፓርኮችም አሉ።

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የተደረገው የሃዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ከያዛቸው 37 ፋብሪካዎች ውስጥ 13ቱ ስራ ጀመረዋል። ስራ ከጀመሩት 13 ፋብሪካዎች ውስጥ ስድስቱ ደግሞ ምርታቸውን ለውጪ ሃገር ገበያ ማቅረብ ጀምረዋል። ልብ በሉ፤ በአንድ ዓመት ቆይታ በአንድ የኢንደስትሪ ፓርክ ብቻ 13 የውጭ ንግድ ላይ ያተኩሩ 13 ፋብሪካዎች ናቸው ወደስራ የገቡት። ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህ በበርካታ ዓመታትም የማይገኝ ነበር።

ኢትዮጵያ በ2007 ዓ/ም የነበራት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ነበር። ባለፈው ዓመት ይህ ወደ 2 ቢሊየን አድጓል። የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ እ ኤ አ በ2016 የኢትዮጵያ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር እንደነበረ አስታውቋል። ይህም ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት የ45 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ያሳየ መሆኑንም አስታውቋል።

እነዚህ የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በኋላ መካከለኛ ገቢ ያላት ሃገር መሆኗ አይቀሬ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህ የህዝቡም የኑሮ ሁኔታ በዛው ልክ እነደሚቀየር ያመለክተል። ለህዝብ የቆመና የህዝብ ውክልና ያለው መንግስት ዋነኛ ግብ ደግሞ ይህ ነው፤ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል የመኖር ዋስትናውን ማረጋገጥ። ሌሎች የመንግስት ተግባራት በሙሉ ይህን የሚያግዙ ናቸው እንጂ በራሳቸው መድረሻ አይደሉም።  እናም የኢፌዴሪ መንግስት ያስቀመጠው ከስምንት ዓመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ መድረስ ተምኔታዊ ሳይሆን ተጨባጭ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy