Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሁንም ህገ ወጥ ስደትን እንታገል!

0 356

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁንም ህገ ወጥ ስደትን እንታገል!

                                                       ታዬ ከበደ

በዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት የተከበረ ነው። የማይሰደድ ህዝብ የለም። ስደት ገፅታው ፈርጀ ብዙ ቢሆንም ህጋዊ ሊሆን ይገባል። ስለ ህገ ወጥ ስደት አደጋ መክፋት ብዙ ተብሏል። መንግስትና ማህበረሰቡ ማድረግ ስለሚገባቸው ጉዳዩች ብዙ ተነግሯል። የስደት አሳፋሪ ሁኔታ ተገልጿል። በዜጎችና በሀገር ላይ ስለሚያስከትለው ቀውስ ተወስቷል። ያም ሆኖ ህገ ወጥ ስደት አሁንም የአገራችን ችግር ሆኗል። ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አልተቻለም።

የግንዛቤ ጉዳይ ቀዳሚውን ስፍራ ይወስዳል። አንዳንድ ወገኖች ህገ ወጥ ስደትን የመግታት ኃላፊነት የመንግስት ብቻ ይመስላቸዋል። ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው። መንግስት ማለት ህዝብ ነው። ምንም እንኳን መንግስት የህዝቡን ይሁንታ ተቀብሎ የሚሰራ ቢሆንም የህዝቡ ድጋፍ ካልታከለበት የትም ሊራመድ አይችልም። እናም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለህጋዊነት ቅድሚያ በመስጠት የህገ ወጥ ስደት ችግርን ለመቅረፍ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለየ መልኩና በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ የሚቻልበት መንገድ እያለ ስደትንና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ዜጎች መኖራቸው የሚታበይ አይደለም። እርግጥ ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር የሁሉም ታዳጊ ሀገሮች ችግር ነው። እናም ሀገራችንም በችግሩ ከሚጠቁት መካከል አንዷ እንዲሁም የድርጊቱ መነሻና መሸጋገሪያ ናት። በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገው ህገ- ወጥ የስዎች ዝውውር ወይም ስደት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የዜጎቻችን መዳረሻ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል።

የህገ-ወጥ ዝውውሩ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ወጣት ሴቶችና ወንዶች በመሆናቸው በቀላሉ ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እነዚህ ዜጎች ውጭውን እንጂ ውስጣቸውን በቅጡ ማማተር ያልቻሉ ይመስለኛል። በዓለማችን ካለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ሳቢያ የትኛውም ሀገር ማርና ወተት የሚዘንብበት አለመሆኑን በበቂ ሁኔታ የተገነዘቡ አይመስለኝም። እርግጥ በህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ የሚጠቁ ኢትዮጵያውን የስደታቸው መንስዔ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ከፊል ዕውነታ ያለው እሳቤ ሊሆን ይችላል። የተሟላ አስተሳሰብ ነው ማለት ግን አይቻልም።

እርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ይገባኛል። ይሁንና የችግሩ መንስዔ ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻሉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ-ወጥ ደላሎች ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡

በላቡና በወዙ ጥሮ…ግሮ ህይወቱን ለመለወጥና ሀገሩን ለመጥቀም የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ ሲቻል ህገ- ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ አግባብነት ያለው ተግባር አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ዕድገቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ልማታዊ ሥራዎች ላይ በመሳተፋቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ለመዳን ችለዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየረዱ ነው። ይህ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

ዛሬ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም።

መንግስት የቀየሰውን አዲስ የስራ ባህል በተግባር በመተርጎምና ያገኙትን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሚሊየነር ለመሆን የበቁ ዜጎቻችን ሊፈጠሩ ችለዋል። በአንፃሩ ደግሞ ለጥቂት አፍራሽ ሃይሎች አሉባልታ ተንበርክከውና ወደ ውጭ በማየት የማያውቁትን ሀገር ሲናፍቁ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

እርግጥ በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅቶ በሀገር ሰርቶ ማደግና መለወጥ እየተቻለ የአጭበርባሪ ደላላዎች ሲሳይ ሆኖ ለችግር መጋለጥ አሳዛኝ ቢሆንም፤ አሁንም አልረፈደምና ዕውነታውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የውጭው ዓለም ወተትና ማር የሚያዘንብ የሚመስላቸው ወገኖች አሉ። የዚህ ቅስቀሳ አራማጆች ደግሞ ህገ ወጥ ደላላዎች ናቸው። ይህ በመሆኑም ለህገ- ወጥ የሰው ዝውውሩ አለመቅረት ምክንያት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ ድህነትን ለማስወገድ የምታካሂደውን ጥረት ለማደናቀፍ በሚደረግ የተሳሳተ ቅስቀሳ ስለባ ሆነው ውጪውን እንዲያማትሩ የተገደዱ ዜጎች ሁኔታ ዛሬም ድረስ ያልቆመ ስለሆነ ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ ዜጎችን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሃይሎች ከመኖራቸው በተጨማሪ፤ የዜግነት ርህራሄ ያልፈጠረባቸው ወገኖችም ችግሩን ዛሬ ላይም ቢሆን አሳሳቢ እንዲሆን ማድረጋቸው አልቀረም። በተለይም የወጣቱን ቀልብ በሌለ ጉዳይ በመሙላት ህገ ወጥ ደላላዎች የሚጫወቱት አሉታዊ ሚና በቀላሉ የሚተይ አልሆነም።

ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ ማንም ባዶ እጁን እንደማይቀር ከወጣቱ ይልቅ የተሻለ ግንዛቤ ያለው ቤተሰብ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ታዲያ ይህንን እውነታ አሳምኖና አስረድቶ የማይጨበጥ ተስፋ አስተሳሰብን በመስማት ቤተሰብም የጉዳዩ ተባባሪ በመሆን የአጋዥነት ሚና ሲጫወት ይታያል። ጥሪታቸውን ሸጠው አሊያም ተበድረው ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች በርካታ ናቸው።

ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን የህገ ወጥ ስደት ችግር ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል።  መንስአኤዎቹን አውቀንም ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy