Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አብረን እንልማ ወይስ አብረን እንቆርቁዝ?

0 1,109

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግብር ዕዳ አይደለም፣ የሥራ አደራ መስጠት እንጂ

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን  በያዝነው ዓመት የነጋዴዎች የእለት ገቢ ግምት ጥናት አካሂዷል። የእለት ገቢ ግምት ጥናቱ ዓላማ ነጋዴዎች ከገቢያቸው ጋር የተመጣጠነ ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ የሚያስችል ተጨባጭና ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት የገቢ ግምት ጥናት ባለመካሄዱ ነጋዴዎች የሚከፍሉት የገቢ ግብር ወቅታዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም። እናም ጥናቱ እንዲካሄድ መድረጉ ተገቢ ነው። አሁን ጥናቱ ተጠናቆ ገቢያቸው ላይ ለውጥ የተገኘባቸው ነጋዴዎች (በቅናሽም ይሁን በጭማሪ) ይፋ ተደርገዋል።  ከሃምሌ 1፣ የ2009 ዓ/ም ጀምሮ በአዲሱ መረጃ መሰረት የገቢ ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል። በአዲሱ የገቢ ግምት ጥናት ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ነጋዴዎችም የይግባኝ አቤቱታ እንዲያቀርቡ እድል ተሰጥቷቸዋል።

በአዲሱ እለታዊ የገቢ ትመና ላይ ቅሬታ  ያላቸው ነጋዴዎች የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ እድል የተሰጣቸው መሆኑ ሳይዘነጋ፤ ውስጥ ውስጡን በደል ተፈጽሞብኛል የሚሉ ሃሜታዎች ይሰማሉ። ካጋጠሙኝ ሃሜተኞች መሃከል አንዳንዶቹ ጭራሽ ለምን ግብር እንድንከፍል እንጠየቃለን የሚሉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። በተሰማሩበት የንግድ ስራ G + የመኖሪያ ቤት ገንብተው፣ የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች ገዝተው፣ የግል አውቶሞቢል ገዝተው፣ ልጆቻቸውን በከፍተኛ ክፍያ የውጭ ሃገራት ኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ . . . ከግብር ከፋይ ደረጃ ‘ሐ’ ወደ ደረጃ ‘ሀ’ ለምን እንድሸጋጋር ተደረገ ብለው መንግስትን የሚያረሩ አጋጥመውኛል። አኔ ያስገረመኝ ወደ ደረጃ ‘ሀ’ እንዲሸጋገሩ መደረጉ ሳይሆን፣ በምን አግባብ ለእለት ጉርስ ከሚሰሩ አነስተኛ ነጋዴዎች እኩል ደረጃ ‘ሐ’ ላይ ተመደበው ግብር ሲከፍሉ እንዲቆዩ እንደተደረገ ነው። የዚህ አይነት ነጋዴዎች ግብር ለምን እንከፍላለን እያሉ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ፣ አገልግሎት በመስተጓጎሎ የበለጠ የሚጎዱት፣ የበለጠ ስለሚጎዶ አብዝተው የሚያማረሩትም እነዚሁ ከፍተኛ ነጋዴች ናቸው።

ያም ሆነ ይህ፤ አዲሱ የነጋዴዎች የእለታዊ ገቢ ትመና የመንግስትን ግብር የመሰብሰበ አቅም በመጠኑም ቢሆን ያሻሽለዋል ተብሎ የገመታል።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ግብር የሚከፈልባት ሃገር አይደለችም ማለት ይቻላል። ሃገሪቱ በግብር የምትሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (GDP) ከአስር በመቶ ብዙም አልዘለለም። ይህን ያህልም የደረሰው በቅርቡ ነው። የበለጸጉ ሃገራት የአጠቃላይ ዓመታዊ ምርታቸውን ከ40 በመቶ በላይ ግብር ይሰበስባሉ። ከሳህራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራት እንኳን እስከ ሃያ በመቶ ግብር ይሰበስባሉ። ምናልባት የተረጋጋ መንግስት ኖሮ የኢትዮጵያን ያህል ዝቅተኛ ግብር የሚሰበሰበበት ሃገር አለ ብሎ መናገር ስህተትነቱ ያይላል። በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው ግብር ከሳህራ በታች ከሚገኙ ተመጣጣኝ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸውን ሃገራት ያህል (እስከ ሃያ በመቶ) መሰብሰብ ቢቻል አሁን ያለውን የመንግስት ገቢ በእጥፍ የሚያሳድግ መሆኑን ልብ በሉ። ይህ ደግሞ አሁን በመንግስት የሚከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን በእጥፍ ማሳደግ ማለት ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ መንግስት በየዓመቱ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመድበው ዓመታዊ በጀት በየዓመቱ እያደገ መጥቷል። በግብር መልክ የሚሰበሰበው ገቢ ከዓመታዊ አጠቃላይ ምርት አኳያ ያለው ምጣኔ የዛን ያህል እድገት ባያሳይም፣ ኢኮኖሚው በማደጉ ምክንያት መንግስት የሚሰበስበውም አጠቃላይ ገቢ እድገት አሳይቷል።

መንግስት የሚመድበው ዓመታዊ በጀት በምን ያህል መጠን እንዳደገ ለመረዳት ከ2004 ዓ/ም ወዲህ ባሉ ዓመታት የተመደቡ ባጀቶችን መጠን እንመልከት (በየዓመቱ አጋማሽ የሚደረጉ ተጨማሪ ባጀቶች ሳይጨምር)። ባለፉ ስድስት ዓመታት የተመደበው ዓመታዊ የፌደራል መንግስት ባጀት በ2004 ዓ/ም 128 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፣  በ2005 ዓ/ም 137 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፣ 2006 ዓ/ም 154 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ፣ 2007 ዓ/ም 178 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ፣ 2008 ዓ/ም 223 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር  በ2009 ዓ/ም 274 ቢሊየን ነው። ለመጪው 2010 የበጀት ዓመት ደግሞ 320 ቢሊንየን ብር ለመመደብ ታቅዷል። የድጎማ በጀቱን ሳይጨምር በጀቱ በየአመቱ  ከ10 በመቶ በላይ እድገት አሳይቷል። ይህ የባለፉ ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት ውጤት ነው።

ይሁን እንጂ እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የመንግስት ባጀት ከውጭ በሚገኝ ድጋፍና ብድር የሚሸፈን ነው። ይህም ሆኖ መንግስት ከራሱ ገቢ ለመሸፈን ያቀደውን ድርሻ እንኳን ማሟላት እያቃተው ከሃገር ውስጥ የገንዘብ ምንጭ በመበደር የሚያሟላበት ሁኔታ ነው ያለው። እርግጥ ይህ ጉድለት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ሃገራዊ ምርት ከ3 በመቶ ያነሰ በመሆኑ የኢኮኖሚ ቀውስ የመፍጠር አቅም የሌለውና እንደጤናማ ጉድለት የሚወሰድ ነው። ሆኖም ሃገሪቱ አሁንም ዓመታዊ በጀቷን ሙሉ በሙሉ በራሷ አቅም የምትሸፍነበት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት።

የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሰሞኑን የመንግስት ገቢ አሰባሰብን ማሻሻልና የበጀት አጠቃቀምን የተመለከተ አጀንዳ ላይ ያተኮረ ስብሰባ አካሂዶ ነበር። ሚኒስቴሩ ከነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ባካሄደው ስብሰባ ላይ፣ በ2009 ዓ/ም የነበረው የግብር አሰባሰብና የወጪ ንግድ ገቢ ደካማ መሆኑ ተገልጿል። ይህ  ደካማ የግብር ገቢ አሰባሰብና እያሽቆለቆለ የመጣው የወጪ ንግድ ገቢ ሳይስተካከል የ2010 በጀትን ማሳካት አዳጋች እንደሚሆንም ተገልጿል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ፣ በግብር ገቢ አሰባሰብና በወጪ ንግድ አፈጻጸም ዙሪያ የታዩ ክፍተቶችን በውይይቱ ወቅት አንስተዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ለ2010 በጀት ዓመት የቀረበው 320 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ረቂቅ በጀት ከዘንድሮው በጀት ዓመት አንጻር የ9 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ አለው። ከዚህ ውስጥ  196 ቢሊየን ብሩን ከግብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል። ይሁን እንጂ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከታየው የግብር ገቢ አሰባሰብ ክፍተት አንጻር ይህን እቅድ ማሳካት አስቸጋሪ እንደሚሆን የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ አስታውቀዋል። እየተጠናቀቀ ባለው የ2009 በጀት ዓመት ከግብር ገቢ 171 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም፣ በ11 ወራቱ 120 ቢሊየን ብር ብቻ መሰብሰቡን ለዚህ ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል።

የሃገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ደካማ እየሆነ መምጣትም የታቀደውን ባጀት ማሟላት ላይ መሰናክል ሊሆን እንደሚችል ተነስታል። በ2009 ዓ/ም ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉ 11 ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው። ይህ ክንውን ከእቅዱ 59 በመቶ ብቻ ነው። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 1 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ለበጀቱ የሚስፈልገውን ገቢ አሟልቶ መሰብሰብ እንዲቻል፣ የግብር አሰባሰቡን አሁን ያለበትን ዝቅተኛ አፈጻጸም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ፣ ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ጋር ተያይዞም በተወሰኑ የምርት አይነቶች ላይ ብቻ የተገደበውን የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ማስፋት እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ግብር ከፋይ ኢትዮጵያውያን አንድ ሊዘነጉት የማይገባ ነገር፣ ግብር መክፈል ለሌላ ሳይሆን ለራስ መሆኑን ነው። ግብር መክፈል በግለሰብ ወይም በሰፈር እድር ደረጃ ሊከናወን የማይችል የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ስራን መንግስት እንዲያከናውን ከአደራ ጋር ሃላፊነት መስጠት እንጂ ከንቱ ወጪ አይደለም። እናም ግብር እዳ ሳይሆን ስራዬን አከናውንልኝ የሚል አደራ ለመንግስት መስጠት መሆኑን በማስታወስ በገቢያችን ልክ ግብር ለመክፈል አንሳሳ። ግብር እዳ አይደለም፣ ለመንግስት የስራ አደራ መስጠት እንጂ።

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy