ስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ
ዳዊት ምትኩ
የሳዑዲ መንግስት ያስቀመጠው የምህረት ጊዜው ከማለቁ በፊት ዜጎች ወደ ሀገራቸው ያለ አንዳች እንግልትና ባዶ እጃቸውን እንዳይመለሱ ለማድረግ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ነው። በዚህም ዜጎች በቀላሉ የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳዑዲ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል። በሪያድና በጂዳ የሚገኙ ሚሲዮኖች የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ ሁኔታ የተቀላጠፈ እንዲሆንና በጉዳዩ ዙሪያ ሊያጋጥሙ በሚችሉ መሰናክሎች ላይ ውይይት በመደረጉም ሁኔታው ለተመላሽ ዜጎች ተመቻችቷል።
ታዲያ እዚህ ላይ በሳዑዲ አረቢያ መንግስት ‘ህገ ወጥ ናቸው’ በማለት የፈረጃቸውን አካላት ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ ማንሳት ይገባል። በሪያድ መንግስት ህገ ወጥ የሚባሉት በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞች፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞች፣ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሀገራት ነዋሪዎች፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው ስደተኞች እንዲሁም ለሃጂና ዑምራ ሄደው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ነዋሪዎች ብሎም ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ አማኞች ናቸው።
እናም የተሰጠው የ90 ቀናት የምህረት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት በዚህ ብያኔ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። የምህረት ጊዜውን አክብረው የሚወጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ የኢሚግሬሽን ፅህፈት ቤቶች የመውጫ ቪዛ ያገኛሉ።
አሊያ ግን ሃብትና ንብረታቸው ተቀምቶና የተጣለባቸውን ቅጣት በመክፈል ጭምር ከሳዑዲ እንዲወጡ ይደረጋል። በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎች መንግስት ያመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም ወደ ሀገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። በምንም ዓይነት መልኩ የህገ ወጥ ደላሎችን መደለያ ቃላት መስማት የለባቸውም። እርግጥ በዚያች ሀገር በህገ ወጥነት የሚኖሩት የሀገራችን ዜጎች ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ የዳረጓቸው ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው።
እነዚህ ደላሎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ እንደላኳቸው ስለሚያውቁ፤ ዜጎችን ‘ዝም ብላችሁ ኑሩ፣ የሚመጣባችሁ ችግር የለም’ በማለት ሊያዘናጓቸው ይችላሉ። ዕውነታው ግን እንዲያ አይደለም። የተሳሳተ ነው። ሃቁ መንግስት የሚለውና የምህረት ጊዜውን መጠቀም ብቻ ነው።
ይህን ማድረግ ካልተቻለ የሳዑዲ መንግስት የጉዞ ሰነድን ከመቀማት አንስቶ “ቅጣት ናቸው” ያላቸውን ማናቸውንም ጉዳዩች ይፈፅማል። ይህን በጥሞና ማገናዘብ ይገባል። በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡ የሀገራችን ዜጎች ምክንያታቸውን ወደ ጎን በማድረግ የኢፌዴሪ መንግስትና የሪያድ መንግስት እያከናወኑ ያሉትን ትክክለኛ መንገድ በመከተል ወደ ሀገራቸው መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል።
ሁላችንም እንደምናውቀው በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው እንደሆነ ይገልፃሉ። በርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት የሚታወቅ ቢሆንም፤ የችግሩ መንስኤ ግን ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም። ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻለና ሰርተው መበልፀግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ ወጥ አዘዋዋሪ ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን በዓይናችን የምናየውና በጆሯአችን የምንሰማው ሃቅ ስለሆነ ነው።
ለነገሩ ማንም ሰው በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ አባባሌ መላው ህዝባችንና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልፅግና እና ኑሮ መሻሻል መሆኑን በአስረጅነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።
ታዲያ ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያሳዝን ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና ራስን ጠቅሞ ቤተሰብንና ሀገርን መጥቀም እየተቻለ ህገ ወጥ አካሄድን መርጦ ለእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ መጋለጡ ተገቢ አይደለም።
በመሆኑም ዜጎች የሳዑዲ መንግስት ያቀረበውን የምህረት ጊዜ ቢጠቀሙ ተገቢውን ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ። አንድም ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት አሻራቸው በሪያድ አስተዳደር ስለማይወሰድ ተመልሰው ሊሄዱ ይችላሉ። ሁለትም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ሊያድጉ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ።
እርግጥም እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ ይቻላል። የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር።
በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊው ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸው የትናንት ትውስታችን መሆኑ የሚካድ አይመስለኝም።
ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት፣ ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው።
እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በአሁኑ ወቅትም በተለይ ወጣቶች መንግስት ካዘጋጀው የ10 ቢሊዩን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። እነዚህ ሁኔታዎችም የሀገራችን መንግስት ምን ያህል የዜጎቹን ሀይወት በመለወጥ ተግባር ላይ መሰማራቱን የሚያሳዩ ናቸው።
ስለሆነም በሳዑዲ መንግስት በህገ ወጥነት ተፈርጀው የሚኖሩ ዜጎች የዘጠና ቀናቱን የምህረት ጊዜ ገደብን ቢጠቀሙ፤ ንብረታቸውን ከመወረስ በማዳን ዳግም ወደ እዚያች ሀገር በህጋዊ መንገድ ተመልሰው የመስራት እድል ይኖራቸዋል።
ይህ በመሆኑም የጊዜ ገደቡ ይህ ፅሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሰባት ቀናት ብቻ የቀሩት ቢሆንም፤ በእነዚህ ቀናቶች ቢሆንም መንግስት ባመቻቸው ሁኔታ ስደተኞቹ መጠቀም ይኖርባቸዋል። እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መበልፀግ እንደሚቻል በመገንዘብ ህይወታቸውን በሀገራቸው ውስጥ ብሩህ ማድረግ እንደሚገባቸው ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። እናም አሁንም ቢሆን በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ራሳቸውን በማዳን ወደ ሀገራቸው መምጣትን እንደ መጨረሻ አማራጭ መውሰድ ይኖርባቸዋል።