Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

  ስደት ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አያውቅም

0 347

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  ስደት ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አያውቅም

                        ሰለሞን ሽፈራው

ሀገራችን ሌሎች የዓለም ህዝቦች በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያት እየተሰደዱ የሚመጡባት እንጂ ዜጎቿ የሚሰደዱባት ሀገር እንዳልነበረች የሚያመለክቱ መዛግብት ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይም ከሚከተሉት ሃይማኖታዊ እሳቤ ጋር ተያይዞ ከሚቃጣባቸው የጥፋት አደጋ ለማምለጥ ሲሉ በተለያየ ጊዜ ወደ ጥንታዊ ሀገረ ኢትዮጵያ በስደት መልክ እየመጡ እንደተጠለሉና ህልውናቸውን ለማስቀጠል ስለቻሉት ህዝቦች የተፃፉ ድርሳናትን ማስታወስ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ለዚህም አብነት መጠቀስ ያለባቸው ሁለት ታሪካዊ እውነታዎችን ብናስታወስ ጠቃሚ የጋራ ግንዛቤ የምንጨብጥ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ፤ አይሁዳውያንን ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚያስተሳስራቸው የማንነት ቁርኝት እንዲፈጠርም ጭምር ምክንያት ስለሆነው፤ የቤተ እስራኤሎቹ (የፈላሻ ማህበረሰቦች) ታሪካዊ አመጣጥ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባገኙ የጽሑፍ ሰነዶች ላይ የተመለከተው ምስክርነት ነው ፡፡

የአይሁድ እምነት ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦች፤ ገና ከዘመነ ኦሪት (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ጀምሮ፤ የዓባይን ወንዝ ተከትለው እንደመጡና ስር መሰረታቸው ግን፤ ዛሬ እስራኤል ተብላ የምትታወቀው ጽዮናዊት ምድር እንደሆነች ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እውነትነት በመረጃ እያስደገፉ የመዘገቡ ዓለም አቀፍ የጥንታዊ ታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች ስለመኖራቸውም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ፕሮፌሰር ግራሐምሃንኮገር “ታቦተ – ጽዮንን ፍለጋ” በሚል ርዕስ የፃፉትና ጽላተ ሙሴ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ አድርገው የተረኩበት ታዋቂ መፀሐፋቸው ላይ፤ ጉዳዩን ከአይሁዳውያኑ ፈላሻዎች አመጣጥ ጋር ለማያያዝ የሞከሩበት ሁኔታ እንዳለ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

እንዲሁም ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ወደሃገራችን የገባበትን ታሪክ ሲወሳ፤ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ምድር የተሰደዱበት አጋጣሚ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ሀገራችን  ከሌላው ዓለም በፊት መጠጊያ ያጡ ህዝቦች የሚሰደዱባትና ፍትህ ላጡ ጥላ ከለላ ሆና የኖረችበት ታሪክ  ያላት እንደሆነች  ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለዚህም ከላይ እንደ አብነት የተጠቀሱትን ሁለት ታሪካዊ እውነታዎች በተሻለ መልኩ መርምሮ መረዳት እንደሚቻል ይሰማኛል፡፡

ለወትሮው የተቸገሩ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ተቀብላ “ኖሩ ቤት ለእንግዳ!” በማስተናገድ የምትታወቀው ሀገራችን የፍልሰት ሰለባ ከሆነች ሰንበትበት ብሏል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የትውልድ ሀገራቸውን ጥለው የዓለማችን ጥግ በገፍ ሲሰደዱ ለሚስተወሉበት አሳዛኝ ክስተት መሰረታዊ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለውም፤ በተለይም ካለፈው የጦርነት ታሪካችን የወረስነው ድህነት እንዲሁም ደግሞ የድህነታችን መገለጫ የሆነውን የጉስቁልና ኑሮ ሽሽት እንደሆነ ይታመናል፡፡

በተለይም ወደ ባለፀጋዎቹ የዓረብ ሀገራት የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሻለ ህይወት ለመኖር የሚያስችላቸውን ገንዘብ የሚያገኙበት ስራ ፍለጋ እንደሆነ ይታመናል፡፡ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ ዓረብ ሀገራት ሲሰደዱ ተስፋ ያሳደሩበትን ያህል ህይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ገንዘብ ሊያገኙ ቀርቶ፤ ላልተጠበቀ አደጋ እየተጋለጡ ወደ ማይወጡት ማህበራዊ ቀውስ ሲገቡ ማየት እጅጉን የተለመደ አሳዛኝ ትዕይንት ሆኗል ነው ፡፡ ባስ ሲልም በቀጣሪዎቻቸው ግፈኛ ተግባር ከፎቅ ላይ እየተወረወሩ አሰቃቂ አሟሟት እንዲሞቱ የሚደረጉበት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ የ“አተርፍ ባይ አጉዳይ” ክፉ እጣ የሚገጥማቸውን ኢትዮጵያውን ወጣት ሴቶች ቤት ይቁጠራቸው ሲሉ የዓይን ምስክርነት የሚሰጡ ወገኖች ጥቂት እንዳልሆኑ ቢታወቅም፤ እዚህ አገር ውስጥ ተፍጨርጭሮ ራስን ለመቻል ከመሞከር ይልቅ መሰደድን የሚመርጥ ዜጋ ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ እየተመለሱ ያሉት ወገኖቻችን የዚሁ ዘመን አመጣሽ ፈሊጥ ሰለባዎች ናቸው ብለን ብንደመድም ከተጨባጩ እውነታ እምብዛም እንደማያርቀን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡  የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጪ ዜጎች የማባረር እርምጃ ግንባር ቀደም ኢላማ ከተደረጉት፤ የበርካታ ሀገራት ሕገ ወጥ ስደተኞች መካከል የተመደቡት ኢትዮጵያውያን፤ በተለይም የጎረቤት ሶማሊያን ወደቦች እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ተጠቅመው ወደ የመንና ከዚያም ወደ ሳዑዲ የገቡ የባህር ላይ ተጓዦች ስለመሆናቸው የሚያመለክቱ ታማኝ ምንጮች አሉ፡፡

ስደት ሕገ ወጥም ተባለ ሕጋዊ፤ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም የሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን እያነሳን ለአብነት ያህል በማስታወስ መተማመን እንደምንችል ይሰማኛል፡፡ ስለሆነም እስራኤል እንደ ሃገር የመፈጠር ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚወሳ የአይሁዳውያን ከዘመናት የስደት ኑሮ በኋላ ወደ ጽዮናዊቷ ምድር የመመለስ ጉዳይ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አሁን እስራኤል እየተባለች የምትጠራው ሀገር፤ እንደ ጎርጎሪሳውያኑ የዘመን ቀመር በ1940ዎቹ መጨረሻ ለመመስረቷ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቆጠረው፤ በተለይም ወደ አውሮፓ ሀገራት ተሰደው የሁለት ሶስት ትውልዶችን ዕድሜ የፈጀ የስደት ህይወት እንደገፉ በሚነገርላቸው አይሁዳውያን ዲያስፖራዎች ላይ በአዶሊፍ ሒትለር ይመራ የነበረው የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ ያካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻና እንዲሁም የፈፀመው እጅግ በጣም ዘግናኝ ጭፍጨፋ ስለመሆኑ  ዓለም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡  አንዳንድ ታዋቂ የዓለም አቀፍ ታሪክ ፀሐፍት ከዚሁ የአይሁድ ዝርያ ባላቸው አውሮፓውያን ላይ ከተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ተግባር አኳያ ስደትን ለመተቸት በሞከሩባቸው ድርሳናት “መላው ሰብዓዊ ፍጡር ሊማርበት የሚገባ ቁምነገር ቢኖር ሁሉም ህዝቦች የኔ የሚሉት የየራሳቸው ልዐላዊት ሀገር እንደሚያስፈልጋቸው ነው” ሲሉ የሚስማሙበት አግባብ አለ፡፡

የታሪክ ፀሐፍት ሊሂቃን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት፤ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ዲያስፖራዎች ለረጅም ጊዜ እዚያ ከመቆየታቸው የተነሳ ከሀገሬው ተወላጆች እኩል ዜግነት ተሰጥቷቸውና ምናልባትም ከሌላው ህዝብ የበለጠ ሀብት ንብረት ለማፍራት ችለው እንደነበርም ጭምር የሚያውቁ መሆናቸውን ሊገልፁልን ፈልገው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ስድስት ሚሊዮን ያህል የአውሮፓ አይሁዶችን ለናዚ ሂትለሩ የኦሽዊትዝ ጅምላዊ ግድያ እንዲዳረጉ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ከሀገሬው ዜጋ የተሻለ የሥራ ትጋት በማሳየታቸውና ሀብት ንብረት በማፍራታቸው እንደሆነ የሚያምኑ የታሪክ አጥኚ ምሁራን አሉ ማለት ይቻላል፡፡

በእርግጥም ደግሞ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት “የጋራ ቃል ኪዳን ኃይሎች” ተብለው ይጠሩ በነበሩት የነእንግሊዝና አሜሪካ ወታደሮች አሸናፊነት ሲደመደም በህይወት ተርፈው የተገኙት የአውሮፓ ሀገራት ነዋሪ አይሁዳውያን ራሳቸው የሚሊዮኖች ወገኖቻቸውን ጅምላዊ እልቂት ስላስከተለው መንስኤ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚያ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ያጋለጣቸው ቀዳሚ ምክንያት አድርገው የወሰዱት ነገር፤ ምንም እንኳን የሁለት ሶስት ትውልዶችን እድሜ ላስቆጠረ እጅግ ረጅም ጊዜ አውሮፓ ውስጥ ኖሮ ካለፈው ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸው ቢታወቅም በመጤነት ተፈርጀው ዕልቂት የተፈረደባቸው ስደት ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል ነው የሚል አቋም ላይ መድረሱን ነበር፡፡

ቃል በቃል “የሰው ልጅ ቢያንስ እንዲህ እንደኛ እውነቱ የተገለጸለት ቀን ተመልሶ የሚሔድበት የራሱ ሀገር ይኖረው ዘንድ ግድ ነው” ሲሉ የአይሁዳዊ ማንነታቸው መሰረት ወደሚገኝበት መካከለኛው ምስራቅ ከመመለስ ውጪ ቀሪ ተስፋ እንደሌላቸው መወሰናቸውንም የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ከዚያም ከዓለም ዙሪያ እየተሰባሰቡ የዛሬዋን እስራኤል እንደ ሀገር ለመመስረትና የማንነታቸው መነሻ አድርገው በሚወስዱት የመካከለኛው ምስራቅ ምድረ በዳ ውስጥ ጥረው ግረው ሀብት እያፈሩ ከቶውንም ሌሎች ህዝቦችን በስደት መልክ የሚያስጠጉ ጭምር ለመሆን የበቁት፡፡

ስለዚህ ከሳዑዲ ዓረቢያ በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ጨምሮ ሌሎችም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በተለያዩ ባለፀጋ ሀገራት ውስጥ የስደት ህይወት እየገፉ የሚገኙ ዜጎቻችን ሁሉ ከዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ጠቃሚ ልምድ ቢቀስሙ ራሳቸውን ካላስፈላጊ እንግልት መታደግ አልፎም የዘለቄታዊ እጣፈንታቸው መቃናት አለመቃናት ለሚወሰንባት እናት ሀገራቸው የጸረድህነት ትግል ዳር መድረስ ትርጉም ያለው እውነታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት የማይችሉበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ይሰማኛል፡፡ ምንም እንኳን እንደኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ዜጎቻቸው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በገፍ ሲሰደዱ የሚስተዋሉበትን እውነታ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ገና ብዙ የቤት ስራ መስራት እንዲጠበቅባቸው ቢታመንም፤ ግን ደግሞ አገር ጥሎ መሰደድ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ ይጠቅማል ባይነኝ፡፡ ለማንኛውም ግን፤ ከሳዑዲ አረቢያ ለተመለሱት ወገኖቻችን እንኳን በሰላም ወደ እናት ሀገራችሁ ለመምጣት አበቃችሁ እያልኩኝ አበቃለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy