Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሜሪካና ኳታር የጀመሩት አዲሱ ጨዋታ

0 799

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሜሪካና ኳታር 12 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የኤፍ-15 ተዋጊ ጀቶች የግዢ ስምምነት ተፈራር መዋል፡፡ የግዢ ስምምነቱ አሜሪካ የአረብ ባህረ ሰላጤ አገራት ለገቡበት ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግ እየሠራሁ እገኛለሁ በምትልበት ወቅት ላይ መፈፀሙ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ በሁለቱ አገራት ስምምነት ግራ እንደተጋባ የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ናቸው፡፡

የኳታር ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው፣ ስምምነቱን በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲ.ሲ የተፈራረሙት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ጀኔራል ጀምስ ማቲስ እና የኳታሩ አቻቸው ካሊድ አልአቲያህ ናቸው፡፡

ከስምምነቱ መፈራረም በኋላ የኳታር መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ አልአቲያህ፣ ስምምነቱ ኳታር ከአሜሪካና ከሌሎች አጋሮቿ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር በማጠናከርና አብሮነት በማደርጀት በአረብ ባህረ ሰላጤ አካባቢ የሚስተዋለውን ፅንፈኝነትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ማጠናከሪያ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ስምምነቱ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማጠናከሪያ አንድ እርምጃ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የደህንነት ትብብር ለማገዝ እንደሚያስችል አመልክቷል፡፡

ዋሽንግተንና ዶሃ የተፈራረሙት አዲሱ ስምምነት አሜሪካ 110 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሳሪያ ለሳዑዲ አረቢያ ለመሸጥ ከተስማማች አንድ ወር እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያና ኳታር ደግሞ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ካቋረጡ ሁለት ሳምንታት እንኳ ሳይሞላቸው ነው፡፡

በቅርቡ ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ሌሎች የአረብ ባህረ ሰላጤ አገራት ኳታር አሸባሪዎችን ትደግፋለች በሚል ክስ ምክንያት ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር እንደዘጋችና ባህሬን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና ራሷ ሳዑዲ አረቢያ የበረራ ክልላቸውን ለኳታር አየር መንገድ በመከልከል በሰዎችና የንግድ ዕቃዎች ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኳታር በበኩሏ ክሱን ውድቅ እንዳደረገችው ይታወቃል፡፡

የባህረ ሰላጤው አገራት በሳዑዲ አረቢያ ፊታውራሪነት የክስ ሾተላቸውን በኳታር ላይ በመዘዙ ጊዜ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን መሃል ሰፋሪ ሆነው ዝም ቢሉም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ኳታር ጥፋተኛ ናት እያሉ በትዊተር ገፃቸው በሚያሰፍሩት መልዕክት የኢሚር ሼህ ታሚን ቢን ሐማድ አልታሃኒን አገር ሲከሱ ነበር፡፡

ታዲያ የ12 ቢሊዮን ዶላሩን የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ዳር ዳር እያለች የነበረችው አሜሪካ ኳታርን ለማግባባት በሚመስል ሁኔታ፣ ሳዑዲ አረቢያ በኳታር ላይ የጠመጠመችውን እስር ላላ እንድታደርግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ትዕዛዝ ብጤ መልዕክት አስተላለፈች፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የሁለቱን አገራት ውዝግብ ለመፍታት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ከኳታር ጦር ጋር ልምምድ ለማድረግ ወደ ኳታር እንዳቀኑ ተገልጿል፡፡ የኳታር ዜና አገልግሎት የአገሪቱን የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ከዶሃ በስተደቡብ ከሚገኘው ሃማድ ወደብ የደረሱት ከኳታር ባህር ኃይል ጋር በመሆን የጦር ልምምድ ለማድረግ ነው፡፡ የጦር መርከቦቹ ወደቡ ላይ ሲደርሱም በኳታር የባህር ኃይል አባላት አቀባበል እንደተደረገላቸው በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ድርጊቱ ከባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ቀውስ ቀድሞ የታሰበበት አልያም ከቀውሱ በኋላ ፔንታጎን ለኳታር መንግሥት ድጋፉን ያሳየበት እርምጃ እንደሆነ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም ተብሏል፡፡

ኳታር በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ግዙፉ የአሜሪካ ባህር ኃይል ማዘዣ ጣቢያ ያለባት አገር ስትሆን አልኡደይድ በተባለው የቀጣናው ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያ 11ሺ የአሜሪካ ወታደሮችና 100 የጦር አውሮፕ ላኖች ይገኛሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy