Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ነፍስ አስይዘው የሚገቡበት ጨዋታ

0 582

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ረቡዕ ቀትር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእንግዳ መጠበቂያና ካፍቴሪያው  ከሳዑዲ በመጡ ኢትዮጵያውያን ተሞልቶ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ተመላሾች ሴቶች ሲሆኑ የእስልምና ሃይማኖት ደንብ በሚፈቅደው ኢጃብና እስከ ዓይናቸው በሚደርስ ኒቃም ተሸፍነዋል፡፡ ያላቸውን ምንም ሳያስቀሩ ጠቅልለው መምጣታቸውን ከጎናቸው የደረደሩዋቸው አለመጠን የተጠቀጠቁ ሻንጣዎችን ዓይቶ መገመት አይከብድም፡፡ ከተመላሾቹ መካከል ነፍሰጡርና አራስ ልጆች የያዙ አሉ፡፡

እነዚህ ወደ አገራቸው  የተመለሱት መንገደኞች የሚቀበላቸው ዘመድ እስኪመጣላቸው ለሰዓታት መጠበቅ  ግድ ብሏቸዋል፡፡ ደርሻለሁ  እዚህ ጋር ነኝ ለማለት ስልክ እየተዋዋሱ ለዘመዶቻቸው ይደውላሉ፡፡ ባሉበት ሆነው የሚያንቀላፉም ነበሩ፡፡ ዓይናቸውን አንድ ቦታ ተክለው በሐሳብ ጭልጥ ብለው የጠፉም ጥቂት አልነበሩም፡፡ ብዙዎች ደግሞ የመከፋትና የሀዘን ስሜት ይነበብባቸዋል፡፡ የሚቀበሏቸው ሰዎች ሲመጡም እንግዳ እንደሚቀበሉ ሰው ሳይሆን የተከፋን እንደሚያፅናኑ ነው አቅፈው ሰላም የሚሉዋቸው፡፡ በዚህ መካከል ሆድ የሚብሳቸውና የሚያለቅሱ ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ከፊታቸው ደስታ የሚነበብባቸውም አሉ፡፡

የ27 ዓመቷ ሀዲያ ሁሴን የሰባት ወር ነፍሰጡት ነች፡፡ ረጅሙ ጉዞ ከእርግዝናዋ ጋር ተደምሮ አድክሟታል፡፡ አነስ የሚለው ሻንጣዋ ላይ ቁጭ እንዳለች የዘመዶቿን መምጣት መጠባበቅ ይዛለች፡፡ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ላስጠበቋት ዘመዶቿ ደጋግማ ስልክ ትደውላለች፡፡ ያለችበትን ቦታ ሳትሰለች ደጋግማ ትነግራቸዋለች፡፡

ትውልድና ዕድገቷ በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ሲሆን ወላጆቿ የሚተዳደሩት በግብርና ነው፡፡ ኑሯቸውን ለማሻሻል ሀዲያን ወደ ሳዑዲ መልክ ግድ ሆነ፡፡  የቤተሰቡቿን ኑሮ የማሻሻል ሃላፊነት የወደቀባት ሀዲያ የዛሬ አምስት ዓመት የትውልድ ቀዬዋን ትታ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተሰደደች፡፡

አካሄዷ በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ኞሯት ነበር፡፡ ይሁንና ከሁለት ዓመታት በላይ በህጋዊነቷ መቆየት አልቻለችም፡፡ ህገወጥ ሆና የምኖርበት አንድ አጋጣሚ  ተፈጠረ፡፡

አሰሪዎች የሠራተኞቻቸውን ሕጋዊ መረጃዎች በመያዣነት የመቀበል ልምድ አላቸው፡፡ ፓስፖርት፣ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ ሳይቀር አሠሪዎቻቸው ጋር እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ቢፈልጉ መረጃዎቻቸውን መውሰድ የሚችሉት አሠሪዎቻቸውን አስፈቅደው ነው፡፡ ጉዳያቸውን ከጨረሱ በኋላም መልሰው ሊሰጧቸው ግድ ነው፡፡ በዚህ መስማማት ካልቻሉ የብዙዎቹ ዕጣ ፈንታ   ሕጋዊ መረጃዎቻቸውን ትተው መውጣት ብቻ ይሆናል፡፡

ሀዲያ በወር የሚከፈላት ገንዘብ ለሥራዋ የማይመጥን  እንደሆነ በመግለጽ አሠሪዎቿ እንዲጨምሩላት ትጠይቃለች፡፡ በወር የምታገኘው ከራሷ አልፎ ለወላጆቿ ለመላክ የሚተርፋት ዓይነት አልነበረም፡፡ በመሆኑም አሠሪዎቿን መጠነኛ ጭማሪ እንዲያደርጉላት በተለያዩ ጊዜያት ተለማምጣ ጠይቃቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካላትም፡፡ በወር ይከፈላት የነበረው 700 ሪያድ ብቻ ሲሆን ይህ ከአብዛኛዎቹ ከምታውቃቸው ጓደኞቿ ወርሀዊ  ክፍያ በእጅጉ ያነሰ ነበር፡፡ በዚህ ተማርራም አንድ ቀን ድንገት ከቤት ወጥታ ተሰወረች፡፡

ማንኛውም ሕጋዊ መረጃዎቿ እዚያው አሰሪዎቿ ጋር ነበር የቀሩት፡፡ ከዚያ ቀን በኋላ ሀዲያ በሳዑዲ ምድር ለሦስት ዓመታት ያህል በሕገወጥነት መኖሯን ትናገራለች፡፡ የተሻለ ክፍያ ታገኝ ስለነበር ለቤተሰቦቿ በየወሩ ገንዘብ መላክ ቻለች፡፡ በዚህ ደስተኛ ብትሆንም በሳዑዲ ሕገወጥ ሆኖ መኖር ከባድ ፈተና ውስጥ ከተታት፡፡ ሶስቱን አመታት ስትኖር ከፖሊስ ጋር ድብብቆሽ እየተጫወተች ነበር፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ ሕጋዊ መረጃ የሌላቸው የሌላ አገር ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስበውን አዋጅ ማውጣቷንና በማስጠንቀቂያው መሠረት በተባሉት ቀናት አገሪቱን ለቀው ባልወጡ ዜጎች ላይ ይወሰዳል የተባውን ዕርምጃ እንደሰማች ጭንቀቷ በረታ፡፡ ጥቂት ካንገራገረች በኋላም ከመሞት መሰንበት ብላ ጓዟን ጠቅልላ ረቡዕ ዕለት አገሯ ገባች፡፡ ‹‹በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ መመለስ አልፈልግም›› የምትለው ከዚህ ወዲህ ሀዲያ የራሷን ሥራ የመሥራት ሐሳብ እንዳላት ትናገራለች፡፡

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ማንኛውም ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው የሚኖሩ ስደተኞች ከመጋቢት 20 እስከ ሰኔ 17 ባሉት 90 ቀናት ውሥጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ የምህረት አዋጅ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በአዋጁ መሰረት የተለያዩ አገሮች ዜጎች ወደየ አገራቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና እንደ ሀዲያ ካሉ ጥቂቶች በቀር አብዛኛዎቹ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ እስካሁን ወደ አገር የተመለሱ ሰዎች ቁጥርም በሳዑዲ ከሚገኙ ሕጋዊ ማስረጃ ከሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ቁጥር አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ከተመላሾቹ አንዱ ማማሩ አሰፋ የሳዑዲ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ምድር እንኳንስ ለሕገወጦች ለሕጋዊዎችም ኑሮ ከባድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ማማሩ ሳዑዲ መኖር ከጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድም አለው፡፡ ይሁንና ሕጋዊ መረጃ ብቻ በሳዑዲ ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር ዋስትና እንደማይሰጥ በቆይታው መረዳቱን ይገልጻል፡፡

በወር 2,500 ሪያድ እየተከፈለው የሸሪካ(የአናጢነት) ስራ ይሰራ ነበር፡፡ ይሁንና ደመወዙ ወቅቱን  ጠብቆ  እንደማይደርሰው ይናገራል፡፡ ደመወዝ ሳይከፍሉት ሦስትና አራት ወራት ያልፋሉ፡፡ እስካሁንም 27,000 ሪያድ የሚሆን ያልተከፈለው ውዝፍ ደሞዝ እንዳለው ይናገራል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ተደማምረው ተስፋ  ስላስቆረጡት ወደ አገሩ ለመመለስ በወሰነው መሠረት በዚህኛው ሳምንት አጋማሽ ላይ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡

ነገር ግን ከሱ በባሰ የመብት ጥሰትና ሌሎችም ችግሮች እየደረሰባቸው የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ሕጋዊ መረጃ ሳኖራቸው በሳዑዲ የሚኖሩ ጓደኞቹ እንዳልተመለሱ ይናገራ፡፡ ‹‹የሕገ ወጦች ኑሮ ስቃይ ነው፡፡ እንደ አውሬ  እንደታደኑ ነው የሚኖሩት›› ይላል፡፡ ሕገ ወጦች በሳዑዲ ከፖሊስ ጋር እንደ ዓይጥና ድመት ሆነው ነው የሚኖሩት፡፡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው በስጋት የተሞላ ነው፡፡ ምንም ነገር ሲያደርጉ እንደ ሌባ ተደብቀው ነው፡፡››

እንደዚያም ሆኖ  ከፖሊሶች ዕይታ የማያመልጡ ብዙ ናቸው፡፡ ፖሊሶች ድንገት ሲደርሱባቸው በየአቅጣጫው ይሮጣሉ፡፡ እድለኛ ከሆኑ ያመልጣሉ፡፡ ማምለጥ ካልቻሉ ግን ምንም ቢደርስባቸው ማወቅ እንደማይቻል ማማሩ ያናገራል፡፡ ‹‹ሊያመልጡ ሲሉ ከመኪና ጋር አላትመው ይጥሏቸዋል›› በማለት አብዛኛዎቹ ጓደኞቹ በዚህ መልኩ ሲያዙ ማየቱን ይናገራል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛው ያጋጠመውንም  እንዲህ ያሥታውሳል፡፡

ሕገወጥ ጓደኛው በሳዑዲ መኖር ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና እንቅስቀሴው ሁሉ በጥንቃቄ የተሞላ በመሆኑ በፖሊስ እጅ ገብቶ አያውቅም፡፡ ይህ ግን እስከፈለገው ጊዜ ድረስ ተደብቆ መኖር እንዲችል ማረጋገጫ አልነበረም፡፡ አንድ ቀን ባልጠበቀው አጋጣሚ ፖሊሶች አድፍጠው ጠብቀው በቁጥጥር ስር አዋሉት፡፡ ፖሊሶቹ ምሽት ላይ ቤቱ ሲደርሱ ገላውን እየታጠበ ነበር ያገኙት፡፡ ገላውን እስኪለቃለቅና ልብስ እስኪለብስ አልጠበቁትም፡፡ እርቃኑን ከቤት ይዘውት  ወጡ፡፡ ‹‹ይህ ከሆነ አምስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይኑር ይሙት አላውቅም›› በማለት የሕገ ወጦች ኑሮ በስጋት የተሞላ እንደሆነ ይናገራል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ህጋዊ መረጃ የሌላቸው ከ300,000 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሕገ ወጦች በተለያዩ መንገዶች ወደ ሳዑዲ የገቡ ናቸው፡፡ በየብስ በረሃ አቋርጠው ሲሄዱ ከአውሬ የተረፉም ይገኙበታል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ በደላላ የሄዱና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚደርስባቸው ሲያልፍም እንደ ዕቃ ከፎቅ ተወርውረው ከሞት የተረፉ፣ እንደ ማሽን ያለ ዕረፍት የሚሠሩና የላባቸውን በወጉ ለማግኘት የሚቸገሩ እንደሆኑ ይነገራል፡፡

ራሳቸውን ከዚያም ሲያልፍ ቤተሰባቸውን ለመቀየር ብድር ገብተው፣ ቤት ሸጠው ከቀናቸው የቤት ካርታ አስይዘው፣ ከብት ሸጠው ያላቸውን ነገር አሟጠው የሚሄዱና ሕጋዊ ፈቃዳቸውን በአጋጣሚዎች እንደ ሀዲያ በማጣት የስቃይ ኑሮ የሚገፉ ብዙ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በሳዑዲ የሚኖሩ ሕገወጥ ኢትዮጵያውያን ላይ ከደረሰው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተአምር የተረፉ ነገ የተሻለ ነገር እንደሚኖር ተስፋ በማድረግ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለመኖር የወሰኑ ናቸው፡፡

ከዚህ ሁሉ ስቃይ አገራቸው ተመልሰው ለመኖር የሚፈልጉ ቢኖሩም ‹‹ምን ተይዞ ጉዞ›› በሚል የባለእዳነት ስሜት የተሸበቡ ሲያልፍም በቤተሰብ ግፊት ለመቆየት የሚገደዱ መኖራቸውን ‹‹የሚበሉት አጥተው በጣም የሚቸገሩበት ጊዜ አለ፡፡ በዚህ መካከል ስልክ ደውለው ለምን ገንዘብ አትልኩም ብለው ልጆቻቸውን የሚጨቃጨቁ ቤተሰቦች አሉ፡፡ ያለውን ችግር አይረዱም፡፡ ሁኔታውን ሊያስረዷቸው ሲሞክሩም ጆሮዋቸው ላይ ስልክ ይዘጋሉ፡፡››

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የመኖሪያና ሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ካወጀ ወር አልፎታል፡፡ ይሁንና ካሉት የውጭ አገር 300,000 ሕገ ወጦች ወደ አገሪቱ መመለስ የቻሉት ‹‹ከ30,000 በላይ ናቸው›› በማለት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የታሰበውን ያህል ሰዎች ሊመለሱ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ በተቀሩት የምሕረት ቀናት ወደ አገራቸው ለሚገቡ ዜጎች 21 ዓይነት የግል መገልገያ ዕቃዎች ላይ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ መብት እንደሰጣቸው፣ ወደ አገሪቱ ከገቡ በኋላም በአነስተኛና ጥቃቅን በመታቀፍ መሥራት እንደሚችሉና ከእዚያ የተሻለ እዚህ መኖር እንደሚችሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በተሰጠው የጊዜ ገደብ አገሩን ለቀው የማይወጡ ዜጎች ላይ የሳዑዲ መንግሥት ከበፊቱ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ በተሰጠው የምህረት ጊዜ የማይጠቅሙ ዜጎች የሚታሰሩባቸው ከ80 በላይ እስር ቤቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ በየቤቱ አስሰው ሕገ ወጦችን የሚያወጡ የፀጥታ ኃይሎችም ሥልጠና ወስደው ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በዜጎች ላይ ካለፈው ጊዜ ጠንከር ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊከሰት እንደሚችልም አስተያየት እየተሰነዘረ ነው፡፡

ለእነዚህ ህገወጦች በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረገና፣ ያስጠለለ እስከ 100,000 ሪያድ ይቀጣል፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመኪና ያጓጓዘ ደግሞ መኪናውና ሙሉ ንብረቱ ይወረሳል፤ ይታሰራል፣ ከዚያም ወደ መጣበት አገር እንዲባረር ይደረጋል፡፡

ማስጠንቀቂያው ጨርቄን ማቄን ሳያሰኝ ወደ አገር እንዲገቡ የሚያስገድድ ዓይነት አቅም ቢኖረውም አቶ መለስ እንዳሉት፣ እስካሁን ወደ አገር ቤት የተመለሱ ሰዎች ቁጥር ከታሰበው በታች ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ጉዳዪች በምክንያትነት ይነሳሉ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ህገ ወጥ ደላሎች ለዜጎች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ወደ አገርቤት እንዳይመለሱ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሳዑዲ መንግሥት  በረመዳን ወር እንዲህ ያለ ድርጊት አይፈጸምም፡፡ በረመዳን ምህረት ይደረጋል በማለት እንዳይመለሱ እያደፋፈሯቸው ይገኛሉ፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ እስከ 40 የሚሆኑ ዜጎችን አጉረው በድብቅ በቤትሰራተኝነት እንዲቀጠሩ እያደረጉ ነው፡፡ አሰሪዎቻቸውን ተማምነው የተቀመጡም አሉ፡፡

ሁኔታው ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈፅሞ የነበረው ኢሰብዓዊ ድርጊት ተዘነጋ እንዴ ያሰኛል፡፡ የተለያዩ አገራት ዜጎች በብዛት ወደ የአገራቸው እየተመለሱ ባሉበት ወቅት ኢትዮጵያውያኑ ለመመለስ አለመፈለጋቸውም ጥያቄ ያስነሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም እንደሚሉት፣ የሳዑዲ ጉዳይን በተመለከተ ማኅበሩም ሆነ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ራሱን የቻለ ግብረ ኃይል ተቋቁሞና በጉዳዩ ላይ ጥናት ተደርጎ ከሕዝብ ጋርም ውይይት ተደርጎ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን  እስካሁን የተሰራው በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ የበለጠ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

የተሰጠው የጊዜ ገደብም ከግማሽ በላይ አልፏል፡፡ ነገር ግን የመጡት ሰዎች ቁጥር የተጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ለዚህም የግንዛቤ ችግር ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ዜጎች ወደ አገር እንዲገቡ ግፊት ሊያደርግባቸው እንደሚገባ ‹‹የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው፡፡ የሳዑዲ መንግሥትም ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በየትኛውም አገር ዜጎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡ እኛም የአንድን አገር ሉዓላዊነት የመጠበቅ ግዴታ አለብን›› በማለት በተሠጠው የጊዜ ገደብ ወደ አገር መመለስ ከመሞት መሰንበት እንዲሁም የአንድን አገራዊ ሉዓላዊነት መጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሁኔታው ሕይወት እስከ መጥፋት፣ አካል እስከ መጉደል ሊያጋጥም እንደሚችል፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በዜጎች ላይ ተከስቶ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በማስታወስ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ በጉዳዩ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገሪቱ የሚመለሱትን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተቀብሎ ወደየሚሄዱበት አካባቢ እንዲሄዱ እገዛ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ራሳቸውን የማቋቋም ሐሳብ ላላቸው ማኅበሩ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዜጎች አደጋ ሳይደርስባቸው በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚዲያ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ወደ አገር የሚመለሱ በሌላ ጊዜ በህጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ መግባት እንደሚችሉም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ‹‹ቆሼ ላይ የደረሰው አደጋ ድንገተኛ ነው፡፡ ይህኛው ግን እያየነው የመጣ ጎርፍ ነው፡፡›› በማለት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ፣ ከቀናት በፊት የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍልና ቤተ ዘመድ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ወላጆች ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኝም የሪፖርተር ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ለመውጣት ልጆቹ የራሳቸው ስለመሆናቸው የዲኤንኤ ምርመራ ማድረግና ማረጋገጥ ግድ ይላቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ልጆቻቸውን ይዘው መውጣት ስለማይችሉ ለመቆየት ይገደዳሉ፡፡ አገልግሎቱ በነፃ የሚሰጥ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ማለቅ ሲችል ሳምንታት እየፈጀና ወላጆች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ አገራቸው መግባት እያገዳቸው እንደሆነ፣ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥበት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሊከሰት የሚችለውን ነገር ከወዲሁ በማስጠንቀቂያ መልክ እየሰሙና ከዚህ ቀደም ተከስተው የሚያውቁ ነገሮችን እያወቁ ወደ አገር ለመመለስ ማንገራገር በሕይወት የመቆመር ያህልና ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፡፡ ሁለተኛ እድል ከማይሰጥ ሞት ጋር ፊትለፊት ከመጋፈጥ ከለላ ወደ ሚሰጠው መሸሽ ከሰዎች ተፈጥሯዊ ምላሽነት ባለፈ ብልህነትም ነው፡፡ ስለዚህም የምህረት ቀናቶቹ ከመጠናቀቃቸው አስቀድሞ አገር መግባትና ከዚያም በአገር ውስጥ ያሉ አማራጮችን መመልከት ካልሆነም ነገሮች ሲረጋጉ አዋጁ በሚፈቅደው መሠረት ለመመለስ መሞከሩ በሰው አገር ከመሞት የተሻለ አማራጭ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy