Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአቅም የመነጨ እርግጠኝነት

0 722

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአቅም የመነጨ እርግጠኝነት

ብ. ነጋሽ

ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ተመትታለች። በ1985/86፣ በ1992/93፣ በ2001/2002 እንዲሁም ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ ያጋጠሙት ድርቆች ተጠቃሽ  ናቸው። እነዚህን የባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ድርቆች ከዚያ ቀደም ከነበሩት ድርቆች ጋር የሚያመሳስላቸው  የሚያለያያቸውም ነገር አለ። የሚያመሳስላቸው እንደ 1965/66ቱ፣ እነደ 1976/77ቱ ድርቅ ሁሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸው ነው። ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ እንደ 1965/66ቱ እና 1966/77ቱ እንዲሁም ከእነዚህ ቀደም  እንዳጋጠሙት ድርቆች የምግብ እጥረቱ ወደቸነፈረነት ተለውጦ የሰው ህይወት ያልጠፋባቸው፣ ሰዎች ከመኖሪያ ቂዬአቸው ያልተፈናቀሉበት መሆኑ ነው።

በተመሳሳይ፣ ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በድርቅ ምክንያት ካጋጠሙት የምግብ እጥረቶች መሃከል በተለይ የባለፈው ዓመትና የዘንድሮው፣ በ1985/86፣ 1992/93 እና በተወሰነ ደረጃ በ2001/2002 ከተከሰቱት ጋር የሚመሳሰሉበትም የሚለያዩበትም ነገር አለ። የሚያመሳስላቸው የምግብ እጥረቶቹ ወደቸነፈርነት ተለውጠው የሰው ህይወት አለመጥፋቱና ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው አለመፈናቀላቸው ነው። የባለፈውን ዓመትና የዘንድሮውን ከቀደሙት የሚለየው ደግሞ የምግብ እጥረቱን ለመከላከል በተከናወነው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የማቅረብ ተግባር ውስጥ የኢፌዴሪ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ መያዙ ነው። ቀደም ያሉትን ድርቆች ተጽእኖ የመከላከሉ ተግባር በዋነኝነት በውጭ እርዳታ የተከናወነ ነበር።

የኢፌዴሪ መንግስት ባለፈው ዓመት፣ በድርቅ ምክንያት በሚያጋጥም የምግብ እጥረት የአንድም ሰው ህይወት አይጠፋም፣ አንድም ሰው ከመኖሪያ ቂዬው አይፈናቀልም የሚል አቋም ይዞ፣ ይህን በይፋ አሳውቆ በተጨባጭ ተግባራዊ አድርጓል። ድርቅ ባስከተለው የምግብ እጥረት ሳቢያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጠባቂነት የተጋለጡት ሰዎች ቁጥር ከመነሻው በአራት እጥፍ ገደማ ጨምሮ በነበረበት ወቅት እንኳን የሰዎችን ህይወት የመታደግ አቅም የነበረው መሆኑ ላይ ጥርጣሬ አላደረበትም። እርግጥ የተትረፈረፈ ሃብት አለኝ አላለም። ከዚህ ይልቅ የከፋ ሁኔታ ከመጣ የግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን ግንባታ ይጓተቱ ይሆናል እንጂ፣ ዜጎቼ በምግብ እጥረት ለረሃብ ተጋልጠው ህይወታቸውን አያጡም ነበር ያለው። ያም ሆነ ይህ የኢፌዴሪ መንግስት የግዙፍ ፕሮጀክቶቹንም ባጀት ማጠፍ ሳያስፈልገው፣ የ16 ቢሊየን ብር በጀት መድቦ፣ በእርዳታ አሰጣጡ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ዜጎቹን ክፉውን ቀን እንዲሻገሩ ማድረግ ችሏል።

መንግስት በእርዳታ አሰጣጡ ላይ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ የዜጎቹን ህይወት መታደግ መቻሉ ላይ የነበረውን መተማመንና አቅም ለመረዳት የባለፈው ዓመት ድርቅ ባስከተለው የምግብ እጥረት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ያደገበትን መጠን መለስ ብለን እናስታውስ።

እንደሚታወሰው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የበልግ ምርት ከሚሰበሰብበት የ2007 ዓ/ም ሰኔ ወር ማብቂያ ጀምሮ ነበር በድርቁ ምክንያት የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ይፋ ያደረገው። ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ከዚህ ግዜ ጀምሮ እየጨመረ የሄደውን ድርቁ ባስከተለው የምግብ እጥረት ሳቢያ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የተጋለጡ ዜጎችን ቁጥር በየወቅቱ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል።

ኮምሽኑ በየወቅቱ ይፋ ሲያደረገው በነበረው መረጃ መሰረት፣ በበልግ የዝናብ ስርጭት መዛባት ሳቢያ ሰኔ 2007 ዓ/ም ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡት ዜጎች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብቻ ነበር። ከ2007 በልግ  በተጨማሪ የክረምቱ ዝናብ መቆራረጥና መቆም በድርቁ ሳቢያ ለምግብ እጥረት የተጋለጡና የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር በሰኔ ወር ከነበረበት 2 ነጥብ 9 መሊየን በነሃሴ ወር ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ከፍ አለ። ጥቅምት 2008 መግቢያ ላይ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ፈላጊዎቹ ቁጥር 8 ነጥብ 2 ሚሊየን ደረሰ።  ታህሳስ ላይ ይፋ በተደረገው መረጃ መሰረት የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ደረሰ።

ልብ በሉ የኢፌዴሪ መንግስት ይህን በ6 ወራት ውስጥ በአራት እጥፍ ገደማ ያደገ የተረጂዎች ቁጥር ማስተናገድ የሚያስችል እርዳታ ማቅረብ ችሏል። ከዚህ በኋላ፣ የ2008 ዓ/ም በልግና ክረምት የዝናብ ስርጭት የተስተካከለ ስለነበረ 2009 ዓ/ም ጥር ላይ የተረጂዎቹ ቁጥር ከፍተኛ መቀነስ አሳይቷል። በዚህ መሰረት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተረጅነት ተጋልጠው ከነበሩት 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች መካከል 4 ነጥብ 6 ሚሊየኑ ከተረጅነት ወጥተው፣ ቁጥሩ ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ዝቅ አለ። ለእነዚህ ተረጂዎች እርዳታ ለማቅረብ 948 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ተገለጸ። የኢፌዴሪ መንግስት ከነበረበት በግማሽ ገደማ የቀነሰ የተረጂዎች ቁጥር፣ ባለፈው ዓመት የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እንዳደረገው እርዳታ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቆ ተግባሩን ቀጥሏል።

መጋቢት 2009 ዓ/ም ላይ ይፋ በተደረገ የተረጂዎች ቁጥር የጥናት ወጤት መሰረት የተረጂዎቹ ቁጥር ወደ 7 ነጥብ 78 ከፍ ማለቱ ተገለጸ። የተረጂዎቹ ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያቶች መሃከል ታህሳስ ወር ላይ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ውርጭ በማሳ ላይ የነበረ ሰብል ላይ  ያደረሰው ጉዳት ተጠቃሽ ነው።

አሁን በሃገሪቱ የሚገኙ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 7 ነጥብ 78 ገደማ ነው። ከእነዚህ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከሚቀርብላቸው ዜጎች ውስጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለ4 ነጥብ 7 ሚሊየኑ በራሱ አቅም እርዳታ እያቀረበ ይገኛል። 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት እርዳታ የሚቀርብላቸው ናቸው። ቀሪዎቹ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎችም የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በሚያስተባብራቸው የለጋሽ ተቋማት እርዳታ እየቀረበላቸው ይገኛል።

ታዲያ ከዚህ የእርዳታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ድንገት አንድ አደናጋሪ ወሪ በውጭ የመገናኛ ብዙሃን ተነዛ። በዚህ ወሬ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ያገኙ ሲመሰላቸው ትንሿንም ጉዳይ ደመቅ የማድረግ አባዜ ያለባቸው ሚዲያዎች እሽኮለሌ ብለዋል። ይህ ወሬ በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚቀረበው ድጋፍ ሰኔ ወር ላይ ስለሚያልቅ እርዳታ ፈላጊዎች ለአስከፊ ረሃብ ተጋልጠዋል የሚል ነበር።

10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎችን ያለአንድ መስተጓጎል የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ሲመግብ የነበረው የኢፌዴሪ መንግስት ድንገት ምን ገጠመው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር። እውነታው ግን ሌላ ይህ አልነበረም። ከ7 ነጥብ 78 ሚሊየን እርዳታ ፈላጊዎች ውስጥ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ያህሉ እርዳታ የማቅረብ ድርሻ የወሰደው የዓለም የምግብ ድርጅት ለእርዳታ የሚያቀርበውን ምግብ አሟጧል፤ ለቀናት የሚሆን ብቻ ነው የቀረው። ድርጅቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ከሰኔ በኋላ እርዳታ ማቅረብ አይችልም።  የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከራሱ ካዝና የሚያወጣው የእርዳታ በጀትም የለውም። እርዳታ የሚያቀርበው  ከአሜሪካ የተራድኦ ድርጅቶችና ከአውሮፓ ሀገራት በሚደረግለት ልገሳ ነው። እናም እነዚህ ለጋሶች ከሰኔ በኋላ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን የምግብ እጥረት ለገጠማቸው ኢትዮጵያውያን የሚያቀርበውን ምግብና ሌሎች እርዳታዎች እንዲሰጡት ነው “በክምችት ያለው እርዳታ ተሟጧል” የሚል ጥሪውን ያስተላለፈው። የዓለም የምግብ ፕሮግራም አልዋሸም። ይህ ከሰኔ በኋላ የሚሰጥ እርዳታ የለኝም የሚለው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጥሪ ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ እየቀረበላቸው የሚገኙ 7 ነጥብ 78 ሚሊየን ዜጎችን የሚመለከት ሳይሆን፣ ድርጅቱ እርዳታ አቀርባለሁ ብሎ በድርሻነት የወሰዳቸውን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ብቻ የሚመለከት ነው። በመሆኑም አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ይህን አዛብተው ከሰኔ በኋላ 7 ነጥብ 78 ህዝብ ለረሃብ ሊጋለጥ ነው ብለው የነዙት ወሬ ፍጹም የተሳሳተና በተጨባጭ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም። የአለም የምግብ ፕሮግራም “እርዳታ አቀርብላቸዋለሁ” በሎ በድርሻነት ለወሰዳቸው 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎቹ የሚያቀረበውን እርዳታ ለጋሾቹ ባይሰጡት እንኳን፣ እነዚህ ዜጎች ለረሃብ አይጋለጡም። የኢፌዴሪ መንግስት በራሱ አቅም እርዳታ እያቀረበላቸው ከሚገኙት 4 ነጥብ 1 ዜጎች ጋር ቀላቀሎ ለ5 ነጥብ 8 ዜጎች እርዳታ ማቅረብ ይችላል። መንግስት ይህን የማድረግ  ዝግጅትም፣ አቅምም አለው። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከዚህ ቀደምም እርዳታ ከሚያቀርብላቸው ዜጎች ውስጥ በተለይ ለህጻናትና ለእናቶች የሚሰጠውን አልሚ ምግብ ማቅረብ አቅቶት፣ መንግስት ይህን ሲሸፍን የቆየበት ሁኔታ ነበረ።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት በድርቅ ምክንያት ባጋጠመ የምግብ እጥረት የአንድም ሰው ህይወት እንደማይጠፋ፣ አንድም ሰው ከቂዬው እንደማይፈናቀል፣ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እንደማያቋርጡ በእርግጠኝነት ተናግሯል። ይህ እርግጠኝነት በተጨባጭ ካለው አቅም የመነጨ ነው። ይህን ደግሞ በተግባር አሳይቷል። እጅግ የከፋ የምግብ እጥረት እንኳን ቢያጋጥም በብዙ ቢሊየን በሚለካ ሃብት እያከናወነ የሚገኘውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለጊዜው ይገታ እንደሆን እንጂ ድርቅ ወደረሃብነት የሚቀየርበት ጊዜ አልፏል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy