Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብቃትና ምርቃት

0 434

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብቃትና ምርቃት

ብ. ነጋሽ

ምርቃት መልካም ምኞት ነው። ከምኞትም ይዘላል። ምርቃት ምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ ምኞትን እንዲሞላ መማለድም ነው። የቅዱሳን፣ የአዋቂዎች (አዛውንት)፣ የወላጆች ምርቃት እንደስጦታ የሚቆጠረው ለዚህ ነው። ልጆች ይመረቃሉ፤ እንዲያድጉ። ሰዎች የኑሮ እርከኖችን ሲሻገሩ፤ ትዳር ሲመሰርቱ፣ ጎጆ ሲወጡ፣ ተምረው ወይም ሰልጥነው ወደአገልጋይነት ሲሻገሩ፣ ሲሾሙ፣ ሲካኑ ወዘተ ይመረቃሉ፤ መጪው እንዲቀናቸው። ሰዎች ኑሮን አዲስ ወደሚጀምሩበት ስፍራ ሲሸኙም ይመረቃሉ። ስራ ሲጀመር፣ መሰረት ሲጣል . . . ምርቃት ይካሄዳል።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለምርቃት ምንነት መተንተን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያለነበት ወር – ሰኔ በየደረጃው ትምህርትና ስልጠና በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደአገልግሎት የሚሸኙበት – የሚመረቁበት ወር መሆኑን መነሻ በማደረግ፣ አጠቃላይ የሃገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ሁኔታና ብቃት ያለው ያለው የሰው ሃይል ፈጠራ ሂደት ላይ አስተያየት መስጠት ነው።

ባለፉ ሃያ ስድስት ዓመታት በሃገሪቱ የትምህርት ልማት እጅግ ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። በ1984 ዓ/ም 4 ሺህ ብቻ የነበረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር አሁን ወደ 40 ሺህ ገደማ ደርሷል። 280  ብቻ የነበሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርተ ቤቶች አሁን ከ3 ሺህ 5 መቶ በላይ ደርሰዋል። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከአስር እጥፍ በላይ ነው ያደገው። በትምህርት ሽፋን ረገድ አንደኛ ደረጃ ከ95 በመቶ በላይ ደርሷል። የሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሃምሳ በመቶ ገደማ ነው። የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን አሁንም የሚቀረው ቢሆንም፣ ባለፉ ዓመታት የተመዘገበው እድገት ግን ቀላል የሚባል አይደለም።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ቁጥር 16 ብቻ ነበር። አሁን የኮሌጆቹ ቁጥር 1 ሺህ 350 ደርሷል። በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ቁጥር በ85 እጥፍ ነው ያደገው። ይህ እጅግ የሚያስደንቅ እድገት ነው።

ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስንመለስ፣ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት 2 ብቻ የነበሩት የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን 36 ደርሰዋል። 10 ዩኒቨርሲቲዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ። የዩኒቨርሲቲዎች አመታዊ የቅበላ አቅም ከ1 መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ደርሷል። ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት መለስተኛ ኮሌጆችን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅበላ አቅም 10 ሺህ እንኳን አይሞላም ነበር።

አሁን በአጠቃላይ በትምህርት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ 30 ሚሊየን ይጠጋሉ ተብሎ ይገመታል። ይህ አሃዝ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ዜጎቸ አንድ ሶስተኛው በትምህርት ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል።

በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር (የግል ተቋማትን ጨመሮ) ከግማሽ ሚሊየን ይበልጥ እንደሆነ እንጂ አያንስም። በየዓመቱ ግማሽ ሚሊየን ያህል ተማሪዎች በተማሩት/በሰለጠኑበት ሞያ በቂ እውቀት አግኝተዋል ተብለው ወደስራው ዓለም እንዲሸጋገሩ በመልካም እድል ምኞት ተመርቀው ይሸኛሉ ማለት ነው። በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተመለከትነው ምርቃት ይህ ነው።

የሃገሪቱ የትምህርትና የስልጠና ዘርፍ ጥመርታ 70 በመቶ ሳይንስና ቴክኖሎጂ 30 በመቶ ደግሞ ማህበራዊ ሳይንስ ነው። የዚህ ጥመርታ ዓላማ የሃገሪቱን ወቅታዊና መጪ የሰው ሃይል ፍላጎት ያገናዘበ ነው። ሃገሪቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ላይ ትገኛለች። የሰው ሃይል ፍላጎቷም በዚህ እቅድ የሚወሰን ነው።

ሃገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የምትገኘው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብ በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ነው። መዋቅራዊ ሽግግሩ ግብርና ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚ ወደኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ማሸጋገርን ይመለከታል። ከዚህ በተጨማሪ በግብርናው ውስጥም ትራንስፎርሜሽን ማደረግን ይመለከታል። ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደኢንደስትሪ መር በማሸጋጋር መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት፣ ግብርናውን ባለበት ወዝቶ ኢንደስትሪውን ነጥሎ ማሳደግ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱንም ዘርፎች በፍጥነት እያደጉ በእድገት ፍጥነት ግን ኢንደስተሪው ልቆ በኢኮኖሚው ውስጥ ባለው ድርሻ የበላይ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው።

ይህ ደግሞ በግብርናው ውስጥም ትራንስፎርሜሽንን ይጠይቃል። የግብርናን ያህል እድሜ ያስቆጠረውንና የእርሻ ስልት ምርታማነትን ማሳደግና ብክነትን መቀነስ ወደሚችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሸጋገርን ይሻል። ይህ ካልሆነ ግብርናውን አሁን ባለው የእርሻ ስልት ከሚገኝበት ደረጃ ብዙ ማሳደግ አይቻልም። አብዛኛው የሃገሪቱ የእርሻ ሰራ የሚከናወነው በቤተሰብ ደረጃ በተያዘ አነሰተኛ ማሳ ነው። በዚህ አነሰተኛ ማሳ ላይ ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ማሳደግ፣ የእርሻና ምርት መሰብሰቢያ ተመጣጣኝ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የግድ ይላል። በአርሶ አደሩ አቅም ሊሰራባቸው የሚችሉ ውሃ ቆጣቢ፣ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ የመሰኖ እርሻ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር በተለይ ሃገሪቱን በተደጋጋሚ የሚያጠቃትን ድርቅ ተቋቁሞ የእርሻ ስራን ለማከናወን ስለሚያስችል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።

ከዚህ በተጓዳኝ በግብርና ውስጥ የጎላ ድርሻ የሚኖራቸው ሰፋፊ የንግድ እርሻዎችን ማስፋፋት አስፈላጊ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እነዚህ ሰፋፊ እርሻዎች የዘመኑን የረቀቀ የእርሻ ሜካናይዜሽን የሚጠቀሙ ናቸው። በአጠቃለይ ግብርናውም ውስጥ ከላይ ለማሳያነት ያህል የተጠቀሰው ትራንስፎርሜሽን ይካሄዳል።

ከላይ የተገለጸው የግብርና ትራንስፎረሜሽን እንዲሁም እጅግ በአነስተኛ መጠን ያለውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ በመፍጠርና በማስፋፋት በአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ሰፊ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ይሻል። በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይለ በሌለበት ትራንስፎርሜሽንን ማሳካት ጉም እንደመዝገን ይቆጠራል። እናም የሃገሪቱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከህብረተሰብ ሳይንስ ጋር ያለው ጥመርታ 70 በ30 እንዲሆን የማድረጉ ዓላማ፣ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ማስቀጠልና ግቡን እንዲመታ ማድረግ የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ሃይል መፍጠር ነው።

የትምህርት ዘርፍ ጥመርታው ዓላማ የሃገሪቱ መጪ የኢኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜን የሚጠይቀውን የሰው ሃይል ማፍራት ከመሆኑም በተጨማሪ የሰለጠነው የሰው ሃይል እሴት መፍጠርና መጨመር የሚያስችል ስራ ላይ እንዲሰማራ የሚያደርግ ሁኔታንም ይፈጥራል። የሃገሪቱ የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ እድገትና ትራንስፎርሜሽኑን ማሳካት የሚያስችል የእሴት ፈጠራና ጭመራ ስራ ላይ መሰማራቱ ይፋ ስራ አጥነትን ከማቃለል በተጨማሪ፣ ስውር ስራ አጥነት (disguised unemployment) የሚኖርበትን እድልም ያጠባል። ይህም ሁሉም በስራ ላይ የተሰማራ የሰው ሃይል አምራች እንዲሆን ያደርጋል። የሰው ሃይልን በአግባቡ በመጠቀም እድገትና ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ፣ በስራ ፈጠራ ዜጎችን ተጠቃሚ ማደረግ ማለት የሄው ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የማሰልጠን ተግባር፣ ተቀጣሪነትን በመጠበቅ የማይገደብ ስራ ፈጣሪ የሰው ሃይል የማፍራት ተግባር ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል አሁን ሃገሪቱ የኢንደስትሪውን እድገት ለማረጋገጥና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የምትከተለው የአነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማትን የማስፋፋት እቅድን ተግባራዊ ለማድረግም ያግዛል።

በአጠቃላይ፤ ትምህርት ቤት ገብተው የሚወጡ ዜጎች በተጨባጭ ኢኮኖሚን ማሳደግና ትራንስፎርም ማድረግ የሚያስችሉ፣ በሃብት ፈጠራ ራሳቸውን መደገፍና መበልጸግ የሚችሉ እንዲሆኑ ማደረግ ይገባል። ይህ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን እውቀትና ክህሎት የዘው እንዲመረቁ ማድረግን ይሻል። ጥቁር ካባ ለብሶ በእንኳን ደስ ያላችሁ ሆታና እልልታ “መመረቅ” ብቻውን ብቃትን አያረጋግጥም። እናም የትምህርት ተቋማት በአግባቡ ያሰልጥኑ፣ በዕውቀት ያበቁትን ብቻም ያስመርቁ።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy