Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግን ቀስቅሱት

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግን ቀስቅሱት

አሜን ተፈሪ

ኢህአዴግ በራሱ ሥር የሰደዱ እንከኖች ሳቢያ የስርዓት ቀውስ ከሚጋብዝ ችግር ውስጥ ሊዘፈቅ የማይችል ጠንካራ ድርጅት መሆኑን በሚታመኑ ዜጎች፣ የድርጅቱ ደጋፊዎች እና አባላት ዘንድ ከባድ ድንጋጤን ያስከተለ ችግር ተጋፍጦ በጥልቅ ተሐድሶ ንቅናቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ የተከሰተው ችግር፤ የፌዴራላዊ -ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ጸንቶ መቆየት እና ከማይቀለበስበት ደረጃ መድረስ ከኢህአዴግ ጋር ተያይዞ ለሚታያቸው ኢህአዴጋውያን ጭምር አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ በተቃዋሚዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ድህነት እና ጽንፈኛ አቋም የተነሳ ድርጅቱን ከእነ እንከኑም ለመደገፍ የሚገደዱ ኢህአዴጋውያን አሳዝኗል፡፡ የስርዓቱ አለኝታ አድርገው ይመለከቱት እና ከእነ እንከኑም ሊደግፉት የሚፈቅዱት ድርጅት፤ ራሱ ‹‹የስርዓቱ ጠላት›› ከመሆን ደረጃ የሚያደርስ ችግር ውስጥ ገብቶ ሲመለከቱ እጅግ አዝነዋል፡፡

በርግጥ ችግሩ ከድርጅቱ የፖለቲካ ትንታኔ አድማስ ውጪ በሆነ እና ተገማች ባልሆነ (ግሎባላዊ) ክስተት ሳቢያ የተፈጠረ ችግር ቢሆን ተስፋ ለመጽናናት ባልተቸገሩ ነበር፡፡  በቁጭት ስሜት ባልተወዘወዙ ነበር፡፡ ሆኖም የስርዓቱ ታማኝ ባለአደራ አድርገው ከሚመለከቱት ኢህአዴግ፤ አጠቃላይ ስርዓቱን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ችግር ሲመለከቱ ተረብሸዋል፡፡

ሐገሪቱን ለዘመናት ሲያደማ ለቆየው ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ ያዋለደ፤ በምድሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ ያደረገ፤ ህዝቦችዋን በድህነት ግርግም አስሮ ያኖረ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም እና ኢትዮጵያውያን የሰላም – የልማት – የዴሞክራሲ ጣዕምን እንዲቀምሱ ያደረገው ኢህአዴግ እንዴት ከዚህ ደረሰ በሚል ተብከንክነዋል፡፡ በአጠቃላይ ከተፈጠረው ችግር ሊወሰድ የሚችለው ትምህርት፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደ ዓይን ብሌን የሚሳሱለትን ፌደራላዊ – ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ከጠላቶቹ ብቻ ሣይሆን ‹‹ከወዳጆቹም›› ጭምር ሊጠበቅ የሚገባው መሆኑ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም በግልጽ ጦር ሰብቀው ከሚመጡ የስርዓቱ ጠላቶች ይልቅ፤ ከወዳጆቹ ጎራ የሚወረወሩ ጥቃቶች አደገኛ የሚያስተምር ይመስለኛል፡፡  

ሁላችንም እንደምናውቀው፤ ድርጅቱ በቀረጻቸው የፖሊሲ ሰነዶች፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ መስና እና ጸረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎች የስርዓቱ አደጋዎች መሆናቸው በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህ ችግር ለኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ የሆኑ ፖለቲካ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በመቀየር የሚወገድ ችግር እንጂ ዘበኛ በማቆም ወይም በኩርኩም ሊወገድ የማይችል አደጋ መሆኑንም ሰነዶቹ በግልጽ ያስረዱናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ግድም ከኢ.ቢ.ሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደ ተናገሩት ኪራይ ሰብሳቢነት በዘላቂነት ማስወገድ የሚቻለው ፈጣን ልማትን በማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህም የኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በአጭር ጊዜ ማዕቀፍ የማይፈታ እና ስትራቴጂያዊ የትግል ግብ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም እንዳሉት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመድፈቅ፣ ለማዳከም እና ለማስወገድ የሚደረግ ትግል ቀጥተኛ ጎዳናን የሚከተል አይደለም፡፡ ‹‹ጉዞው ቀጥተኛ አይደለም፤ ዚግዛግ ነው፡፡ አንዳንዴ ልማታዊነት ሲቀዘቅዝ፤ ኪራይ ሰብሳቢነት ጉልበት አግኝቶ ብቅ ይላል፡፡ በሌላ ጊዜ፤ ልማታዊነት ሲጠናከር፤ ኪራይ ሰብሳቢነት ይደፈቃል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ ሁኔታ አግኝቶ ብቅ ሲል፤ አናት – አናቱን እያሉ መልሶ ወደ ውስጥ እንዲደፈቅ ማድረግ የሚካሄድ ትግል ነው›› በማለት ትግሉ ፈታኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ልማታዊነት ሁሌም ግለቱን ጠብቆ እንዲኖር በማድረግ እና ልማትን በማፋጠን ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ የሆነውን ነባራዊ ሁኔታ በፍጥነት ለመቀየር ጥረት ከማድረግ ውጭ ሌላ አቋራጭ የመፍትሔ ጎዳና እንደሌለም ግልጽ አድርገዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የፓርቲያቸው ትንታኔ ትክክል ነው፡፡ ለዳር ተመልካች ግራ አጋቢ የሚሆነውም፤ ድርጅቱ እንዲህ አብጠርጥሮ በሚያውቀው እና ለበርካታ ዓመታት ሲያማርረው በቆየው ችግር ሳቢያ ስርዓቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመጠበቅ ከሚያስገድድ ቀውስ መግባታችን ነው፡፡ የኢህአዴግ አስቀድሞ በሚያውቀው እና ዘወትር ‹‹ከፊቴ የተጋረጠ አደጋ›› በሚለው ችግር ተጠልፎ ሲወድቅ ማየት፤ ድርጅቱ መፋዘዝ ውስጥ እንደቆየ የሚመሰክር ነው፡፡ ችግሩን በጊዜው ኮርኩሞ ባለመድፈቁ፤ የህዝብ ቅሬታ እና ብሶት ተጠራቅሞ፤ ጽዋው ሞልቶ ሊፈስ ሲወዛወዝ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ በጥናት ላይ የተመሠረተ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር መሻሻያ እና የፀረ- ሙስና ጦርነት ባወጀ ማግስት፤ የህዝብ ቁጣ ገነፈለ፡፡ ኢህአዴግ እጁን ሲዘረጋ እና ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ አንድ ሆነ፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ከፍ ሲል በተጠቀሰው ቃለ መጠይቅ እንደተናገሩት፤ ‹‹ኢህአዴግ መለካት ያለበት፤ በሚያጋጥሙት ችግሮች ሳይሆን ለችግሮቹ በሚያስቀምጠው መፍትሔ እና መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠውን ለማስፈጸም በሚያደርገው ትግል እና በሚያስገኘው ውጤት›› ብለው ነበር፡፡ በዚህ ሐሳባቸው እስማማለሁ፡፡ ድርጅቱ በጥልቅ መታደስን የሚጠይቅ ችግር ውስጥ መሆኑን መቀበሉ እና ጥልቅ ተሐድሶ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሩ በህዝቡ ዘንድ ተስፋ አሳድሯል፡፡        

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ፤ ወደ ሞት የሚገፉ ከባባድ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አደጋዎች እያጋጣሙት፤ ለችግሮቹ ትክክለኛ መፍትሔ እያስቀመጠ በድል ጎዳና መዝለቁን አውቃለሁ፡፡ ኢህአዴግ፤ ‹‹ታመመ! -በቃ ሞተ!›› ሲሉት፤ አፈር ልሶ – እንደ ንስር ታድሶ እየተነሳ፤ በቁርጠኛ እና ሐቀኛ የትግል መንፈስ ችግሮቹን እያሸነፈ በድል መንገድ እየተራመደ ተጉዟል፡፡ ረጅም የትግል ጎዳናውን በድል መዝሙር እያደመቀ፤ በታሪክ መዝገብ ላይ ገድል እያረቀቀ በመጓዝ ከዚህ ደርሷል፡፡ በመንገዱ ርዝመት፣ በጎዳናው ጠመዝማዛነት፣ በፈተናው ውስብስብነት፣ በትግሉ አስቸጋሪነት እና በመከራው ጽናት ሳይሸነፍ ከዚህ የትግል ምዕራፍ ተገኝቷል፡፡ ለፈተናዎች እጅ ሰጥቶ ሳይንበረከክ ተጉዟል፡፡ ‹‹እንዳያልፉት የለም›› የሚያሰኙ በርካታ መሰናክሎችን በብቃት ተሻግሯል፡፡

የእልፍ ሰማዕታትን ክቡር ደም አጥቅሶ፤ ከአጥንታቸው ፍንካች ብዕር ቀርጾ፤ የውርዝውና ዘመናቸውን ሳይሳሱ በገበሩ ታጋዮች ሞት ታሽቶ በለዘበ የታሪክ ብራና ታላቅ የድል ገድል ደጉሷል፡፡ ይህ ድርጅት፤ እንደ ጣዝማ ደረቅ ግንድን በሚሰረስር የግምገማ መድረክ አማካኝነት በየጊዜው የሚገጥሙትን ችግሮች በመለየት ራሱን እያረመ የመጓዝ ልዩ ባህል ያለው ድርጅት ነው፡፡ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቆቅልሾች የማንበብ፣ የመረዳት እና የመተንተን ብቃት ያለው ይህ ድርጅት፤ ራስን ያለ ርኅራኄ በመፈተሽ ባህሉ እየታገዘ ረጅም እና መራራ የትግል ጉዞውን በድል ችቦ አጸሕይቶ ብዙ የትግል ምዕራፎችን አልፎ መጥቷል፡፡

አሁን ድርጅቱ የነበረውን ጥንካሬ ይዞ መገኘቱ ዳግም የሚፈተንበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ ችግሮችን የመረዳት እና የማረም ብቃቱ በሚፈተንበት የትግል መድረክ ላይ ይገኛል፡፡ በየምዕራፉ የሚፈጠሩትን ወሳኝ የትግል አጀንዳዎችን ነቅሶ እያወጣ እና ራሱን ያለ ርኅራኄ እየገመገመ፤ መድረኩ የሚጠይቀውን የትግል አቋም በመገንባት ረጅም መንገድ የተጓዘው ይህ ድርጅት አሁን ‹‹በጥልቅ የመታደስ›› ንቅናቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ችግር ሲገጥመው፤ የችግሩን መንስዔ ውጫዊ በማድረግ የቅዠት እንቅልፍ ለመተኛት የሚሻ ድርጅት አይደለም፡፡ እስካሁን ባለው ታሪኩ በተጨባጭ እንደተገለጠው በማናቸውም ሁኔታ ለሚገጥሙት ችግሮች ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ የድል አድራጊነት ታሪኩ ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል፡፡

ከፊቱ ለሚጋረጡ የችግሮች ሁሉ ራሱን ባለቤት የሚያደርግ ሰው (ድርጅት)፤ ራሷን አሸዋ ውስጥ በመቅበር አደጋውን ለማምለጥ እንደምትሞክር ሰጎን፤ ራሱን ለአደጋ አጋልጦ አይተኛም፡፡ የሚያስብ አዕምሮውን በሰበብ ካቴና ጠፍሮ አይዘናጋም፡፡ ዘጠኝ ሞት ሲመጣበት አንዱን ግባ ብሎ ከችግሮች መደብ ላይ አይጋደምም፡፡ ለሚገጥሙት ችግሮች ሁሉ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ የሚነሳ ሰው (ድርጅት)፤ ለህመሙ ፈውስ የሚሆነውን መድኃኒት ለማግኘት የሰው እጅ አይመለከትም፡፡ ‹‹የችግሩ ባለቤት እኔ ነኝ›› የሚል ሰው፤ ራሱን የመፍትሔው ባለቤት ያደርጋል፡፡ እጅጌውን ሰብስቦ ለሥራ ይነሳል፡፡ በችግሮቹ ላይ ባለሥልጣን ይሆናል፡፡

የድርጅቱን ታሪክ የሚመለከት ሰው፤ ኢህአዴግ ችግር ሲገጥመው በዝንጋዔ ወይም በ‹‹ቆይ ነገ›› በሽታ የሚታወክበት አጋጣሚ ቢኖርም፤ በመጨረሻ ራሱን በድፍረት በመመርመር፤ ጠላቶቹ በማጥላላት መንፈስ የሚያወርዱበትን ውግዘት በሚያስከነዳ ኃይል ችግሮቹን ይፈትሻል፡፡ ይህን ታሪኩን ዳራ አድርገን ከተነሳን፤ ራሱን የችግሮቹ ባለቤት አድርጎ መውሰዱን ከግምት ካስገባን፤ ኢህአዴግ የጀመረው ‹‹በጥልቀት የመታደስ›› ንቅናቄ፤ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ንቅናቄ እንደሚሆን መተማመን ይቻላል፡፡ ሆኖም ከፍ ሲል በውዳሴ ያነሳነው የድርጅቱ ጥንካሬ ወይም ህዝባዊ ባህርይ በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ተሸርሽሮ እንዳይሆን የሚሰጉ ሰዎች፤ አሁን የተከሰተውን ችግር፤ ድርጅቱ ዛሬም ከነባር ጥንካሬው ጋር መገኘቱን ለማረጋገጥ የቀረበ ፈተና አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ለዚህም ነው፤ ‹‹ድርጅቱ ችግሮችን የመረዳት እና የማረም ብቃቱ ከሚፈተንበት የትግል መድረክ ይገኛል›› ያልኩት፡፡

ይሁንና ዛሬም እንደ ቀድሞው ያጋጠሙትን ችግሮች ውጫዊ ለማድረግ አለመሞከሩ እና የጠላቶቹን ወቀሳ እና ትችት በሚያስንቅ ደረጃ የራሱን ችግሮች በሰላ ትችት እየነቀሰ፤ ‹‹በሌዘርጀት›› ትኩረት ችግሮቹን መርምሮ እና አብጠርጥሮ ለማየት ‹‹በጥልቅ የመታደስ›› ንቅናቄ መክፈቱ፤ ከዚህ ጥረት የሚገኘውን ውጤት በተስፋ ለመጠበቅ በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡  ስለዚህ የመድረኩን ልዩ ባህርይ ተንትኖ፤ የመድረኩን አጀንዳዎች አጉልቶ እና ግልጽነት ፈጥሮ ለመሄድ የሚያደርገው ሙከራ፤ ድርጅቱ በጥልቅ ተሐድሶ ሂደቱ ቀጣዩን ምዕራፍ በስኬት ለመጓዝ የሚያበቃ ኃይል ይዞ ከችግሩ እንደሚወጣ በእምነት መናገር ይቻላል፡፡ ወድቆ መነሳትን ደጋግሞ የሚያውቀው ኢህአዴግ፤ ዛሬም ችግሮቹን እንደ ፀሐይ አጥርቶ በሚያሳይ የግምገማ ባህሉ ታግዞ፤ ብልሽቱን ገላልጦ ፈትሾ መፍትሔ በማስቀመጥ፤ አዲስ ኃይል ተሞልቶ የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግን ቀስቅሱት፤ በህዝብ የተሰጠውን ሥልጣን እና አደራ አክብሮ፤ ህዝባዊ ባህርይውን ጠብቆ፤ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል አኳኋን ራሱን አስተካክሎ እንደተለመደው የትግል ጉዞውን ይቀጥላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy