Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ነጩ አብዮት ሸፍጥ

0 434

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ነጩ አብዮት ሸፍጥ

 

 

አሜን ተፈሪ

ባለፈው ዓመት የታየው ሐገራዊ ሁኔታ ለኢህአዴግ፣ ለመንግስት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወጣቶችና ለመላው የሐገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር፡፡ ከመንግስት እና ከገዢው ፓርቲ አኳያ የተገኘው ትምህርት፤ ህዝቡ በመንግስት ዕቅዶች፣ ፕሮግራሞች እና መመሪያዎች ላይ የተሟላ ግንዛቤ እንዲያገኝ አለማድረግ ችግር እንደሚያስከትል የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በቂ ግንዛቤ ባልተፈጠረበት ሁኔታ ተግባራዊ የሚደረጉ ዕቅዶችን፤ አፍራሽ ኃይሎች የጥፋት መለከት አድርገው እንደሚጠቀሙባቸው አይተናል፡፡ ዕቅዶች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት ከህዝቡ ጋር ካልተመከረባቸው፤ ችግሩ ከዴሞክራሲያዊ አሰራር መጓደል ጋር ብቻ ተያይዞ የሚታይ የመርህ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከልማት ጉዟችን የሚያደናቅፍ ሁከት እንደሚዳጋብዝ ተመልክተናል፡፡ ወርቅ የሚያዘንብ ዕቅድ ተነድፎ፤ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጣ አስተውለናል፡፡ በመሆኑም፤ የመንግስት ዕቅዶች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት ህዝቡ በጉዳዩ ላይ እንዲመክርበት አለማድረግ፤ የመልካም አስተዳደር አንድ ምሰሶ የሆነውን የአሳታፋፊነትን ጉዳይ የሚያጓድል አሰራር ከመሆን አልፎ፤ የህዳሴ ጉዟችንን የሚያደናቅፍ አደጋ እንደሚጋብዝም ተመልክተናል፡፡

 

ባለፈው ዓመት የታየው የተቃውሞ ሰልፍ እና ግርግር በዋነኛነት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ይታይ እንጂ ሌሎች ክልሎች ከችግሩ ነፃ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረው የችግሩ ዋነኛ መንስኤ፤ ህዝቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያሳድር ያደረገው የመልካም አስተዳደር ችግር በመሆኑ ነገሩ በሁለቱ ክልል ብቻ የተወሰነ ሊሆን አይችልም፡፡ የድህነት፣ የስራ አጥነት፣ የማንነት፣ የወሰን፣ የመሰረተ ልማትና የተለያዩ አገልገሎቶች አለመሟላት ወዘተ … ችግሮች መጠናቸው ሊለያይ ካልሆነ በቀር በሁሉም ክልሎች የታዩ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ በሁሉም ክልሎች የሚገኘው ህዝብ ተቃውሞውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይገልጽ ነበር፡፡

 

ይህ የህዝብ ቅሬታ አንድ አቀጣጣይ ነዳጅ ሆኖ የሚያገለግል አጀንዳ ሲገኝ ድንገት ቦግ የሚል እሣት ሲሆን አይተናል፡፡ የሁከት ኃይሎች አጀንዳውን የህዝቡን ስሜት በሚገዛ አኳኋን እየተጠመዘዙ፤ የሁከት ማቀጣጠያ ነዳጅ አጀንዳ ሲያደርጉት ታዝበናል፡፡ በመሆኑም፤ መሰረታዊውን ችግር ለመፍታት በፍጥነትና ውጤታማ በሆነ አግባብ መረባረብ አስፈላጊነቱ እንዳለ ሆኖ፤ የመንግስትን ዕቅዶች በተገቢው ጊዜ እና በተሟላ ሁኔታ ለህዝብ ማብራራት አስፈላጊ መሆኑ በኢህአዴግ ደረጃ የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል፡፡

 

ይህ ችግር ከቀለም አብዮት ነጋዴዎች ፍላጎት ጋር ተቀናጅቶ አሳሳቢ ቅርጽ ይዟል፡፡ እንደሚታወቀው፤ የቀለም አብዮት ነጋዴዎች ‹‹ለምዕራባውያን ፍላጎት የማያድሩ ናቸው›› የሚሏቸውን እና ‹‹እየተጠናከሩ ከሄዱ አይታዘዙንም›› ብለው የሚፈርጇቸውን መንግስታት በሁከት ገበያ ሊሰቅሏቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከውስጥ የሚኖርን ቅሬታ በማራገብና ከውስጥም ከውጭ የሚኖርን ተቃዋሚ ኃይል ገደብ በሌለው ድጋፍ በማደራጀት በተለያየ ቀለም የተሰየሙ አመፆችን በማነሳሳት ጠንካራውን መንግስት በመጣል አሻንጉሊታቸው በሆነ ደካማ መንግስት የመተካት ፍላጎት ያላቸው የቀለም አብዮተኞች ናቸው፡፡

 

ስለሆነም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ለምዕራባውያን ፍላጎት የማያድር በመሆኑ፤ ይህ መንግስት እየተጠናከረ ከሄደ አይታዘዘንም ብለው የሚያስቡ ወገኖች፤ በተለያየ ጊዜ ልማታዊውን መንግስት በቀለም አብዮት ለመናጥ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ሙከራቸው እየከሸፈ ህልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የነጩ አብዮት ህልም ከስሟል፡፡

 

ታዲያ እነዚህ ወገኖች ባለፈው ዓመት ተከሰቶ የነበረውን ችግር፤ ከመቸውም ጊዜ የተሻለ ልዩ አጋጣሚ አድርገው በመውሰድ ባለ በሌለ አቅማቸው ተረባርበው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት የታላቁ መሪ የመለስ ዜናዊን አራተኛ ዓመት መታሰቢያን እንደ መነሻ በመውሰድ ነጭ ቲሸርት አዘጋጅተው ለመበተን፣ ቲሸርቱ ያልደረሰውም የየራሱን ነጭ ልብስ ለብሶ አደባባይ እንዲወጣ በማህበራዊ ሚዲያዎች አውጀው ነበር፡፡ የቀለም አብዮት ነጋዴዎች አሁንም በገበያው አሉ፡፡ የቀለም አብዮት ነጋዴዎች ተንቀሳቃሽ ዒላማዎች ናቸው፡፡ የእነሱን ፍላጎት ወይም ተፈጥሮ መቀየር አንችልም፡፡ ሆኖም ራሳችንን መቀየር እንችላለን፡፡ ሐገራችንን የመቀየር ሥራችን ራሳችንን በመቀየር የሚፈጸም ነው፡፡ ሳንውል ሳናድር ራሳችንን መቀየር ይኖርብናል፡፡

 

ስለሆነም ባንድ በኩል የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የሆነውን ውስጣዊ ድክመታችንን ይዋል ይደር ሳንል መፍታት፤ በዚህ ረገድ መላው ህብረተሰብና ወጣቱ የመፍትሄው አካላት በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ መንግስት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጡ መድረኮችን መክፈት፣ በህዝቡና በመንግስት መካከል ከመቸውም ጊዜ በላይ መቀራረብና ጠንካራ ትስስር መፍጠር፣ ይህንንም የሚያሳልጡ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ፣ የአደረጃጀትና አሰራር ለውጦችን ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል፤ ደግሞ ሐገሪቱን ለማተራመስ የሚደረግን ማናቸውንም አፍራሽ ድርጊት የመመከትና በመላ ሐገሪቱ ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ይኖርበታል፡፡

 

ባለፈው ዓመት የታዩት ሁከቶች በመሰረቱ ሳይፈቱ የቆዩት ችግሮቻችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ የተጀመረው ዕድገትና ተስፋ ሰጭ ጉዞ ሳይሰናከል ቀጥሎ ያልተፈቱት ችግሮች የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲኖር እና የሐገሪቱ ሰላም እንዳይናጋ ሳይፈቱ የቆዩት ችግሮቻችንን በፍጥነት መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ስጋት የተፈጠረው ከሥሩ ሊነቀል ይገባል፡፡ ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› ከሚል ጥርጣሬ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ አፍራሽ ኃይሎች ዋነኛ መሣሪያቸው ባደረጉት የማህበራዊ ሚዲያ በየደቂቃው የሚሰራጨው የፈጠራ ወሬና አሸባሪ መልዕክት በቀላሉ ህዝቡን የሚያደናግረው፤ ኢህአዴግና መንግስት ህዝቡ እንዳይደናገር እና ትክክለኛውን ሁኔታ እንዲረዳ የማድረግ ሥራቸው ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ችግር መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፡፡  

 

በርግጥ ኢህአዴግና መንግስት፤ ህዝቡን ‹‹በርግጥ ችግሩ ይፈታ ይሆን?›› ከሚል ጥርጣሬ የሚያላቅቅ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ስጋቱን የሚያቃልል ተጨባጭ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ በማመን፤ ይህንን እውን ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡

 

ኢህአዴግ በ4ዐ ዓመት የትግል ጉዞው ውስጥ በርካታ ችግሮች ተፈታትነውት ሁሉንም ትክክለኛ የችግሮች አፈታት ስልት በመጠቀም ብዙም ጉዳት ሳያደርሱ መፍታት እንደቻለ የድርጅቱ ታሪክ ያስረዳል፡፡ የድርጅቱን ህልውና የሚፈታተኑ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ ሰፋፊ የእርማትና የተሃድሶ ንቅናቄዎችን በማካሄድ ስር ነቀል መፍትሔ በመስጠት ለድል መብቃት ችሏል፡፡ ይህ የድርጅቱ ታሪክ አሁን እየወሰዳቸው ካሉ ርምጃዎች ጋር ተዳምሮ ተስፋን ማለምለም ይችላል፡፡

 

ኢህአዴግ ይህንን ዕድል በዋዛ ፈዛዛ ካስመለጠው ሐገሪቱ ወደ ኋላ የምትሄድበትን ርቀት መገመት ያስቸግራል፡፡ እንደገና ወደ ህዳሴው መድረክ ለመመለስ የሚኖረውም ጉዞ ወደ ኋላ ከሄድንበት ርቀት እጅግ የረዘመ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የሐገራችን ወጣቶች፤ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል በእጃቸው ላይ እንዳለ በመገንዘብ፤ ይህን ዕድል አጥብቀው ሊይዙትና በየጊዜው እየዳበረ እንዲሄድ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በምንም ምክንያት በእጃቸው ባለው ዕድል ላይ ቁማር ሊጫወቱ አይገባም፡፡ ኢህአዴግ የሐገራችን ወጣቶች ሐገር የመረከብ ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ዛሬም እንደዱሮው የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ የወጣቶች የልማትና መልካም አስተዳዳር ፍላጎቶች ሊሟሉ የሚችሉት በሐገራችን ሰላምና የህግ የበላይነት በተረጋገጠበት ሁኔታ መሆኑን ወጣቶች እንዲረዱ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ሰላምና የህግ የበላይነትን በማረጋገጡ እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ተጨባጭ ሥራዎችን መስራት ይገባዋል፡፡

 

ከሰሞኑ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው፤ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ መስተዳደር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም ለመወሰን የወጣው ረቂቅ ደንብ እንደከዚህ ቀደሙ የተሳሳቱ ጥያቄዎች ማዳወሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የተሳሳቱ ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ ብቻ የሚገለፁ መሆናቸው አሳሳቢ ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ አምና እንደታዘብነው ጥያቄው የተሳከረ ወይም ቁጣው በማን ላይ እንደሆነ የማይታወቅ አመጽ የሚካሄድበት ዕድል እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ ወጣቶች አይደለም ለተመልካች ለራሳቸው ግልፅ ባልሆነ አካሄድ፤ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል በፈጠሩና ለህዝቡ አገልግሎት በሚሰጡ የመንግስት፣ የህዝብና የግለሰቦች የልማት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል፡፡ የስራ አጥነት ችግር ይፈታ እያሉ ለወንድም  እህቶቻቸው የሥራ ዕድል የፈጠሩ ተቋማትን በማፈራረስ ከነበራቸው ሥራ ተፈናቅለው ለሥራ አጥነት የሚዳርጉ፤ የመሰረተ ልማት አልተሟላልንም እያሉ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን የሚያወድሙ፤ የኑሮ ውድነት ይቃለል የሚል መፈክር እያሰሙ ዜጎች የዕለት ሥራቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዳያከናውኑ፣ የሸቀጦች ዝውውር እንዳይኖር መንገድ በመዝጋት፣ የንግድ ቤቶች እንዳይከፈቱ በማወክ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ወጣቶች ሊኖሩ አይገባም፡፡

 

በርግጥ ኢህአዴግና መንግስት በሰልፎቹ የተሳተፉ ወጣቶች በሙሉ በእንደዚህ ዓይነት አፍራሽ ድርጊት ተሰማርተዋል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ ጥፋቱን የሚፈፅሙትና በሰልፉ ቦንብ፣ ሽጉጥና ጠመንዣ ታጥቀው በመግባት የፀጥታ ኃይሎች ህግ ለማሰከበር ያደረጉትን ጥረት ወደ ግጭት የቀየሩት ጥቂት የተለየ ዓላማ ካላቸው ኃይሎች ጋር የተሳሰሩና የተወናበዱ ወጣቶች እንደሆኑ ይገነዘባሉ፡፡

 

በዚህ ሂደት የገበያ ግርግር እንዲሉ በሁከቱ የሚሳተፉ የነበሩትን ያህል ጥያቄያችንና ተቃውሟችንን በሰላማዊ መንገድ ነው ማሰማት ያለብን ብለው የተከራከሩና በቻሉት አቅምም ጥፋቶች እንዳይፈፀሙ ሲከላከሉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ወጣቱ ኑሮውን እንዲያማርር ያደረጉ ችግሮች እንዲፈቱለት መጠየቅ ይችላል፡፡ ጠይቆ  ያልተፈቱለት ችግሮች ሲገጥሙት በመንግስት ላይ ያሳደረውን ቅሬታ በአደባባይ መግለጽ ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ሲያደርግ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሐገሪቱን ለማፈራረስ ወደ ታቀደ የቀለም አብዮት ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱትን አፍራሽ ኃይሎች ነቅቶ መከላከል ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግ የነጩ አብዮትን ተስፋ ማምከን ይኖርብናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy