Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደት ለአገርና ለወገን ውርደት ነው!

0 280

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደት ለአገርና ለወገን ውርደት ነው! 

ስሜነህ

የሳዑዲ መንግሥት በአገሩ የሚኖሩ የየትኛውም አገር ህገ ወጥ ስደተኞች በዘጠና ቀናት ውስጥ አገሩን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ የቀሩት ከሰላሳ ቀናት ያነሰ ነው ። ሰኔ 20 /2009 ዓ/ም ያበቃል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህገወጥ ስደተኛ ካላት ሃገራችን እስካሁን ለመመለስ የቻሉት ከ10 ሺህ የማይበልጡ ሲሆን ለመመለስ የተመዘገቡት ደግሞ ከ45 ሺህ የማይበልጡ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። እነዚህ ስደተኞች በ90 ቀናት አመላልሶ ለመጨረስ ቢያንስ በቀን ከ5ሺህ ያላነሱ ዜጎችን ማመላለስ የሚጠበቅ ቢሆንም አሁን በቀን እየመጡ የሚገኙት ዜጎች ከ200 የማይበልጡ መሆናቸው ያሳስባል።

የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ የሳዑዲ መንግሥት ሊያስከትልባቸው የሚችለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ የከፋ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ባለበት በዚህ ሰአት፤በጊዜ ገደቡ ለማይጠቀሙ ህገወጥ ስደተኞች 98 እስር ቤት አይደለም “ማጎሪያዎች” ስለማዘጋጀቷ ሳውዲ እየተናገረች በምትገኝበት በዚህ ሰዓት ዜጎቻችን ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት ከላይ በተመለከተው መልኩ መሆኑ በእርግጥም አሳሳቢ እና የውርደታችንን ደረጃ ከወዲሁ የሚያመላክት ነው። ዜጎቻችን ወደ አገራቸው ቢመለሱ አገራቸው  ሰርቶ ለመለወጥ ምቹ መሆኗ በሚታወቅበት አግባብ ውስጥ እንዲህ አይነት ቅሌት ውስጥ መግባት አሳፋሪነቱ አያከራክርም።

የሳውዲ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የሁሉም አገራት ዜጎች ካለፈው መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በ90 ቀናት እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። ጉዳዩ እንደታወቀ የኢፌዴሪ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማካሄድ ላይ መሆኑም ይታወቃል፡፡ለተመላሾች በሚወጡበት አገር ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ወደአገር እስኪመለሱና ብሎም ወደየቀያቸው ሲመለሱ አቅም በፈቀደው መልኩ በዘለቄታ እስከሚቋቋሙበት ድረስ ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን ዝርዝር ጉዳዮችን በማጥናትና ሥርዓት በማበጀት ሌት ተቀን እየሰራም ይገኛል፡፡ 

በሳውዲ ዓረቢያም አንድ ግብረ ሃይል በማቋቋም በዚያ የሚገኙ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ እና መረጃ እየሰጠ መሆኑም ይታወቃል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተለያዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ያለቀረጥ እንዲያስገቡም መንግሥት ፈቅዷል፡፡

የመንግስት ፍላጎት ከሳዑዲ ተመላሽ  ዜጎቻችን አንዳችም ዓይነት ጉዳት እና እንግልት ሳይደርስባቸው በተሰጣቸው የእፎይታ ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማስቻል መሆኑ በተደጋጋሚ በብሄራዊ ግብረ ሃይሉ በኩል በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ያም ሆኖ ግን በእስካሁኑ ሂደት የተመለሱትም ሆነ ለመመለስ ዝግጁ የሆኑት ዜጎቻችን ከላይ የተመለከተው መሆኑ ያሳስባል። ምክንያቱም ዜጎቻችን የሳውዲ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ  ወደ አገራቸው ካልተመለሱ  አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይጣሳሉ፣ ንብረቶቻቸው ይወረሳሉ፣ ለእንግልት ይዳረጋሉ። በመሆኑም  በሳውዲ የሚገኙት ዜጎቻችን ይህንኑ ከወዲሁ ተገንዝበው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በቀሪዎቹ ቀናት  ፈጥነው ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ የሚኖርባቸው መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡

የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ  ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ  በማድረግ በኩል በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን መንግሥት፣ ሚዲያዎች፣ ማህበራት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው ህዝባችን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ዜጎቻችንን ቶሎ እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።በአገር ሰርቶ መለወጥ ግን  ኩራት መሆኑንም መገንዘብና ማስገንዘብ ተገቢ ነው።

የዜጎቻችን ፍላጎት በዚህ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ መንግስት በዋናነት ደላሎችን ተጠያቂ ያደርጋል።ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በአንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ባደረኩት የቀጥታ ስልክ ውይይት ለዚህ ጉዳይ በምክንያትነት የተጠቀሱት በርከት ያሉ እና መሰረታዊ የሚባሉ ናቸው።ከነዚህ መካከል ሊወገድ ይቅርና ሊቀረፍም እንኳ ያልቻለው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ዋነኛው ነው።መንግስት ለተመላሾች የሚገባውን ቃል በተግባር አይፈጽምም የሚለውም ሌላኛው በምክንያትነት ከአድማጮች የተጠቀሰ ነው።በነገራችን ላይ አንዳንዶቹ ደግሞ ስለምን በጉቦ ይመለሳሉ ሲሉም የጠየቁ ሲሆን፤ ከዚያ እስኪመጡ ያለው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ ከቀረጥ ነጻ የሚለው ማበረታቻ ግን ዜጎችን ማበላለጥ ህገወጥነትን ማበረታታትና ይልቁንም ህገ መንግስታዊ ስርአቱን መጻረር ነው ሲሉ ሞግተዋል።ሁሉም በራሱ ትክክል ነው።አለመመለስ ግን አማራጭ አይደለም።እነዚህ ህገወጦች መረጃው የላቸውም የሚሉትን ያህል ከደላላም በላይ አሰሪዎቻቸው አይዞሽ ፤አይዞህ ቀኑ ሲደርስ እልክሃለው እልክሻለሁ እያሉም የሚያዘናጓቸው እንደሆነም የ 2006 ተመላሽ የነበሩ ዜጎች ተሞክሯቸውን ገልጸዋል።ይህ ደግሞ በጣም ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።አዋጁ ደብቀው የተገኙ የሳውዲ ዜጎችንም የተመለከተ ቢሆንም ሃገራቸው ነውና ለነሱ የማይሻሻል ነገር ይኖራል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።ምክንያቱም ህገወጡን የማስወጣት ተልእኮው ዋነኛ አላማም ለዜጎቿ የስራ እድሎችን ለማስፋት ስለሆነ።ዋነኛው አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ይህ አይደለም።እነዚህ አሰሪዎች ተጠያቂ ላለመሆን ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ ቀናትና ሰዓታት ሲቀሩትም አስወጥተው ሜዳ ሊወረውሯቸው ይችላሉም እና ነው።ይህም ኢሰብአዊ ተግባራቸው  በተደጋጋሚ ታይቷል።

በመንግስት በኩል ከላይ የተመለከቱት  እንደተጠበቁ ሆነው ዜጎቻችን አለመመለሳቸው አማራጭ እንደማይሆን በመገንዘብ እና የቀኑ መቃረብ እውን እየሆነ በመጣው ልክ እየተሰራ ለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል።ይህ ደግሞ የሳውዲ አቋም እንደማይለወጥ ማሳያና የጉዳዩን የአሳሳቢነት ልክ የሚያጠይቅ ነው።

መንግስት ህገ-ወጥ ስደተኞችን ከሳውዲ አረቢያ ለማስመለስ የሚያደርገውን ጥረት ስደተኛ ቤተሰቦቻቸውን የማሳመን ዘመቻ በሁሉም ክልሎች እየተደረገ ነው።የዘመቻው መነሻ  የሳውዲ መንግስት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ምንም ዓይነት እንግልት ሳይደርስባቸው በሰላም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት ከላይ በተመለከተው መልኩ ሆኖ መገኘቱ ነው ። የዘመቻው መድረሻ ደግሞ በተለያየ ምክንያት አዋጁ የሚዘገይ ወይም የሚቀር የሚመስላቸው አንዳንድ ቤተሰቦችና ጓደኞች ዜጎች በወቅቱ ወደ ሃገራቸው እንዳይመለሱ የሚያደርጉትን ግፊት እንዲያቆሙ ማስቻል ነው።

ዘመቻው የስልክ መልእክቶችንም ያካትታል። በየአካባቢው የተቋቋመው ግብረሃይል የየራሱን አካባቢ ህገወጥ ስደተኛ የአዋጁ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት በሰላም እንዲመለሱ በየጊዜው በስልክ እያሳሰበ ነው። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ እየተደረገ የሚገኘው የክልሎች  ጥረት ስደተኞች በየአካባቢያቸው ሊሰማሩበት በሚችሉት የስራ መስክ አጫጭር ስልጠና የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታንም ታሳቢ ያደረገ ነው።

 

ይህ ብቻ አይደለም ። በሳውዲ አረቢያ ያለ ፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማነሳሳት ከአማራ፣ ኦሮሚያና ከትግራይ ክልሎች የተውጣጣ የልዑካን ቡድን ወደ አገሪቱ ማቅናቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከላይ ለተመለከተው የሬዲዮ ፕሮግራም ገልጿል። ግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ-ኃይልም ዜጎችን ለማስመለስ በትኩረት እየሰራ ሲሆን፤ ከልዑካን ቡድኑ በተጨማሪ ዜጎችን የማስመለስ ሂደቱን የሚያግዙ 12 አባላት ያሉት የዲፕሎማቶች ቡድን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት አስቀድሞ ወደ አገሪቱ ተልኳል፡፡ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎች የመገልገያ ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመቀናጀት ሁኔታዎችንም አመቻችቷል።

በእነዚህ በተቀሩት የምሕረት ቀናት ወደ አገራቸው ለሚገቡ ዜጎች 21 ዓይነት የግል መገልገያ ዕቃዎች ላይ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ መብት እንደሰጣቸው፣ ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላም በአነስተኛና ጥቃቅን በመታቀፍ መሥራት እንደሚችሉና ከእዚያ የተሻለ እዚህ መኖር የሚያስችላቸው እድል ተመቻችቷል ፤የሃገሪቱ ኢኮኖሚም ለዚህ የሚበቃ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በተሰጠው የጊዜ ገደብ አገሩን ለቀው የማይወጡ ዜጎች ላይ የሳዑዲ መንግሥት ከበፊቱ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ የማያከራክር ለመሆኑ ከላይ የተመለከቱት ማሳያዎች በቂ ናቸው፡፡ በተሰጠው የምህረት ጊዜ የማይጠቅሙ ዜጎች በየቤቱ አስሰው የፀጥታ ኃይሎችም ሥልጠና ወስደው ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በዜጎች ላይ ካለፈው ጊዜ ጠንከር ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊከሰት እንደሚችልም አስተያየት እየተሰነዘረ ነው፡፡

ለእነዚህ ህገወጦች በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረገና፣ ያስጠለለ እስከ 100,000 ሪያድ ይቀጣል፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመኪና ያጓጓዘ ደግሞ መኪናውና ሙሉ ንብረቱ ይወረሳል፤ ይታሰራል፣ ከዚያም ወደ መጣበት አገር እንዲባረር ይደረጋል፡፡

ማስጠንቀቂያው ጨርቄን ማቄን ሳያሰኝ ወደ አገር እንዲገቡ የሚያስገድድ ዓይነት አቅም ቢኖረውም  እስካሁን ወደ አገር ቤት የተመለሱ ሰዎች ቁጥር ከላይ በተመለከተው መልኩ ከታሰበው በታች መሆኑ ያሳስባል፡፡  የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበርን ጨምሮ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ቢሆንም  ከላይ ከተመለከተው ተመላሾችና የመመለስ ፍላጎት አኳያ ከዚህ የበለጠ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

የተሰጠው የጊዜ ገደብም ሊጠናቀቅ የቀረው ጥቂት ቀናት ብቻ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ዘመቻ ያስፈልጋል። ማኅበረሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ዜጎች ወደ አገር እንዲገቡ ግፊት ሊያደርግባቸው ይገባል። ጉዳዩ የሕይወትና የሞት ጉዳይ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል፡፡  ምክንያቱም የሳውዲ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በየትኛውም አገር ዜጎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የደረሰበት ውሳኔ ለመሆኑ በተደጋጋሚ ገልጿልና፡፡ ስለሆነም  የአንድን አገር ሉዓላዊነት የመጠበቅ ግዴታ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የህዝብም መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በተሠጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገር መመለስ ከመሞት መሰንበት እንዲሁም የአንድን አገራዊ ሉዓላዊነት መጠበቅ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy